በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከአንድ ትልቅ ዛፍ ላይ የቀረበ ጸሎት

ከአንድ ትልቅ ዛፍ ላይ የቀረበ ጸሎት

 “የተወለድኩት ይሖዋን በሚያገለግል ቤተሰብ ውስጥ ነው” ትላለች በአሁኑ ጊዜ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የምትኖረው ሬቸል። “የሚያሳዝነው ሰባት ዓመት ሲሆነኝ አባቴ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ያለውን ግንኙነት ያቋረጠ ከመሆኑም ሌላ ቀንደኛ ተቃዋሚ ሆነ። በዚህም የተነሳ ይሖዋን ማምለክ በጣም ከባድ ሆነብኝ። አባቴ የተለያዩ መደለያዎችን በማቅረብ ለምሳሌ ሞባይል እንደሚሰጠኝ፣ ዲዝኒላንድ ወደተባለ መዝናኛ ቦታ እንደሚወስደኝ፣ ሌላው ቀርቶ ክሬዲት ካርድ እንደሚሰጠኝ ቃል በመግባት ለይሖዋ የማቀርበውን አገልግሎት እንዳቆም ለማድረግ ይሞክር ነበር። አንዳንዴ ደግሞ ይሖዋን እንድተው ለማድረግ ሲል በኃይል ይደበድበኝ ነበር። መናገርም ሆነ መራመድ ካልቻልኩ ስብሰባ መሄዴን እንደማቆም በመናገር ይዝት ነበር። ሆኖም ምንም ነገር ይሖዋን ከማገልገል ሊያስቆመኝ አልቻለም። ፈጽሞ ከስብሰባዎች ላለመቅረት ቆርጬ ነበር።

 “አባቴ፣ እናቴ ባለችበት አይመታኝም ነበር። እናቴ እሱ እንደሚደበድበኝ ካወቀች እንደምትጎዳ ይነግረኛል። በወቅቱ አባቴ ማርሻል አርት በግድ ያስተምረኝ ስለነበር ሰውነቴ የሚበልዘው በዚያ ምክንያት እንደሆነ ለእናቴ ይነግራታል።

 “በጣም ልጅ ስለነበርኩና አባቴን ስለምፈራው ስለሚደርስብኝ ነገር ለእናቴ ልነግራት አልቻልኩም። የምነግረው ለይሖዋ ነበር። በሜሪላንድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ካለው ቤታችን ጀርባ ጫካ ስለነበር ወደዚያ ሄጄ በእግሬ ረዘም ላለ ጊዜ የመጓዝ ልማድ ነበረኝ። ጫካው ውስጥ አንድ ትልቅ ዛፍ ነበር፤ እዚያ ዛፍ ላይ ከወጣሁ በኋላ የሚመች ቅርንጫፍ ላይ ቁጭ ብዬ ይሖዋን አነጋግረዋለሁ። ስለሚሰማኝ ስሜት እንዲሁም በሕይወት ተርፌ ትልቅ ሰው እንድሆን ከረዳኝ እሱን እንዴት እንደማገለግለው በጸሎት እነግረዋለሁ። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ምን እንደማደርግ፣ ምን ዓይነት ቤተሰብ እንደሚኖረኝ እንዲሁም ሥቃይና ፍርሃት በማይኖርበት በዚያ ጊዜ ስለማገኘው ሰላምና ደስታም እነግረዋለሁ።

 “አባቴ በጉቦም ሆነ በድብደባ ለአምላክ ጀርባዬን እንድሰጥ ለማድረግ በሞከረባቸው ጊዜያት ሁሉ ይሖዋ ያጽናናኝና ያበረታታኝ ነበር። ታማኝና ጠንካራ ሆኜ እንድቀጥል ረድቶኛል።

 “በአሥር ዓመቴ የተጠመቅኩ ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። መጀመሪያ ላይ አባቴ ስለመጠመቄም ሆነ አቅኚ ስለመሆኔ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ሲያውቅ ግን በቡጢ ስለመታኝ መንገጭላዬ ተላቀቀ።

 “አንዳንዶች ገና ልጅ ስለሆንኩ አቅኚ ለመሆን ትንሽ ብቆይ የተሻለ እንደሆነ ይመክሩኝ ነበር፤ እንዲህ የሚሉኝ የውሳኔው ክብደት እንዳልገባኝ ስለተሰማቸው ነው። ደግሞም በአካባቢያችን የነበሩ ብዙ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ቀስ በቀስ ከይሖዋ ሲርቁ ተመልክቻለሁ። ሕይወታቸው ያተኮረው በጭፈራና በመዝናኛ ላይ ነበር። እውነት ለመናገር እነዚህ ልጆች ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ ያሉ ነበር የሚመስሉት። አንዳንዴ እንደ እነሱ መሆን ያምረኛል። ‘ስብከቴን ትቼ እንደ እኩዮቼ ዘና የማልለው ለምንድን ነው?’ የሚል ሐሳብ ይመጣብኛል። ግን እንዲህ ሲሰማኝ ስለ ጉዳዩ ለይሖዋ እነግረዋለሁ።

 “አሥራ አምስት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ አንድ ታዋቂ የሞዴሊንግ ድርጅት የሥራ ግብዣ አቀረበልኝ። በሚላን፣ ጣሊያን ካለው ቢሯቸው ጋር አብሬ ከሠራሁ በጣም ጥሩ ክፍያ እንደሚከፍሉኝ ነገሩኝ። ሞዴል መሆን፣ የተለያዩ መጽሔቶች ላይ መውጣትና ውድ ልብሶችን ለብሼ ብዙ መድረኮች ላይ መታየት እንደምችል ሲነግሩኝ ጓጉቼ ነበር። በወቅቱ አቅኚ ከሆንኩ ሦስት ዓመት ገደማ ሆኖኝ ስለነበር ‘ይህ ሥራ ራሴን ለማስተዳደርና ለረጅም ጊዜ በአቅኚነት ለመቀጠል ሊረዳኝ ይችላል’ ብዬ አሰብኩ። ደግሞም አባቴ ጥሎን ሄዶ ስለነበር በማገኘው ገንዘብ እናቴን መርዳት እንደምችል ተሰማኝ።

 “ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ለብዙ ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለችውን እናቴን እንዲሁም የምቀርበውንና የማከብረውን አንድ ሽማግሌ አማከርኩ። በተጨማሪም ሌላ ጊዜ እንደማደርገው ወደዚያ ዛፍ ሄጄ በጉዳዩ ላይ ይበልጥ ጸለይኩበት። ይሖዋ ያ ሽማግሌ በጋበዘኝ አንድ ጥቅስ አማካኝነት ጸሎቴን መለሰልኝ። ጥቅሱ መክብብ 5:4 ሲሆን ‘ለአምላክ ስእለት በምትሳልበት ጊዜ ሁሉ ስእለትህን ለመፈጸም አትዘግይ፤ ስእለትህን ፈጽም’ ይላል። በሙሉ ጊዜዬ ይሖዋን ለማገልገል ተስያለሁ፤ የቀረበልኝ የሥራ ግብዣ ደግሞ በመንፈሳዊ ሊጎዳኝ እንደሚችል ተሰማኝ። ስለዚህ ግብዣውን ላለመቀበል ወሰንኩ።

 “አሁን ያ ሁሉ አልፎ ትልቅ ሰው ሆኛለሁ! ከባለቤቴ ከሃሲር እና ዘጠኝ ዓመት ከሆነው ከልጃችን ከኮነር ጋር አስደሳች ሕይወት እየመራሁ ነው። ሃሲር የጉባኤ ሽማግሌ ነው፤ ኮነር ደግሞ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኗል። እኔም ላለፉት 27 ዓመታት፣ በሙሉ ጊዜ እያገለገልኩ ነው።

 “ከቤታችን ጀርባ ባለው ጫካ ውስጥ በዚያ ትልቅ ዛፍ ላይ ሆኜ ይሖዋን ረዘም ላለ ጊዜ ስላነጋገርኩባቸው ጊዜያት ብዙ ጊዜ አስባለሁ። ይሖዋ እንዲረዳኝ ለምኜው ነበር፤ እሱም አስደናቂ በሆነ መንገድ ረድቶኛል። አበረታቶኛል፣ አጽናንቶኛል እንዲሁም መርቶኛል። በሕይወቴ ሁሉ ይሖዋ እንዴት ያለ አስደናቂ አባት እንደሆነ በተደጋጋሚ አሳይቶኛል። በሙሉ ልቤ እሱን ለማገልገል በመምረጤ ደስተኛ ነኝ። በሕይወቴ ካደረግኳቸው ውሳኔዎች ሁሉ በጣም የሚያኮራኝ ይህ ውሳኔዬ ነው።”