በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“አሁን ጨካኝ ሰው አይደለሁም”

“አሁን ጨካኝ ሰው አይደለሁም”
  • የትውልድ ዘመን፦ 1973

  • የትውልድ አገር፦ ኡጋንዳ

  • የኋላ ታሪክ፦ ዓመፀኛ፣ ሥነ ምግባር የጎደለውና ሰካራም የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ

 የተወለድኩት ኡጋንዳ ውስጥ በጎምባ አውራጃ ነው። በዚያ የሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች በጣም ድሆች ነበሩ። በምንኖርበት አካባቢ ኤሌክትሪክ ስላልነበረ ምሽት ላይ ኩራዝ እንጠቀም ነበር።

 በግብርና የሚተዳደሩት ወላጆቼ ወደ ኡጋንዳ የመጡት ከሩዋንዳ ነው። የቡናና የሙዝ እርሻ ነበራቸው፤ ከሙዙ ደግሞ ዋራጊ የተባለ ተወዳጅ መጠጥ ይሠራሉ። ወላጆቼ ዶሮ፣ ፍየል፣ አሳማና ላም ያረቡ ነበር። የአካባቢያችን ባሕልና አስተዳደጌ ሚስት ምንጊዜም ለባሏ መገዛት እንዳለባትና ሐሳቧን መግለጽ እንደማይፈቀድላት እንዲሰማኝ አድርጓል።

 ሃያ ሦስት ዓመት ሲሆነኝ ወደ ሩዋንዳ ሄጄ በዚያ መኖር ጀመርኩ። እዚያም ከእኩዮቼ ጋር ጭፈራ ቤት እንገባ ነበር። እንዲያውም ቋሚ ደንበኛ ከመሆኔ የተነሳ የአንዱ ጭፈራ ቤት ኃላፊ በነፃ እንድገባ የሚያስችል ካርድ ሰጠኝ። ድብድብና ዓመፅ የሚታይባቸው ፊልሞች ማየትም እወድ ነበር። ጓደኞቼና የመዝናኛ ምርጫዬ ዓመፀኛ፣ ሥነ ምግባር የጎደለውና ሰካራም እንድሆን አደረጉኝ።

 በ2000 ዓ.ም. ስኮላስቲክ ካባግዊራ ከተባለች ሴት ጋር መኖር ጀመርኩ፤ ሦስት ልጆች ወለድን። ከልጅነቴ ጀምሮ እንደተማርኩት ስኮላስቲክ ሰላም ስትለኝም ሆነ አንድ ነገር ስትጠይቀኝ እንድትንበረከክ እጠብቅባት ነበር። ከዚህም ሌላ የቤተሰባችን ንብረት በሙሉ የግል ንብረቴ እንደሆነና የፈለግኩትን ነገር ላደርግበት እንደምችል ይሰማኝ ነበር። ብዙ ጊዜ ምሽት ላይ እወጣና ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ እመለሳለሁ፤ አብዛኛውን ጊዜ ሰክሬ ነበር የምመለሰው። በር ሳንኳኳ ስኮላስቲክ ወዲያውኑ ካልከፈተችልኝ እደበድባት ነበር።

 በወቅቱ በአንድ የጥበቃ ድርጅት ውስጥ ተቆጣጣሪ ሆኜ እሠራ ነበር፤ ጥሩ ደሞዝ ይከፈለኝ ነበር። ስኮላስቲክ ባሕርይው ይሻሻላል ብላ አስባ ሳይሆን አይቀርም እሷ ወደምትሄድበት የጴንጤቆስጤ ቤተ ክርስቲያን አብሬያት እንድሄድ ልታግባባኝ ትሞክር ነበር። እኔ ግን ፍላጎት አልነበረኝም። እንዲያውም ከሌላ ሴት ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀመርኩ። ጨካኝና ሥነ ምግባር የጎደለኝ ሰው በመሆኔ ምክንያት ስኮላስቲክ ሦስቱን ልጆቻችንን ይዛ ወላጆቿ ቤት ገባች።

 አንድ በዕድሜ ጠና ያለ ወዳጃችን ስለ አኗኗሬ ቆም ብዬ እንዳስብበት ነገረኝ። ወደ ስኮላስቲክ እንድመለስ አበረታታኝ። ልጆቻችን ያለአባት ማደግ እንደሌለባቸው ነገረኝ። ስለዚህ በ2005 መጠጣት አቆምኩ፤ ከዚያም ከሌላኛዋ ሴት ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋርጬ ከስኮላስቲክ ጋር መኖር ጀመርኩ። በ2006 ተጋባን። ያም ቢሆን ሚስቴን መበደሌንና መጨቆኔን አላቆምኩም።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

 በ2008 ዦኤል የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታችን መጣ፤ እኔም መልእክቱን አዳመጥኩ። ለበርካታ ወራት እሱና ቦናቬንቸር የተባለ ወንድም ወደ ቤታችን ይመጡ ነበር፤ የጦፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እናደርግ ነበር። ብዙ ጥያቄዎችን እጠይቃቸው ነበር፤ በተለይ ስለ ራእይ መጽሐፍ ብዙ ጥያቄ ነበረኝ። እርግጥ የምወያየው መሳሳታቸውን ላሳምናቸው ስለፈለግኩ ነበር። ለምሳሌ ራእይ 7:9 “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ‘በአምላክ ዙፋንና በበጉ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እንደቆሙ’ የሚናገር ከመሆኑ አንጻር “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ምድር ላይ ይኖራሉ ብለው የሚያስተምሩት ለምን እንደሆነ ጠይቄያቸው ነበር። ዦኤል ለጥያቄዎቼ በትዕግሥት መልስ ሰጠኝ። ኢሳይያስ 66:1⁠ን አሳየኝ፤ እዚያ ላይ አምላክ ምድርን “የእግሬ ማሳረፊያ” በማለት ጠርቷታል። በመሆኑም እጅግ ብዙ ሕዝብ በአምላክ ዙፋን ፊት የቆሙት ምድር ላይ ሆነው ነው። በተጨማሪም ጻድቃን በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ የሚናገረውን መዝሙር 37:29⁠ን አነበብኩ።

 ውሎ አድሮ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማሁ። ቦናቬንቸር እኔንና ስኮላስቲክን ያስጠናን ጀመር። መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናን ስንሄድ በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ለማድረግ ተነሳሳሁ። ሚስቴን በአክብሮት መያዝ ጀመርኩ። እንደ ቀድሞው ስታነጋግረኝ ወይም አንድ ነገር ልትጠይቀኝ ስትፈልግ እንድትንበረከክ መጠበቅ አቆምኩ። እንዲሁም የቤተሰባችን ንብረት በሙሉ የግል ንብረቴ እንደሆነ መናገር ተውኩ። ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን ፊልሞች ማየትም አቆምኩ። እነዚህን ለውጦች ማድረግ ከባድ ነበር፤ ራሴን መግዛትና ትሑት መሆን ጠይቆብኛል።

መጽሐፍ ቅዱስ የተሻልኩ ባል እንድሆን ረድቶኛል

 ከጥቂት ዓመታት በፊት የመጀመሪያ ልጃችንን ክርስቲያንን ከዘመዶቻችን ጋር እንዲኖር ወደ ኡጋንዳ ልከነው ነበር። ዘዳግም 6:4-7⁠ን ካነበብኩ በኋላ ግን አምላክ እኔና ባለቤቴ ልጆቻችንን እንድንንከባከብና የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች እንድናስተምራቸው እንደሚጠብቅብን ተገነዘብኩ። ልጃችን ወደ ቤት ሲመለስ እኛም ሆንን እሱ በጣም ተደሰትን!

ያገኘሁት ጥቅም

 ይሖዋ መሐሪ አምላክ እንደሆነ ተምሬያለሁ፤ ስለዚህ ለቀድሞው ባሕርዬ እና ድርጊቴ ሁሉ ይቅር እንዳለኝ እተማመናለሁ። ስኮላስቲክ አብራኝ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናቷ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሁለታችንም ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ታኅሣሥ 4, 2010 ተጠመቅን። አሁን እርስ በርስ እንተማመናለን፤ በቤተሰባችን ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ያስደስተናል። ከሥራ ቀጥታ ወደ ቤት ስለምገባ ባለቤቴ በጣም ደስተኛ ነች። በአክብሮት እይዛታለሁ፣ አልኮል ላለመጠጣት ወስኛለሁ፣ እንዲሁም አሁን ጨካኝ ሰው አይደለሁም፤ በዚህም በጣም ተደስታለች። በ2015 ለጉባኤው እረኛ እንድሆን የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ ተሾምኩ። ከአምስቱ ልጆቻችን መካከል ሦስቱ ተጠምቀዋል።

 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ስጀምር የተማርኩትን ነገር በጭፍን አልተቀበልኩም። መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው ለጥያቄዎቼ መልስ ስለሰጡኝ በጣም ተገርሜያለሁ። እኔና ስኮላስቲክ እውነተኛውን አምላክ የሚያገለግሉ ሰዎች የአምላክን መሥፈርቶች ከማለሳለስ ይልቅ በመሥፈርቶቹ መሠረት መኖር እንዳለባቸው ተገንዝበናል። ይሖዋ ስለሳበኝና የመንፈሳዊ ቤተሰቡ አባል ስላደረገኝ በጣም አመሰግነዋለሁ። ስለ ሕይወቴ መለስ ብዬ ሳስብ ቅን ልብ ያለው የትኛውም ሰው በአምላክ እርዳታ አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግና አምላክን ማስደሰት እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ።