በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ጽዮናውያን ናቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች ጽዮናውያን ናቸው?

 አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያኖች ናቸው፤ እምነታቸው የተመሠረተውም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ነው። አንዳንድ ሃይማኖቶች አይሁዳውያን የቀድሞ መኖሪያቸው ወደሆነው ወደ ፓለስቲና ምድር መሰባሰባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ ቢያስተምሩም የይሖዋ ምሥክሮች ይህን አመለካከት አይጋሩም። ይህ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኝ ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ አያምኑም። እንዲያውም ቅዱሳን መጻሕፍት የትኛውንም ሰብዓዊ መንግሥት ደግፈው አይናገሩም፤ እንዲሁም አንድን ዘር ወይም ብሔር ከሌላው አያስበልጡም። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁት መጠበቂያ ግንብ መጽሔት በአንድ ወቅት እንዲህ በማለት በግልጽና በማያሻማ መንገድ ተናግሯል፦ “ለፖለቲካዊ ጽዮናዊነት ምንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ማቅረብ አይቻልም።”

 ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ጽዮናዊነት “በፓለስቲና ውስጥ የአይሁድ መንግሥት ማቋቋምንና ይህን መንግሥት መደገፍን ዓላማ ያደረገ የአይሁዳውያን ብሔራዊ ንቅናቄ” እንደሆነ ተናግሯል። ለጽዮናዊነት መጠንሰስ ምክንያት የሆነው ነገር ሃይማኖትና ፖለቲካ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ጽዮናዊነት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደሆነ አድርገው አይናገሩም፤ እንዲሁም ከፖለቲካዊ ጽዮናዊነት ፍጹም ገለልተኛ ናቸው።

 የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ሙሉ በሙሉ ሃይማኖታዊ ሲሆን ጽዮናዊነትን ጨምሮ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አያራምድም። የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ መሆናቸውን ታሪክ በግልጽ ያሳያል፤ እንዲያውም የይሖዋ ምሥክሮች የገለልተኛ አቋማቸውን ለድርድር ለማቅረብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ለከፍተኛ ስደት ተዳርገዋል። በተጨማሪም በምድር ላይ ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የሚችለው በሰማይ የሚገኘው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነና የትኛውም ሰብዓዊ መንግሥት ወይም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ይህን ማድረግ እንደማይችል እናምናለን።

 የይሖዋ ምሥክሮች የትም ይኑሩ የት ሰብዓዊ መንግሥታት ለሚያወጡት ሕግ መገዛት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ፤ ይህ ከሚመሩባቸው ዓቢይ መመሪያዎች አንዱ ነው። በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ አያምፁም፤ እንዲሁም በትጥቅ ትግል አይሳተፉም።