በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኢየሱስ የሞተው በመስቀል ላይ ነው?

ኢየሱስ የሞተው በመስቀል ላይ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በርካታ ሰዎች መስቀል ዋነኛው የክርስትና መለያ ምልክት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተገደለበትን እንጨት ቅርጽ አይገልጽም፤ ስለሆነም ማንም ሰው ኢየሱስ በምን ዓይነት እንጨት ላይ እንደተሰቀለ በእርግጠኝነት ማወቅ አይችልም። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ የሞተው በመስቀል ላይ ሳይሆን ቀጥ ባለ እንጨት ላይ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ ይዟል።

 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የሞተበትን እንጨት ለማመልከት አብዛኛውን ጊዜ ስታውሮስ የሚለውን ግሪክኛ ቃል ይጠቀማል። (ማቴዎስ 27:40፤ ዮሐንስ 19:17) የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ቃል “መስቀል” ብለው ቢተረጉሙትም በርካታ ምሁራን ቃሉ “ቀጥ ያለ እንጨት” a የሚል ፍቺ እንዳለው ይስማማሉ። ኤ ክሪቲካል ሌክሲከን ኤንድ ኮንኮርዳንስ ቱ ዚ ኢንግሊሽ ኤንድ ግሪክ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንደተናገረው ከሆነ ስታውሮስ የሚለው ቃል “በየትኛውም አቅጣጫ የተነባበሩ ሁለት እንጨቶችን ፈጽሞ ሊያመለክት አይችልም።”

 መጽሐፍ ቅዱስ ዛይሎን የተባለውን ከስታውሮስ ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ያለውን የግሪክኛ ቃልም ይጠቀማል። (የሐዋርያት ሥራ 5:30፤ 1 ጴጥሮስ 2:24) ይህ ቃል “እንጨት፣” “አጠና” ወይም “ዛፍ” የሚል ፍቺ አለው። b ዘ ከምፓንየን ባይብል “በግሪክኛ በተጻፈው [አዲስ ኪዳን] ውስጥ ሁለት እንጨቶችን የሚያመለክት ምንም ዓይነት ሐሳብ አይገኝም” ይላል።

መስቀልን ለአምልኮ መጠቀም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለው?

ክሩክስ ሲምፕሌክስ​—ወንጀለኛን ለመቅጣት የሚያገለግል ወጥ እንጨት የሚጠራበት የላቲን ስም

 ኢየሱስ የተሰቀለበት እንጨት ቅርጹ ምንም ይሁን ምን የሚከተሉት ነጥቦችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መስቀልን ለአምልኮ መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያሉ።

  1.   አምላክ መስቀልን ጨምሮ ሥዕሎችንና ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን ያወግዛል። እስራኤላውያን ‘በማንኛውም ዓይነት ምስል የተቀረጸ’ ነገር ለአምልኮ ሊጠቀሙ እንደማይገባ አምላክ ነግሯቸው ነበር፤ ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ ‘ከጣዖት አምልኮ እንዲሸሹ’ ታዝዘዋል።​—ዘዳግም 4:15-19፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14

  2.   የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መስቀልን ለአምልኮ አልተጠቀሙበትም። c ሐዋርያት ያስተማሩትን ትምህርትና የተዉትን ምሳሌ ሁሉም ክርስቲያኖች ሊከተሉት ይገባል።​—2 ተሰሎንቄ 2:15

  3.   መስቀልን ለአምልኮ መጠቀም የአረማውያን ልማድ ነው። d ኢየሱስ ከሞተ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ አብያተ ክርስቲያናት ከእሱ ትምህርት ማፈንገጥ ጀመሩ፤ በዚህ ወቅት አዳዲስ ምዕመናን “አረማዊ እያሉ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ምልክቶችንና ምስሎችን እንዲያስወግዱ አይጠበቅባቸውም ነበር።” ይህ ደግሞ መስቀልንም ይጨምራል። (ዚ ኤክስፓንድድ ቫይንስ ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አረማዊ ምልክቶችን መጠቀምን ያወግዛል፤ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን ለማፍራት ተብሎም እንኳ እነዚህ ነገሮች ጥቅም ላይ እንዲውሉ መፍቀድ ተቀባይነት የለውም።​—2 ቆሮንቶስ 6:17

a የሚከተሉትን ጽሑፎች ተመልከት፦ New Bible Dictionary, Third Edition, edited by D. R. W. Wood, page 245; Theological Dictionary of the New Testament, Volume VII, page 572; The International Standard Bible Encyclopedia, Revised Edition, Volume 1, page 825; and The Imperial Bible-Dictionary, Volume II, page 84

b የሚከተሉትን ጽሑፎች ተመልከት፦ The Expanded Vine’s Expository Dictionary of New Testament Words, page 1165; A Greek-English Lexicon, by Liddell and Scott, Ninth Edition, pages 1191-​1192; and Theological Dictionary of the New Testament, Volume V, page 37

c የሚከተሉትን ጽሑፎች ተመልከት፦ Encyclopædia Britannica, 2003, entry “Cross”; The Cross​—Its History and Symbolism, page 40; and The Companion Bible, Oxford University Press, appendix 162, page 186

d የሚከተሉትን ጽሑፎች ተመልከት፦ The Encyclopedia of Religion, Volume 4, page 165; The Encyclopedia Americana, Volume 8, page 246; and Symbols Around Us, pages 205-​207