በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ አስከሬን ስለ ማቃጠል ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ አስከሬን ስለ ማቃጠል ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ አስከሬን ማቃጠልን በተመለከተ ቀጥተኛ መመሪያ አይሰጥም። አስከሬን መቅበርንም ሆነ ማቃጠልን አስመልክቶ የተሰጠ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ የለም።

 መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የሞቱ ሰዎችን እንደቀበሩ የሚናገሩ ዘገባዎችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም ለሚስቱ ለሣራ የመቃብር ቦታ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ነበር።—ዘፍጥረት 23:2-20፤ 49:29-32

 መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የሞቱ ሰዎችን እንዳቃጠሉ የሚናገሩ ዘገባዎችንም ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦልና ሦስት ልጆቹ ጦር ሜዳ ላይ ተገድለው አስከሬናቸው በጠላት ክልል ውስጥ ወድቆ ነበር፤ ከዚያም የጠላት ወታደሮች የእነዚህን ሰዎች አስከሬን ወስደው ግንብ ላይ ሰቀሉት። ሆኖም ታማኝ የሆኑ እስራኤላውያን ወታደሮች ይህን ሲሰሙ የሳኦልንና የልጆቹን አስከሬን ወስደው ካቃጠሉት በኋላ አፅማቸውን ቀበሩት። (1 ሳሙኤል 31:8-13) መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ እስራኤላውያን በሳኦልና በልጆቹ አስከሬን ላይ ያደረጉት ነገር ተቀባይነት ያለው እንደነበረ ይጠቁማል።—2 ሳሙኤል 2:4-6

ብዙዎች አስከሬን ማቃጠልን በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 የተሳሳተ አመለካከት፦ አስከሬንን ማቃጠል ለሟቹ አካል አክብሮት አለማሳየት ነው።

 እውነታው፦ መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ወደ አፈር እንደሚመለሱ ይናገራል፤ የሰው አስከሬን ሲበሰብስ ወደ አፈርነት መቀየሩ አይቀርም። (ዘፍጥረት 3:19) ስለዚህ የአስከሬኑ መቃጠል አስከሬኑን ወደ አመድ ወይም ወደ አፈር የመለወጥ ሂደቱን ከማፋጠን ውጪ የሚያመጣው ለውጥ የለም።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ በጥንት ዘመን አስከሬናቸው የሚቃጠለው የአምላክን ሞገስ ያጡ ሰዎች ብቻ ነበሩ።

 እውነታው፦ አካንንና ቤተሰቡን ጨምሮ ታማኝ ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች አስከሬን እንዲቃጠል ተደርጎ ነበር። (ኢያሱ 7:25) ሆኖም ይህ የሚደረገው ሁልጊዜ አልነበረም። (ዘዳግም 21:22, 23) ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የንጉሥ ሳኦል ልጅ የሆነውን የዮናታንን ጨምሮ የአንዳንድ ታማኝ ሰዎች አስከሬንም ተቃጥሎ ነበር።

 የተሳሳተ አመለካከት፦ አስከሬኑ ከተቃጠለ አምላክ ግለሰቡን ከሞት ሊያስነሳው አይችልም።

 እውነታው፦ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ቢቀበር፣ ቢቃጠል፣ ባሕር ውስጥ ቢሰምጥ አሊያም የዱር አውሬ ቢበላው አምላክ ግለሰቡን በትንሣኤ እንዳያስነሳው እንቅፋት አይሆንበትም። (ራእይ 20:13) ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ለግለሰቡ አዲስ አካል ሰጥቶ ማስነሳት ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:35, 38