በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ሮም 6:23—“የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን . . . የዘላለም ሕይወት ነው”

ሮም 6:23—“የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን . . . የዘላለም ሕይወት ነው”

 “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነውና፤ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።”—ሮም 6:23 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።”—ሮም 6:23 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የሮም 6:23 ትርጉም

 ሐዋርያው ጳውሎስ በእነዚህ ቃላት አማካኝነት የሰው ልጆች የሚሞቱት ኃጢአተኛ ስለሆኑ እንደሆነ ገልጿል። ሆኖም አምላክ ለታማኝ አገልጋዮቹ አስደናቂ ተስፋ ይኸውም የዘላለም ሕይወት ስጦታ አዘጋጅቷል።

 “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው።” ሁሉም ሰዎች ሲወለዱ ጀምሮ ፍጹማን ስላልሆኑ ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ አላቸው። a (መዝሙር 51:5፤ መክብብ 7:20) ሁሉም ሰዎች ኃጢአተኛ ስለሆኑ ውሎ አድሮ ማርጀታቸውና መሞታቸው አይቀርም።—ሮም 5:12

 ጳውሎስ ይህን ሐሳብ በምሳሌ ለማስረዳት ኃጢአትን ደሞዝ ከሚከፍል ጌታ ጋር አመሳስሎታል። አንድ ሠራተኛ ለሥራው ደሞዝ እንደሚጠብቅ ሁሉ ሰዎችም ፍጹማን ስላልሆኑ እንደሚሞቱ መጠበቅ ይችላሉ።

 ይሁንና ጳውሎስ “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል” በማለትም ተናግሯል። (ሮም 6:7) አንድ ሰው ሲሞት፣ ከፈጸማቸው ኃጢአቶች ሁሉ ነፃ ይወጣል። በመሆኑም ሙታን ቀደም ሲል በፈጸሙት ኃጢአት የተነሳ ይሠቃያሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሙታን ምንም ዓይነት ነገር እንደማያስቡ፣ እንደማያደርጉ እንዲሁም እንደማይሰማቸው በግልጽ ይናገራል።—መክብብ 9:5

 “አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።” ኃጢአት ከሚከፍለው “ደሞዝ” በተቃራኒ አምላክ የዘላለም ሕይወት ስጦታ እንደሚሰጠን ቃል ገብቷል። “ስጦታ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “የጸጋ ስጦታ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ይህ ቃል ተቀባዩ ‘ይገባኛል’ ወይም ‘የልፋቴ ዋጋ ነው’ ሊለው የማይችለውን ስጦታ ያመለክታል። ኃጢአተኛ የሆነ ሰው በራሱ ጥረት መዳን ወይም የዘላለም ሕይወት ሊያገኝ አይችልም። (መዝሙር 49:7, 8) ይሁንና አምላክ በኢየሱስ ለሚያምኑ ሰዎች ውድ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ስጦታ በነፃ ይሰጣቸዋል።—ዮሐንስ 3:16፤ ሮም 5:15, 18

የሮም 6:23 አውድ

 ጳውሎስ በሮም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ይህን ደብዳቤ የጻፈው በ56 ዓ.ም. ገደማ ነው። በዘመኑ ከነበሩት ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ ስለ አምላክ ምሕረት የተሳሳተ አመለካከት የነበራቸው ይመስላል። የግሪክ ፍልስፍና ባሳደረባቸው ተጽዕኖ የተነሳ፣ ብዙ ኃጢአት በሠሩ መጠን የአምላክ ይቅርታ ይበልጥ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው አስበው ሊሆን ይችላል። (ሮም 6:1) ሌሎች ደግሞ በሙሴ ሕግ ሥር ስላልሆኑ ለሚፈጽሙት ስህተት ተጠያቂ እንደማይሆኑ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። (ሮም 6:15) ጳውሎስ በደብዳቤው ላይ፣ ክርስቲያኖች ኃጢአት ሕይወታቸውን እንዲቆጣጠረው ከፈቀዱ ከአምላክ ምሕረት ተጠቃሚ እንደማይሆኑ ጎላ አድርጎ ገልጿል።—ሮም 6:12-14, 16

 ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ፣ በዘመናችን ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ሲወለዱ ጀምሮ ኃጢአተኛ ቢሆኑም እንኳ ተስፋ እንዳላቸው ዋስትና ይሰጣቸዋል። አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚያከብሩና ለመጥፎ ምኞቶቻቸው እጅ የማይሰጡ ከሆነ አምላክ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል።—ሮም 6:22

 የሮም መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a “ኃጢአት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር የሚጋጭን ማንኛውም ድርጊት ወይም ዝንባሌ ለማመልከት ነው። (1 ዮሐንስ 3:4) “ኃጢአት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።