በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ራእይ 21:4—“እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል”

ራእይ 21:4—“እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል”

 “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:4 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”—ራእይ 21:4 የ1954 ትርጉም

የራእይ 21:4 ትርጉም

 አምላክ በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆችን ለሐዘን እየዳረገ ያለውን ሥቃይና መከራ ብቻ ሳይሆን የእነዚህን ችግሮች መንስኤም እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል።

 “እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።” እነዚህ ቃላት ይሖዋ a ‘ከፊት ሁሉ እንባን እንደሚያብስ’ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት የሰጠውን ተስፋ ያረጋግጣሉ። (ኢሳይያስ 25:8፤ ራእይ 7:17) ይህ አገላለጽ አምላክ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣትን ጨምሮ ለሥቃይ በሚዳርጉ የተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ለሚያለቅሱ ሰዎች ያለውን አሳቢነት ያሳያል።

 “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም።” ይህ አገላለጽ “ሞት ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” ወይም “ከአሁን በኋላ ሞት የሚባል ነገር አይኖርም” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። አምላክ ሞትንም ሆነ የምንወደውን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትልብንን ሥቃይ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል። የሞቱ ሰዎችም በትንሣኤ ይነሳሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:21, 22) በዚህ መንገድ “ሞት ይደመሰሳል።”—1 ቆሮንቶስ 15:26

 “ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” አምላክ ማንኛውም ዓይነት ሥቃይ እንደማይሰማን፣ ሌላው ቀርቶ አደጋ ወይም ጉዳት ሊያስከትል ከሚችል ነገር እንድንርቅ የሚያስጠነቅቀን ተፈጥሯዊ የሥቃይ ስሜት ጭምር እንደሚጠፋ መናገሩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህ ተስፋ በኃጢአት b እና በአለፍጽምና ምክንያት የሚመጣ ማንኛውም ዓይነት አእምሯዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ ሥቃይ እንደሚወገድ የሚጠቁም ነው።—ሮም 8:21, 22

 “ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” ይህ የመደምደሚያ ሐሳብ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ የሚታየውን አስደናቂ ለውጥ ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ከሞት፣ ከእንባ፣ ከለቅሶና ከሥቃይ ማምለጥ የማይቻልበት ቀድሞ የነበረው የሰው ልጅ ሕይወት በአዲስ ዓይነት አኗኗር ይተካል።” ያኔ የሰው ልጆች በአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ መሠረት በተመቻቹ ሁኔታዎች ሥር በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ መኖር ይችላሉ።—ዘፍጥረት 1:27, 28

የራእይ 21:4 አውድ

 በምዕራፍ 21 መጀመሪያ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ያየውን ነገር ሲገልጽ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ” ብሏል። (ራእይ 21:1) ዮሐንስ ወደፊት የሚኖረውን ሥር ነቀል ለውጥ ለመግለጽ ምሳሌያዊ አነጋገር ተጠቅሟል፤ ይህ ለውጥ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችም ላይ ተጠቅሶ ይገኛል። (ኢሳይያስ 65:17፤ 66:22፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ማለትም ‘አዲሱ ሰማይ’ ሰብዓዊ አገዛዞችን በሙሉ በመተካት ‘አዲሱን ምድር’ ማለትም በምድር ላይ የሚኖረውን አዲስ የሰው ዘር ማኅበረሰብ ያስተዳድራል።—ኢሳይያስ 65:21-23

 ይህ ራእይ በምድር ላይ ስለሚኖረው ሕይወት እየተናገረ እንዳለ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ አምላክ የሰጠው ይህ ተስፋ የሚጀምረው “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው” በሚሉት ቃላት ነው። (ራእይ 21:3) በመሆኑም ተስፋው የተሰጠው በሰማይ ላሉ መላእክት ሳይሆን በምድር ላይ ለሚኖሩ የሰው ልጆች ነው። ሁለተኛ፣ ራእዩ ‘ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ስለማይኖርበት’ ዓለም ይናገራል። (ራእይ 21:4) በሰማይ ሞት ኖሮ አያውቅም፤ ሞት የሚያጠቃው በምድር ላይ ያሉ ሰዎችን ብቻ ነው። (ሮም 5:14) በመሆኑም ይህ ጥቅስ ወደፊት በምድር ላይ የሚኖረውን ሁኔታ የሚገልጽ ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይሆናል።

 የራእይ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ኃጢአት ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር የሚጋጭን ድርጊት፣ ስሜት ወይም አስተሳሰብ ያመለክታል፤ ተገቢ የሆነውን ነገር ሳያደርጉ መቅረትም ኃጢአት ሊባል ይችላል። (1 ዮሐንስ 3:4) “ኃጢአት ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።