በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጆቻችሁን አመስጋኝ እንዲሆኑ አስተምሯቸው

ልጆቻችሁን አመስጋኝ እንዲሆኑ አስተምሯቸው

 ጥናቶች እንደሚያሳዩት አመስጋኝ የሆኑ ሰዎች ይበልጥ ደስተኛና ጤናማ ናቸው፤ ችግሮችን የመቋቋም አቅማቸው የተሻለ ነው፤ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ጥሩ ወዳጅነት አላቸው። ሮበርት ኤመንስ የተባሉ ተመራማሪ እንደተናገሩት አመስጋኝነት “አንድ ሰው እንደ ምቀኝነት፣ ጥላቻ፣ ስግብግብነትና ምሬት ያሉ ጎጂ ባሕርያት እንዳይኖሩት ያደርጋል።” a

 ታዲያ ልጆች አመስጋኝ መሆናቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? በ700 ልጆች ላይ ለአራት ዓመት የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው አመስጋኝ የሆኑ ልጆች በአመዛኙ ሲታይ ፈተና ላይ አይኮርጁም፤ ዕፅና አልኮል መጠጥ አይጠቀሙም ወይም የባሕርይ ችግር የለባቸውም።

  •   ይገባኛል የሚለው አመለካከት አመስጋኝነትን ያጠፋል። ብዙ ልጆች ጥሩ ነገር ሲደረግላቸው ይገባኛል የሚል ስሜት አላቸው። ያገኙትን ጥሩ ነገር እንደ ስጦታ ሳይሆን እንደ ደሞዝ አድርገው ከተመለከቱት ደግሞ ለማመስገን አይነሳሱም።

     እንዲህ ያለው አመለካከት በዛሬው ጊዜ በጣም የተለመደ ነው። ካትሪን የተባለች እናት ያስተዋለችውን ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ዓለማችን፣ ይገባኛል የሚለው መንፈስ የሚሰበክበት ትምህርት ቤት ነው። ሚድያው የሚያማልሉ ምስሎችን ያዥጎደጉድብንና ‘ይሄማ ይገባሃል’ ወይም ‘ማንም እንዳይቀድምህ’ ይለናል።”

  •   ገና በለጋ ዕድሜ አመስጋኝነትን ማስተማር ይቻላል። ኬይ የተባለች እናት እንዲህ ብላለች፦ “ልጆች ነጭ ወረቀት ናቸው። ገና በለጋነታቸው ጥሩ ልማዶችን ካስተማርናቸው ያንኑ ይዘው ያድጋሉ፤ አንድ ችግኝ ተቃንቶ እንዲያድግ እንጨት እንደምንጠቀመው ማለት ነው።”

አመስጋኝነትን ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?

  •   አመስጋኝነታቸውን በንግግር እንዲገልጹ አስተምሯቸው። ሕፃናትም እንኳ ሥልጠናው ከተሰጣቸው፣ አንድ ሰው ስጦታ ሲሰጣቸው ወይም አንድ ነገር ሲያደርግላቸው ‘አመሰግናለሁ’ ማለትን ይማራሉ። እያደጉና ከፍ እያሉ ሲሄዱ ደግሞ ሌሎች ለሚያደርጉላቸው መልካም ነገር ያላቸው አድናቆት እያደገ ይሄዳል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ።”—ቆላስይስ 3:15

     “የልጅ ልጃችን ገና ሦስት ዓመቱ ቢሆንም ሁልጊዜ ‘አመሰግናለሁ’ ይላል፤ አንድ ነገር ሲጠይቅም ‘እባክህ’ ብሎ ነው የሚጀምረው። ይህን የተማረው ከወላጆቹ ነው። እነሱ በተግባራቸውም ሆነ በንግግራቸው አመስጋኝ መሆናቸው ለእሱም አመስጋኝነትን እያስተማረው ነው።”—ጄፍሪ

  •   አመስጋኝነታቸውን በተግባር እንዲገልጹ አስተምሯቸው። በቀጣዩ ጊዜ ልጆቻችሁ ስጦታ ሲሰጣቸው የምስጋና ደብዳቤ እንዲጽፉ አስተምሯቸው። ከዚህም በተጨማሪ ለልጆቻችሁ የቤት ውስጥ ሥራ ስጧቸው፤ ይህም የቤት አያያዝ ምን ያህል ልፋት እንደሚጠይቅ እንዲረዱ ያስችላቸዋል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

     “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙት ሁለት ልጆቻችን ምግብ በማዘጋጀት፣ በማብሰልና ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎች በመሥራት ያግዙናል። ይህን ሲያደርጉ፣ ወላጅ መሆን ምን ያህል ድካም እንደሚጠይቅ መረዳት ችለዋል፤ ለሚደረግላቸው ነገርም ይበልጥ አመስጋኝ ናቸው።”—ቤቨርሊ

  •   የአመስጋኝነት አመለካከት እንዲኖራቸው አስተምሯቸው። አመስጋኝነት፣ የትሕትና አፈር የሚያሳድገው ችግኝ ነው ማለት ይቻላል። ትሑት ሰዎች ለስኬታቸው የሌሎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አምነው ይቀበላሉ፤ ይህም ለሚደረግላቸው ድጋፍ አመስጋኝ እንዲሆኑ ያነሳሳቸዋል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ፤ . . . ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:3, 4

     “አንዳንዴ ማታ ራት ስንበላ የምንጫወተው ጌም አለ። እያንዳንዱ ሰው ተራው ሲደርስ አመስጋኝ የሆነበትን አንድ ነገር ይጠቅሳል። በዚህ ጊዜ የሁላችንም ትኩረት የሚያርፈው አዎንታዊ በሆኑና አመስጋኝ እንድንሆን በሚያደርጉ ሐሳቦች ላይ ይሆናል፤ አሉታዊ የሆኑና በራሳችን ጥቅም ላይ ያተኮሩ ሐሳቦች ቦታ አይኖራቸውም።”—ታማራ

 ጠቃሚ ምክር፦ ምሳሌ ሁኑ። ልጆች፣ እናንተ ራሳችሁ አዘውትራችሁ ሌሎችንም ሆነ እነሱን ስታመሰግኑ የሚሰሟችሁ ከሆነ አመስጋኝነትን መማር ይበልጥ ቀላል ይሆንላቸዋል።

a ታንክስ! ሀው ፕራክቲሲንግ ግራቲትዩድ ካን ሜክ ዩ ሀፒየር ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።