በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጆችን ትሕትና ማስተማር

ልጆችን ትሕትና ማስተማር

ተፈታታኙ ነገር

  • ልጃችሁ ትዕቢተኛ እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ነገሮችን ያደርጋል፤ የሚገርመው ገና አሥር ዓመቱ ነው!

  • ሁሉም ሰው ልዩ እንክብካቤ እንዲያደርግለት ይጠብቃል።

‘እንዲህ ያለ ጠባይ ያመጣው ከየት ነው? እኔ የምፈልገው ስለ ራሱ ጥሩ አመለካከት እንዲኖረው እንጂ ራሱን ከሌሎች የተሻለ አድርጎ እንዲመለከት አይደለም!’ ብላችሁ ታስባላችሁ።

ልጃችሁ ለራሱ ያለው ግምት ሳይቀንስ ትሕትናን እንዲማር መርዳት የምትችሉበት መንገድ ይኖር ይሆን?

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ፣ ወላጆች ልጆቻቸው የሚፈልጉትን ሁሉ እንዲያደርጉላቸው፣ ምንም የሚያስመሰግን ነገር ባይሠሩም እንኳ አብዝተው እንዲያመሰግኗቸው እንዲሁም ለልጆቻቸው እርማትና ተግሣጽ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ሲመከሩ ቆይተዋል። ልጆች ልዩ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ተደርገው ካደጉ ለራሳቸው ጥሩ ግምት ይኖራቸዋል ተብሎ ይታሰብ ነበር። ሆኖም የተገኘው ውጤት ምን ያሳያል? ጀነሬሽን ሚ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ልጆች ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው አድርጎ ለማሳደግ የተደረገው ጥረት፣ የታረመ ጠባይ ያላቸውና ደስተኛ ልጆችን ከማፍራት ይልቅ ከራስ በላይ ንፋስ የሚል አመለካከት ያለው ትውልድ አስገኝቷል።”

ያለምንም ምክንያት ውዳሴ እየተቸራቸው ያደጉ ልጆች አዋቂ በሚሆኑበት ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን መወጣት እንዲሁም ትችትንና ሽንፈትን በጸጋ መቀበል ይከብዳቸዋል። በራሳቸው ፍላጎት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ተደርገው ስላደጉ ትልቅ ሲሆኑ ከሌሎች ሰዎች ጋር ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት መመሥረት ያስቸግራቸዋል። በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ ደስታ የሚርቃቸው ከመሆኑም ሌላ ለመንፈስ ጭንቀት ይዳረጋሉ።

ልጆች ለራሳቸው ትክክለኛ ግምት እንዲኖራቸው አድርጎ ማሳደግ የሚቻለው ልዩ እንደሆኑ በተደጋጋሚ በመንገር ሳይሆን በሕይወታቸው ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን ማከናወን እንዲችሉ በመርዳት ነው። ይህ ደግሞ ልጆቻችሁ እንዲሁ በራሳቸው ብቃት እንዲተማመኑ ከማድረግ ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። ልጆቻችሁ አንድን ክህሎት መማር፣ መለማመድና ይበልጥ እያሻሻሉ መሄድ ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 22:29) በተጨማሪም ሌሎች ሰዎች ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ማሰብ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:24) ይህ ሁሉ ትሕትና ይጠይቃል።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

የሚያስመሰግን ነገር በሚያደርጉበት ጊዜ ብቻ አመስግኗቸው። ልጃችሁ በትምህርት ቤት ፈተና ጥሩ ውጤት ካመጣች ልታመሰግኗት ይገባል። ዝቅተኛ ውጤት ካመጣች ደግሞ ጥፋቱ የመምህሩ እንደሆነ ለመናገር አትቸኩሉ። ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችሁ ልጃችሁ ትሕትና እንድትማር አይረዳትም። በመሆኑም በሚቀጥለው ጊዜ እንዴት ማሻሻል እንደምትችል ንገሯት። ልጆቻችሁ በእርግጥ የሚያስመሰግን ነገር ሲያከናውኑ ብቻ አመስግኗቸው።

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እርማት ስጧቸው። ይህ ሲባል ልጃችሁ የሚሠራውን እያንዳንዱን ስህተት ማረም አለባችሁ ማለት አይደለም። (ቆላስይስ 3:21) ከባድ ስህተቶችን ግን ማረም አስፈላጊ ነው። የተሳሳቱ ዝንባሌዎችንም ማስተካከል ያስፈልጋል። አለዚያ እነዚህ ዝንባሌዎች በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ሥር እየሰደዱ ሊሄዱ ይችላሉ።

ለምሳሌ ልጃችሁ የጉረኝነት አዝማሚያ ይታይበታል እንበል። ይህ ዝንባሌው ካልታረመ ልጁ ራሱን ከፍ አድርጎ መመልከትና ሌሎችን ማግለል ሊጀምር ይችላል። ስለዚህ ጉረኛ መሆን ሰዎች ለእሱ መጥፎ አመለካከት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግና ውሎ አድሮም ለኀፍረት ሊዳርገው እንደሚችል አስረዱት። (ምሳሌ 27:2) በተጨማሪም ስለ ራሱ ትክክለኛ አመለካከት ያለው ሰው ችሎታውን ለሌሎች ማወጅ እንደማያስፈልገው ግለጹለት። ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንፈስ እንዲህ ያለ እርማት መስጠታችሁ ልጁ ለራሱ ያለው አክብሮት ሳይጠፋ ትሕትናን እንዲማር ያስችለዋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ማቴዎስ 23:12

ልጆቻችሁን ወደፊት ለሚያጋጥማቸው የኑሮ ውጣ ውረድ አዘጋጇቸው። ልጃችሁ የጠየቀውን ሁሉ የምታደርጉለት ከሆነ ሊሞላቀቅ ይችላል። ለምሳሌ ልጃችሁ አቅማችሁ የማይፈቅድላችሁን ነገር እንድታደርጉለት ከጠየቃችሁ እንደ አቅም መኖር አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት አስረዱት። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሽርሽር ለመሄድ ወይም ዘና ለማለት የያዛችሁትን ፕሮግራም መሰረዝ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል፤ በዚህ ጊዜ በሕይወት ውስጥ ሁሉ ነገር እንዳሰቡት እንደማይሆንና ያሰባችሁት ነገር ሳይሳካ ሲቀር የሚሰማችሁን ሐዘን ለመቋቋም እናንተ ምን እንደምታደርጉ አስረዱት። ልጃችሁ ምንም ዓይነት ችግር እንዳያገኘው ከመከላከል ይልቅ ትልቅ ሰው ሲሆን ለሚያጋጥሙት አስቸጋሪ ሁኔታዎች አዘጋጁት።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 29:21

ለጋስ እንዲሆኑ አበረታቷቸው። ልጃችሁ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ” እንደሚያስገኝ እንዲመለከት አድርጉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ዕቃ በመግዛት፣ በመጓጓዣ ወይም በጥገና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ዝርዝር ከልጃችሁ ጋር አብራችሁ በመሆን አውጡ። ከዚያም እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ስትሄዱ ልጃችሁን ይዛችሁት ሂዱ። ልጃችሁ ሌሎችን በምትረዱበት ጊዜ እናንተ የምታገኙትን ደስታና እርካታ እንዲያይ አድርጉ። ልጃችሁ ትሕትናን እንዲማር የምትረዱበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ራሳችሁ ምሳሌ በመሆን ማስተማር ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ሉቃስ 6:38