በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | ትዳር

ቅናት ትዳራችሁን እንዳይበጠብጠው ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ቅናት ትዳራችሁን እንዳይበጠብጠው ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

 ጥርጣሬና አለመተማመን የሰፈነበት ትዳር አይሰምርም። ታዲያ አግባብነት የሌለው ቅናት ትዳራችሁን እንዳይበጠብጠው ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 ቅናት ምንድን ነው?

 “ቅናት” የሚለው ቃል እንደየአገባቡ የተለያየ ፍቺ ሊኖረው ይችላል። በዚህ ርዕስ ላይ ግን የተሠራበት አንድ ሰው የትዳር ጓደኛችንን እንደከጀላት ወይም የትዳር ጓደኛችን ሌላን ሰው እንደከጀለች ሲሰማን የሚፈጠርብንን ስሜት ለማመልከት ነው። aትዳራችን አደጋ ላይ እንዳለ ይሰማን ይሆናል። በእርግጥ ሁኔታው እንደዚህ ከሆነ ቅናት ቢያድርብን ተገቢና ተፈጥሯዊ ነው። ደግሞም ከትዳር የጠበቀ ጥምረት ስለሌለ ጥንዶቹ ትዳራቸውን ለመታደግ የሚችሉትን ሁሉ ቢያደርጉ የሚያስገርም አይደለም።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። . . . አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”—ማቴዎስ 19:6

 “ቅናት እንደ እሳት አደጋ ማስጠንቀቂያ ደወል ነው። ትዳራችሁን ስጋት ውስጥ የሚጥል ነገር ካለ ያነቃሃል፤ እርምጃ እንድትወስድም ያደርግሃል።”—ቤንጃሚን

 አግባብነት የሌለው ቅናት ግን መሠረተ ቢስ ከሆነ ጥርጣሬና ስጋት የመነጨ ነው። እውነተኛ ፍቅር ከእንዲህ ዓይነት ጎጂ ቅናት ይጠብቀናል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 7) ዶክተር ሮበርት ሌሂ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “[መሠረተ ቢስ በሆነ ቅናት] ተነሳስተህ የምትወስደው እርምጃ፣ የምትሳሳለትን ጥምረት ጭራሽ አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል።” b

 ተገቢ ያልሆነ ቅናት መንስኤው ምንድን ነው?

 በቀድሞ ትዳርህ ክህደት ተፈጽሞብህ ከነበረ፣ አለምክንያት የመቅናት አባዜ ሊጠናወትህ ይችላል። አሊያም ደግሞ የወላጆችህ ትዳር በእምነት ማጉደል የተነሳ ፈርሶ ሊሆን ይችላል፤ አንተም ይህ ዕጣ እንዳይገጥምህ ትሰጋለህ።

 “ልጅ እያለሁ አባቴ ለእናቴ ታማኝ አልነበረም፤ ስለዚህ ከድሮም ጀምሮ ሰው ማመን በጣም ይቸግረኛል። ይህ ያስከተለው የስሜት ጠባሳ አልፎ አልፎ በትዳሬ ላይ ችግር መፍጠሩ አልቀረም።”—ሜሊሳ

 ሌላው ምክንያት ደግሞ ይሄ ነው፦ በራስ መተማመን የሚጎድልህ ከሆነ ሌሎች ሰዎች የትዳር ጓደኛህን እንደሚቀሙህ ማሰብ ሊቀናህ ይችላል። ይባስ ብሎም የትዳር ጓደኛህ ዕድሉን ብታገኝ አንተን ትታ ሌላ ሰው ጋ እንደምትሄድ ራስህን ልታሳምን ትችላለህ።

 “ባለቤቴ ጓደኛው ሲያገባ ሚዜ እንዲሆን ተጠይቆ ነበር። በሠርጉ ላይ ከሴቷ ሚዜ ጋር የሚጣመርባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ሳስብ ነገሩን መቀበል ከበደኝ። ስለዚህ ሚዜ እንዳይሆን ነገርኩት።”—ናኦሚ

 እርግጥ ነው፣ የሠርግ ልማዶች እንደየአካባቢው ይለያያሉ፤ ደግሞም ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ሲያደርጉ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊመሩ ይገባል። ናኦሚ በዚያ ወቅት ያደረገችው ነገር ምክንያታዊ ነበር? አሁን ላይ ሆና ስታስበው፣ የምትቀናበት ምንም ምክንያት እንዳልነበር ይሰማታል። እንዲህ ብላለች፦ “በወቅቱ ስለ ራሴ ጥሩ ስሜት አልነበረኝም። ባለቤቴ ከሌሎች ሴቶች ጋር የሚያወዳድረኝ ይመስለኝ ነበር፤ ይህ ግን ራሴ የፈጠርኩት ነገር ነበር።”

 መንስኤው ምንም ይሁን ምን መሠረተ ቢስ የሆነ ቅናት፣ የትዳር ጓደኛህን እንድትጠረጥራት ብሎም ያለጥፋቷ በእምነት ማጉደል እንድትወነጅላት ሊያደርግህ ይችላል። ይህ የሚፈጥረው አለመተማመን ደግሞ ትዳርህን፣ ምናልባትም ጤንነትህን እንኳ አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ቅናት እንደ ካንሰር ነው።”—ምሳሌ 14:30 ኢዚ ቱ ሪድ ቨርዥን

 ቅናት ትዳርህን እንዳይበጠብጠው ምን ማድረግ ትችላለህ?

 በትዳር ጓደኛህ ላይ ያለህን እምነት አጠናክር። በትዳር ጓደኛህ ላይ የእምነት ማጉደል አዝማሚያዎችን ለማግኘት አትሞክር፤ ከዚህ ይልቅ ቀደም ሲል እንድታምናት ያደረጉህን ነገሮች አስብ።

 “የባለቤቴን መልካም ባሕርያት ለማሰብ እሞክራለሁ። ለሌላ ሰው ትኩረት ሲሰጥ ባይ፣ ይህን የሚያደርገው ስለ ሌሎች ከልቡ ስለሚጨነቅ እንጂ ሌላ ነገር አስቦ እንዳልሆነ አውቃለሁ። የወላጆቼ ትዳር ማለት የእኔ ትዳር እንዳልሆነ ራሴን ምንጊዜም እነግረዋለሁ።”—ሜሊሳ

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ፍቅር . . . ሁሉን ያምናል።”—1 ቆሮንቶስ 13:4, 7

 ጥርጣሬህን ተጠራጠረው። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዶክተር ሌሂ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ወደ አእምሯችን የሚመጡ ሐሳቦችን፣ እውነት ናቸው ብሎ መቀበል ይቀናናል። ያ ነገር እውነት እንደሆነ ስላመንን ብቻ እውነት ለመሆኑ ማስረጃ እንዳለን ይሰማናል። ይሁን እንጂ አንድን ነገር እውነት ነው ብለን ማመናችን እውነት አያደርገውም፤ የእኛ እርግጠኝነት፣ ማስረጃ መሆን አይችልም።” c

 “ለሁኔታዎች የራሳችንን ትርጉም መስጠትና ‘እንዲህ ነው’ ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ፣ የሌለ ችግር መፍጠር ነው።”—ናዲን

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።”—ፊልጵስዩስ 4:5

 የሚያሳስብህን ነገር ንገራት። ለቅናት መንስኤ የሆነህ ነገር ምንም ይሁን ምን፣ ያሳሰበህን ነገር ለባለቤትህ ንገራት፤ ከዚያም ከሌሎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ረገድ ሁለታችሁም የምትስማሙባቸውን ምክንያታዊ ገደቦች አውጡ።

 “እንዲህ ያለውን ውይይት ስታደርጉ፣ የትዳር ጓደኛችሁ ሊጎዳችሁ እንደማይፈልግ ከዚህ ይልቅ እሱም ለትዳራችሁ የሚጠቅመውን ነገር ለማድረግ እየጣረ እንደሆነ አስቡ። አንዳችሁ የሌላውን ቅንነት አትጠራጠሩ። ምናልባት እናንተ ነገሩን አጋንናችሁ ተመልክታችሁት ወይም ከትዳር ጓደኛችሁ ከልክ በላይ እየጠበቃችሁ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የትዳር ጓደኛችሁ፣ ያጎደለው ነገር እንዳለ አልተሰማው ይሆናል።”—ሲያራ

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።”—1 ቆሮንቶስ 10:24

a ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል ይህ ርዕስ የተዘጋጀው ከባሎች አንጻር ቢሆንም ሐሳቦቹ ለሚስቶችም ይሠራሉ።

b c የቅናት መድኃኒት (The Jealousy Cure) ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።