በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ

ቁጣን መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት ነው?

ቁጣን መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት ነው?

 የትዳር ጓደኛሽ የሚያናድድሽ አንድ ነገር ተናግሮ አሊያም አድርጓል እንበል፤ አንቺ ደግሞ ንዴትሽን አምቀሽ ለመያዝ እየሞከርሽ ነው። ሆኖም የትዳር ጓደኛሽ አንድ ችግር እንዳለ ስለተረዳ ጥያቄዎች ይጠይቅሽ ይሆናል። ይህ ደግሞ የባሰ ያበሳጭሻል። ታዲያ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙሽ ቁጣሽን መቆጣጠር የምትችይው እንዴት ነው?

 ማወቅ የሚኖርብሽ ነገር

  •   በቁጣ መገንፈል ጤናን ይጎዳል። በቁጣ መገንፈል ለከፍተኛ የደም ግፊት፣ ለልብ በሽታ፣ ለመንፈስ ጭንቀት፣ እንዲሁም ለምግብ መፈጨት ችግር ይበልጥ እንደሚያጋልጥ ጥናቶች ያሳያሉ። በተጨማሪም ቁጣ እንቅልፍ ከማጣት፣ ከከፍተኛ ውጥረት፣ ከቆዳ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ችግሮች እንዲሁም በጭንቅላት ውስጥ ደም ከመፍሰስ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይነገራል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “ከቁጣ ተቆጠብ፤ . . . ጉዳት ላይ ሊጥልህ ስለሚችል አትበሳጭ” የሚል ምክር መስጠቱ የሚያስገርም አይደለም።—መዝሙር 37:8 ግርጌ

  •   ቁጣን አምቆ መያዝም ቢሆን ጉዳት ያስከትላል። ቁጣን አምቆ መያዝ ውስጣችንን ከሚጎዳ በሽታ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ተጠራጣሪ ወይም ተቺ እንድትሆኚ ሊያደርግሽ ይችላል። እንዲህ ያለው መንፈስ ደግሞ ትዳራችሁን አስቸጋሪ ሊያደርገው ብሎም ከመሠረቱ ሊያናጋው ይችላል።

 ምን ማድረግ ትችያለሽ?

  •   የትዳር ጓደኛሽ ያሉትን ጥሩ ባሕርያት ለማስተዋል ሞክሪ። የትዳር አጋርሽን እንድታደንቂው የሚያደርጉሽን ሦስት ነገሮች ጻፊ። ከዚያም የትዳር ጓደኛሽ ሲያናድድሽ፣ የጠቀስሻቸው ነገሮችን ለማስታወስ ሞክሪ። ይህም ቁጣሽን ለመቆጣጠር ይረዳሻል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ።”ቆላስይስ 3:15

  •    ይቅር ባይ ሁኚ። በመጀመሪያ ጉዳዩን በትዳር አጋርሽ ቦታ ሆነሽ ለመመልከት ጥረት አድርጊ። ይህም የትዳር አጋርሽን ‘ስሜት ለመረዳት’ ያስችልሻል። (1 ጴጥሮስ 3:8) ከዚያም ‘ያስቆጣኝ ነገር የትዳር አጋሬን ይቅር እንዳልል የሚያደርግ ነው?’ በማለት ራስሽን ጠይቂ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ‘በደልን መተዉ ውበት ያጎናጽፋል’።ምሳሌ 19:11

  •    ሐሳብሽን በደግነትና በዘዴ አስረጂ። ስትናገሪ ‘እኔ’ እያልሽ አውሪ። ለምሳሌ፣ “የት እንዳለህ ደውለህ እንኳ አትናገርም?” ከማለት ይልቅ “እየመሸ ሲሄድ በጣም ተጨነቅኩ፤ ደህንነትህን ማረጋገጥ ፈልጌ ነበር” ብለሽ ተናገሪ። ሐሳብሽን በገርነት መግለጽሽ ቁጣሽን ለመቆጣጠር ይረዳሻል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን።”—ቆላስይስ 4:6

  •    በጥሞና አዳምጪ። ሐሳብሽን ከገለጽሽ በኋላ የትዳር ጓደኛሽ ሲናገር ጣልቃ ሳትገቢ አዳምጪው። ተናግሮ ሲጨርስ ሐሳቡን በትክክል መረዳትሽን ለማረጋገጥ በራስሽ አባባል ደግመሽ መናገርሽ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በጥሞና ማዳመጥሽ፣ ቁጣሽን ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ‘ለመስማት የፈጠናችሁ ለመናገር የዘገያችሁ ሁኑ።’ያዕቆብ 1:19