በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በእምነታቸው ምሰሏቸው | ኢዮብ

“ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!”

“ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!”

 ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ክፉኛ በሚያሠቃይ ቁስል ተመትቶ መሬት ላይ ተቀምጧል። የወረሩትን ዝንቦች ለማባረር እንኳ አቅም የሌለው ይህ ሰው አንገቱን አቀርቅሮ ብቻውን ቁጭ ብሏል። ሐዘኑን ለመግለጽ አመድ ላይ ተቀምጦ የቆሰለ ገላውን በገል ያክካል። ብዙ ነገር አጥቷል፤ የነበረው ግርማ ሞገስ ሁሉ ጠፍቷል። ወዳጆቹ፣ ጎረቤቶቹና ዘመዶቹ ትተውታል። ትናንሽ ልጆች እንኳ እያሾፉበት ነው። አምላኩ ይሖዋም እንደተወው ተሰምቶታል፤ ግን ተሳስቶ ነበር።—ኢዮብ 2:8፤ 19:18, 22

 ይህ ሰው ኢዮብ ነው። አምላክ ስለ እሱ ሲናገር “በምድር ላይ እንደ እሱ ያለ ሰው የለም” ብሎ ነበር። (ኢዮብ 1:8) ኢዮብ ከሞተ ብዙ መቶ ዘመናት ካለፉ በኋላም ይሖዋ ኢዮብን በጽድቁ እንደ ምሳሌ ጠቅሶታል።—ሕዝቅኤል 14:14, 20

 መከራ ወይም ያልታሰበ አደጋ ደርሶብሃል? ከሆነ የኢዮብ ታሪክ በእጅጉ ሊያጽናናህ ይችላል። በተጨማሪም ታሪኩ ከሁሉም የአምላክ አገልጋዮች የሚጠበቀውን ባሕርይ ማለትም ንጹሕ አቋምን በተመለከተ ያለህን ግንዛቤ ያሰፋልሃል። ንጹሕ አቋም ለአምላክ ሙሉ በሙሉ ማደርንና አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥምም የእሱን ፈቃድ ማድረግን ይጨምራል። ስለ ንጹሕ አቋም ለመማር እስቲ የኢዮብን ታሪክ እንመርምር።

ኢዮብ ያላወቀው ነገር

 ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የሆነው ሙሴ፣ ኢዮብ ከሞተ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ታሪኩን እንደጻፈው ይታመናል። ሙሴ ኢዮብ ያጋጠሙትን ነገሮች ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በሰማይ ላይ ተከናውነው የነበሩ ነገሮችንም ጭምር በመንፈስ ተመርቶ ገልጾልናል።

 ዘገባው የሚጀምረው ኢዮብ ደስተኛ ሕይወት ይመራ እንደነበር በመተረክ ነው። ኢዮብ በዖጽ ምድር የሚኖር ታዋቂ፣ የተከበረና ሀብታም ሰው ነበር፤ ዖጽ የምትገኘው በሰሜናዊ አረቢያ ሳይሆን አይቀርም። ኢዮብ ድሆችን ይረዳ እንዲሁም ለተጨቆኑት ይሟገት ነበር። ኢዮብና ሚስቱ አሥር ልጆች ነበሯቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢዮብ መንፈሳዊ ሰው ነበር። የሩቅ ዘመዶቹ የሆኑት አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ዮሴፍ እንዳደረጉት ሁሉ ይሖዋን ለማስደሰት አቅሙ የፈቀደውን ያደርግ ነበር። እንደነዚህ ሰዎች ኢዮብም ለቤተሰቡ እንደ ካህን በመሆን ልጆቹን ወክሎ መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።—ኢዮብ 1:1-5፤ 31:16-22

 ቀጥሎ ግን ተራኪው ትኩረቱን ወደ ሌላ አቅጣጫ በማዞር በሰማይ ስለተከናወነው ነገር ገለጸ። ኢዮብ ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። የይሖዋ ታማኝ መላእክት በአምላክ ፊት ተሰብስበው ሳለ ዓመፀኛው መልአክ ሰይጣን መጣ። ሰይጣን ጻድቁን ኢዮብን እንደሚጠላው ይሖዋ ያውቅ ነበር፤ በመሆኑም ስለ ኢዮብ አስደናቂ አቋም ለሰይጣን ነገረው። በዚህ ጊዜ ሰይጣን “ኢዮብ አምላክን የሚፈራው እንዲያው በከንቱ ነው? እሱን፣ ቤቱንና ያለውን ነገር ሁሉ በአጥር ከልለህ የለም?” በማለት መለሰ። ሰይጣን ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎችን ይጠላል። ምክንያቱም በሙሉ ልባቸው ለይሖዋ ያደሩ መሆናቸውን ሲያሳዩ ሰይጣን ከሃዲና ጨካኝ መሆኑን ማረጋገጣቸው ነው። ስለዚህ ሰይጣን፣ ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ ነው በማለት ወነጀለው። ሰይጣን ኢዮብ ያለውን ሁሉ ቢያጣ አምላክን ፊት ለፊት እንደሚረግም ተናገረ።—ኢዮብ 1:6-11

 ኢዮብ ባያውቀውም ይሖዋ ትልቅ መብት ሰጥቶት ነበር፤ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን የማረጋገጥ አጋጣሚ አገኘ። ሰይጣን ኢዮብ ያለውን ነገር በሙሉ እንዲያጠፋ ተፈቀደለት። በኢዮብ ላይ ግን ጉዳት እንዲያደርስ አልተፈቀደለትም። ከዚያም ሰይጣን በጭካኔ ጥቃት ሰነዘረ። ኢዮብ በአንድ ቀን አሰቃቂ መከራ ተደራረበበት። በመጀመሪያ ከብቶቹና አህዮቹ፣ ከዚያም በጎቹ፣ ቀጥሎም ግመሎቹ በድንገት እንዳለቁ ሰማ። ከዚህ የከፋው ደግሞ እንስሶቹን የሚጠብቁት አገልጋዮቹ ተገደሉ። ከጥፋቱ ጋር ተያይዞ ለኢዮብ የደረሰው አንደኛው መልእክት “ከአምላክ ዘንድ” እሳት እንደወረደ የሚገልጽ ነበር፤ ይህ ምናልባት መብረቅን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ኢዮብ ስለሞቱት አገልጋዮቹ ወይም ስላጋጠመው ድንገተኛ ድህነት የሚያመዛዝንበት ዕድል እንኳ ሳያገኝ አንድ አስከፊ ዜና ተነገረው። አሥሩ ልጆቹ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ተሰባስበው ሳሉ ኃይለኛ ነፋስ መጥቶ ቤቱን መታውና ሁሉም ልጆቹ ሞቱ!—ኢዮብ 1:12-19

 ኢዮብ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት እንኳ አዳጋች ነው። ልብሱን ቀደደ፤ ፀጉሩን ተላጨ፤ ከዚያም መሬት ላይ ተደፋ። ኢዮብ አምላክ የሰጠውን ነገር መልሶ እንደነሳው ተሰምቶት ነበር። በእርግጥም መሠሪ የሆነው ሰይጣን መከራው የመጣው ከአምላክ እንዲመስል አድርጎ ነበር። ያም ቢሆን፣ ሰይጣን እንደጠበቀው ኢዮብ አምላክን አልረገመም። ከዚህ ይልቅ ኢዮብ “የይሖዋ ስም ምንጊዜም ይወደስ” አለ።—ኢዮብ 1:20-22

ኢዮብ ሰይጣን እንደከሰሰው አላወቀም ነበር

“በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል”

 በንዴት የበገነው ሰይጣን ተስፋ አልቆረጠም። መላእክት ተሰብስበው ባሉበት ለሁለተኛ ጊዜ ይሖዋ ፊት ቀረበ። ኢዮብ የሰይጣንን ጥቃቶች በሙሉ በጽናት በመቋቋሙ ይሖዋ የኢዮብን ንጹሕ አቋም አድንቆ በድጋሚ ተናገረ። ሰይጣን ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ቁርበት ስለ ቁርበት ነው። ሰውም ለሕይወቱ ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል። ሆኖም እስቲ እጅህን ዘርግተህ በአጥንቱና በሥጋው ላይ ጉዳት አድርስበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።” ሰይጣን ኢዮብ በከባድ ሕመም ከተመታ አምላክን እንደሚረግም እርግጠኛ ነበር። ይሖዋ ግን ሙሉ በሙሉ በአገልጋዩ በመተማመን፣ የኢዮብን ሕይወት ሳይነካ በሰውነቱ ላይ ጉዳት እንዲያደርስ ለሰይጣን ፈቀደለት።—ኢዮብ 2:1-6

 ኢዮብ በመግቢያው ላይ በተጠቀሰው አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ የገባው በዚህ ጊዜ ነበር። ሚስቱም ብትሆን በጣም ታሳዝናለች። አሥሩን ልጆቿን ማጣቷ ያስከተለባት ሐዘን ሳያንስ ባሏ በበሽታ ሲማቅቅ ለማየት ተገዳለች! በጭንቀት ተውጣ “አሁንም በንጹሕ አቋምህ እንደጸናህ ነው? አምላክን እርገምና ሙት!” አለችው። ኢዮብ በደንብ ከሚያውቃትና ከሚወዳት ሚስቱ እንዲህ ዓይነት ንግግር አልጠበቀም። በመሆኑም “የምትናገሪው ማመዛዘን እንደጎደላት ሴት ነው” አላት። በዚህ ጊዜም ቢሆን ኢዮብ አምላኩን አልረገመም፤ በከንፈሩም አልበደለም።—ኢዮብ 2:7-10

 ይህ አሳዛኝ ታሪክ አንተንም እንደሚመለከትህ ታውቃለህ? ሰይጣን የወነጀለው ኢዮብን ብቻ ሳይሆን የሰው ዘርን በአጠቃላይ እንደሆነ ልብ በል። “ሰውም ለሕይወቱ ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል” ብሏል። በሌላ አነጋገር ሰይጣን ማናችንም ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ እንደማንችል ተከራክሯል። አምላክን እንደማትወደውና ሕይወትህን ለማዳን ስትል አምላክን እንደምትከዳ ያምናል። በሌላ አባባል ሰይጣን ‘እሱም እንደ እኔ ራስ ወዳድ ነው’ በማለት እየከሰሰህ ነው! ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ማጋለጥ ትፈልጋለህ? ሁላችንም እንዲህ የማድረግ አጋጣሚ ተከፍቶልናል። (ምሳሌ 27:11) እስቲ አሁን ደግሞ ኢዮብ ቀጥሎ ምን እንዳጋጠመው እንመልከት።

የሚያስጨንቁ አጽናኞች

 ኢዮብን የሚያውቁ ሦስት ሰዎች ወይም ዘገባው እንደሚለው ጓደኞቹ፣ የደረሰበትን ነገር ሲሰሙ እሱን ለማጽናናት መጡ። ከርቀት ሲያዩት እሱ መሆኑን እንኳ መለየት አልቻሉም። ቆዳው ከመጥቆሩና ከመታመሙ የተነሳ የቀድሞው ገጽታው ጨርሶ የለም። እነዚህ ሦስት ሰዎች ማለትም ኤሊፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በማልቀስና ራሳቸው ላይ አቧራ በመነስነስ ያዘኑ መስለው ለመታየት ሞከሩ። ከዚያም ጸጥ ብለው ከኢዮብ ጋር መሬት ላይ ተቀመጡ። አንድ ሳምንት ሙሉ አንድም ቃል ሳይተነፍሱ ቀንና ሌሊት መሬት ላይ ቁጭ አሉ። ዝም ያሉት ለማጽናናት ብለው አይደለም፤ ምክንያቱም ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ምንም ጥያቄ አልጠየቁትም። የተረዱት ማንም ሰው ሊያስተውል የሚችለውን ነገር ይኸውም ሥቃዩ በጣም ከባድ መሆኑን ብቻ ነው።—ኢዮብ 2:11-13፤ 30:30

 በመጨረሻም ኢዮብ ራሱ መናገር ጀመረ። በሥቃይ ተሞልቶ፣ የተወለደበትን ቀን ረገመ። የሐዘኑ ዋነኛ መንስኤ ምን እንደሆነም ገለጸ። ያሳዘነው ዋነኛ ነገር መከራ ያመጣበት አምላክ እንደሆነ ማሰቡ ነው! (ኢዮብ 3:1, 2, 23) ኢዮብ እምነቱ ባይጠፋም ማጽናኛ በእጅጉ ያስፈልገው ነበር። ሦስቱ ሰዎች መናገር ሲጀምሩ ግን ኢዮብ ዝምታቸው የተሻለ እንደነበር ተገነዘበ።—ኢዮብ 13:5

 ከኢዮብ በዕድሜ የሚበልጠው፣ ምናልባትም ከሁሉም ታላቅ የሆነው ኤሊፋዝ መናገር ጀመረ። ቀጥሎም በልዳዶስና ሶፋር ተናገሩ። ሁለቱ ሰዎች እንደ በቀቀን የኤሊፋዝን ንግግር አስተጋብተዋል ሊባል ይችላል። የኢዮብ አጽናኝ ተብዬዎች ከተናገሩት ነገር አንዳንዱ ጎጂ ላይመስል ይችላል፤ ምክንያቱም ብዙ ሰዎች ደጋግመው እንደሚያነበንቡት አምላክ ታላቅ እንደሆነ፣ ክፉ ሰዎችን እንደሚቀጣና ለጥሩ ሰዎች ወሮታቸውን እንደሚከፍል ተናግረዋል። ሆኖም ከመጀመሪያው አንስቶ ንግግራቸው ደግነት የጎደለው ነበር። ኤሊፋዝ የተጠቀመው፣ የሚከተለውን አሳማኝ የሚመስል ሆኖም ብዙ ነገሮችን ከግምት ያላስገባ መከራከሪያ ነጥብ ነበር፦ ‘አምላክ ጥሩ ነው እንዲሁም ክፉዎችን ይቀጣል፤ ኢዮብ ቅጣት እየደረሰበት እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ስለዚህ ኢዮብ የሆነ ክፋት ፈጽሟል ማለት ነው።’—ኢዮብ 4:1, 7, 8፤ 5:3-6

 ኢዮብ ሦስቱ አጽናኝ ተብዬዎች የተናገሩትን ሐሳብ ያልተቀበለው መሆኑ አያስገርምም። እንዲያውም አጥብቆ ተቃውሟቸዋል። (ኢዮብ 6:25) እነሱ ግን ኢዮብ በስውር የፈጸመው ኃጢአት እንዳለ እርግጠኞች ነበሩ፤ ኢዮብ መከራ የደረሰበት በጥፋቱ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። ኤሊፋዝ ኢዮብ እብሪተኛ፣ ክፉና ፈሪሃ አምላክ የሌለው እንደሆነ በመግለጽ ወነጀለው። (ኢዮብ 15:4, 7-9, 20-24፤ 22:6-11) ሶፋርም ክፋት መፈጸሙንና በኃጢአት መደሰቱን እንዲያቆም ነገረው። (ኢዮብ 11:2, 3, 14፤ 20:5, 12, 13) በልዳዶስ ደግሞ እጅግ የሚያቆስል ነገር ተናገረ። የኢዮብ ልጆች የሆነ የፈጸሙት ኃጢአት እንዳለና መሞት እንደሚገባቸው ገለጸ።—ኢዮብ 8:4, 13

ሦስቱ የኢዮብ ጓደኞች የሥቃይ እንጂ የመጽናናት ምንጭ አልሆኑለትም

በንጹሕ አቋም ላይ የተሰነዘረ ጥቃት

 ሦስቱ ሰዎች ከዚህም የከፋ ነገር አድርገዋል። ኢዮብ ለአምላክ ታማኝ እንዳልሆነ መናገራቸው ሳያንስ ሰዎች ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቃቸው ምንም ጥቅም እንደሌለው ተናገሩ! ኤሊፋዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በተናገረበት ወቅት አንድ መንፈስ እንዳነጋገረው ገልጾ ነበር። ኤሊፋዝ ከዚህ ጋኔን በሰማው ነገር ላይ ተመሥርቶ የደረሰበት መደምደሚያ መርዘኛ ነበር፤ አምላክ “በአገልጋዮቹ ላይ እምነት የለውም፤ በመላእክቱም ላይ ስህተት ያገኛል” ብሏል። እንደ እሱ አባባል ከሆነ የሰው ልጆች በፍጹም አምላክን ማስደሰት አይችሉም! በኋላ ደግሞ በልዳዶስ፣ አምላክ ኢዮብን ከእጭ አስበልጦ እንደማያየውና በንጹሕ አቋም መመላለሱ ምንም ግድ እንደማይሰጠው ተናግሯል።—ኢዮብ 4:12-18፤ 15:15፤ 22:2, 3፤ 25:4-6

 ከባድ መከራ የደረሰበትን ሰው ለማጽናናት ሞክረህ ታውቃለህ? እንዲህ ማድረግ ቀላል አይደለም። ሆኖም የኢዮብ አጽናኝ ተብዬዎች ያደረጉት ነገር ምን ማድረግ እንደሌለብን ያስተምረናል። እነዚህ ሰዎች ያንን ሁሉ ነገር ሲያወሩ ኢዮብን አንዴ እንኳ በስሙ አልጠሩትም! የኢዮብን ስሜት ለመረዳት ወይም እሱን በደግነት ለማነጋገር አልተነሳሱም። a አንተም ስሜቱ የተጎዳ ወዳጅህን ለማጽናናት ስትሞክር ሐዘኔታ፣ አሳቢነትና ደግነት ለማሳየት ሞክር። የግለሰቡን እምነትና ድፍረት ለማሳደግ ጥረት አድርግ፤ እንዲሁም በአምላክ እንዲታመን ብሎም ደግነቱን፣ ምሕረቱንና ፍትሑን እንዲያስተውል እርዳው። ሦስቱ አጽናኝ ተብዬዎች በኢዮብ ቦታ ቢሆኑ ኖሮ ኢዮብ እንዲህ ያለ ደግነት ያሳያቸው ነበር። (ኢዮብ 16:4, 5) ይሁንና ኢዮብ በንጹሕ አቋሙ ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት በተሰነዘረበት ጊዜ ምን አደረገ?

ኢዮብ በአቋሙ ጸንቷል

 ኢዮብ የደረሰበት መከራ ሳያንስ የጓደኞቹ ትችት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነበት። መጀመሪያውኑም ቢሆን ‘እንዳመጣለት እንደሚናገር’ እንዲሁም የሚናገረው ቃል “ተስፋ የቆረጠ ሰው ንግግር” እንደሆነ ገልጾ ነበር። (ኢዮብ 6:3, 26) ለምን እንዲህ እንዳለ መረዳት አያዳግትም። እንዳመጣለት የተናገረው በከፍተኛ ሐዘን ስለተዋጠ ነው። ስለ ጉዳዩ የነበረው ግንዛቤም በጣም ውስን ነበር። በእሱና በቤተሰቡ ላይ የደረሰው መከራ ድንገተኛ ስለሆነና መለኮታዊ ምንጭ ያለው ስለሚመስል መከራውን ያመጣበት ይሖዋ እንደሆነ ደምድሞ ነበር። ከበስተ ጀርባ ስለነበሩት ነገሮች ምንም እውቀት ስላልነበረው ባየው ነገር ላይ ተመሥርቶ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደረሰ።

 ያም ቢሆን ኢዮብ ጠንካራ እምነት ያለው ሰው ነበር። ከጓደኞቹ ጋር ባደረገው ክርክር ላይ የጠቀሰው አብዛኛው ሐሳብ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል፤ የተናገራቸው ቃላት ዛሬም ድረስ ትክክል፣ ማራኪና አበረታች ናቸው። አስደናቂ ስለሆኑት የይሖዋ ፍጥረታት በተናገረበት ወቅት አምላክ ካልገለጠለት በቀር ማንም ሰው በሌላ መንገድ ሊያውቀው የማይችለውን ነገር ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ‘ምድርን ያለምንም ነገር እንዳንጠለጠለ’ ገልጿል፤ የሳይንስ ሊቃውንት ይህን የደረሱበት ከበርካታ መቶ ዘመናት በኋላ ነው። b (ኢዮብ 26:7) ኢዮብ ስለ ወደፊት ተስፋው የተናገረው ሐሳብም እንደ ሌሎች የእምነት አባቶች ታላቅ እምነት እንዳለው የሚያሳይ ነው። ቢሞት እንኳ አምላክ እንደሚያስታውሰው፣ እንደሚናፍቀው አልፎ ተርፎም ከሞት እንደሚያስነሳው ያምን ነበር።—ኢዮብ 14:13-15፤ ዕብራውያን 11:17-19, 35

 በንጹሕ አቋም ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ኤሊፋዝና ሁለቱ ጓደኞቹ፣ ሰዎች ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቃቸው ለአምላክ ምንም እንደማይፈይድለት ገልጸው ነበር። ታዲያ ኢዮብ ይህን መርዘኛ ሐሳብ ተቀብሏል? በጭራሽ! ኢዮብ ይሖዋ የሰዎች ንጹሕ አቋም እንደሚያሳስበው አበክሮ ተናግሯል። “አምላክ . . . ንጹሕ አቋም እንዳለኝ ይገነዘባል” ብሏል። (ኢዮብ 31:6) በተጨማሪም ኢዮብ ሦስቱ አጽናኝ ተብዬዎች ያቀረቡት ሐሰተኛ ሐሳብ በንጹሕ አቋሙ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት እንደሆነ ገብቶት ነበር። የሰነዘሩት ሐሳብ የእነሱን አፍ ያዘጋውን ረጅሙን ንግግሩን እንዲናገር አነሳስቶታል።

 ኢዮብ ንጹሕ አቋም ከዕለት ተዕለት ሕይወቱ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም በአኗኗሩና በምግባሩ ንጹሕ አቋሙን እንደጠበቀ ተናገረ። ለምሳሌ ከማንኛውም ዓይነት ጣዖት አምልኮ እንደራቀ፣ ሌሎችን በአክብሮትና በደግነት እንደያዘ፣ ለትዳሩ ታማኝ በመሆን የሥነ ምግባር ንጽሕናውን እንደጠበቀና ከሁሉም በላይ ደግሞ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን በታማኝነት እንዳገለገለ ገለጸ። በመሆኑም ኢዮብ በሙሉ ልቡ “እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!” ማለት ችሎ ነበር።—ኢዮብ 27:5፤ 31:1, 2, 9-11, 16-18, 26-28

ኢዮብ ምንም ነገር ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍበት አልፈቀደም

ኢዮብን በእምነቱ እንምሰለው

 ንጹሕ አቋምን የመጠበቅ ጉዳይ የኢዮብን ያህል ያሳስብሃል? ‘ንጹሕ አቋሜን እጠብቃለሁ’ ብሎ መናገር ቀላል ነው፤ ሆኖም ኢዮብ ንጹሕ አቋምን መጠበቅ ተግባርንም እንደሚጨምር ተገንዝቦ ነበር። አስቸጋሪ ሁኔታ ቢገጥመንም አምላክን በመታዘዝና በየዕለቱ በእሱ ዘንድ ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ በሙሉ ልባችን ለአምላክ ያደርን መሆናችንን እናሳያለን። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ልክ እንደ ኢዮብ የይሖዋን ልብ እናስደስታለን፤ ጠላቱን ሰይጣንን ደግሞ እናበሳጨዋለን። ኢዮብን በእምነቱ መምሰል የምንችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ይህ ነው!

 ይሁንና የኢዮብ ታሪክ በዚህ አላበቃም። የራሱን ጽድቅ በማረጋገጥ ላይ ከማተኮሩ የተነሳ ሚዛኑን ስቶ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ለአምላኩ ጥብቅና ሳይቆም ቀርቷል። በመሆኑም እርማትና መንፈሳዊ እርዳታ ያስፈልገው ነበር። ደግሞም ሥቃዩና ሐዘኑ ገና ስላልለቀቀው እውነተኛ ማጽናኛ ያስፈልገዋል። ታዲያ ይሖዋ በእምነትና በንጹሕ አቋም ረገድ ምሳሌ ለሚሆነው ለዚህ ሰው ምን ያደርግለት ይሆን? በዚህ ዓምድ ውስጥ የሚወጣ ሌላ ርዕስ እነዚህን ነጥቦች ያብራራል።

a የሚያስገርመው ነገር፣ ኤሊፋዝ እሱና ጓደኞቹ ኢዮብን በለሰለሰ አንደበት ወይም በደግነት እንዳነጋገሩት ገልጾ ነበር፤ ምናልባት እንዲህ የተሰማው ኢዮብ ላይ ስላልጮኹበት ሊሆን ይችላል። (ኢዮብ 15:11) ይሁን እንጂ በለሰለሰ አንደበት የተነገሩ ቃላትም ስሜትን ሊያቆስሉ ይችላሉ።

b የሳይንስ ሊቃውንት ምድር ያለምንም ድጋፍ እንደተንጠለጠለች የሚገልጽ ንድፈ ሐሳብ ማቅረብ የጀመሩት ከ3,000 ዓመት ገደማ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። አብዛኞቹ ሰዎች ኢዮብ የተናገረውን ሐሳብ እውነተኝነት መቀበል የጀመሩት ደግሞ ምድርን ከሕዋ ላይ ፎቶግራፍ ማንሳት ከተጀመረ በኋላ ነው።