በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

የፖሜሎ ልጣጭ ያለው ግጭት የመቋቋም ችሎታ

የፖሜሎ ልጣጭ ያለው ግጭት የመቋቋም ችሎታ

 ፖሜሎ በዛፍ ላይ የሚበቅል የብርቱካን ዝርያ የሆነ ጣፋጭ ፍሬ ነው። ይህ ፍሬ ከ10 ሜትር ከሚበልጥ ከፍታ ቢወድቅም ጉዳት አይደርስበትም። ፖሜሎ እንዲህ ያለ ግጭት የመቋቋም ችሎታ ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው?

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ተመራማሪዎች ነጭ ቀለም ያለው የፖሜሎ ልጣጭ ውስጠኛ ክፍል እንደ ስፖንጅ ዓይነት ባሕርይ እንዳለው አስተውለዋል፤ በዚህ ክፍል ውስጥ ባሉት ሴሎች መካከል ክፍተት አለ። ወደሚበላው ክፍል እየተጠጋን ስንሄድ በሴሎቹ መካከል ያለው ክፍተት እየጨመረ ይሄዳል፤ ይህ ክፍተት በአየር ወይም በፈሳሽ የተሞላ ነው። ፍሬው ወድቆ ከመሬቱ ጋር ሲጋጭ ይህ ፈሳሽ እንደ ትራስ ይሆንለታል። የፖሜሎው ልጣጭ በመኮማተር የግጭቱን ኃይል ስለሚቋቋም ፍሬው አይፈርጥም።

 ሳይንቲስቶች የፖሜሎ ልጣጭ ያለውን ንድፍ በመኮረጅ ከብረት የተሠራ ግጭትን መቋቋም የሚችል ፎም ያዘጋጁ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሙከራ እያካሄዱበት ነው። ሳይንቲስቶች እንዲህ ያለው ንድፍ ለሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች የጭንቅላት መከላከያ ለመሥራት፣ ለመኪኖች የግጭት መከላከያ ለማዘጋጀት እንዲሁም የጠፈር ጣቢያዎች በተወርዋሪ ኮከቦች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል እንደሚያስችል ያምናሉ።

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? የፖሜሎ ልጣጭ ያለው ግጭት የመቋቋም ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?