በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

E+/IvanJekic via Getty Images

ንድፍ አውጪ አለው?

የዳንዴሊየን ዘር የበረራ ጥበብ

የዳንዴሊየን ዘር የበረራ ጥበብ

 ተፈጥሮ ላይ ድንቅ የበረራ ጥበብ ከምናይባቸው ነገሮች አንዱ የዳንዴሊየን ዘር ነው። ነፋስ የዳንዴሊየን ተክል ላይ ሲነፍስ ብዛት ያላቸው የዳንዴሊየን ዘሮች አየር ላይ ይበተናሉ፤ ትናንሽ ፓራሹቶች ይመስላሉ። አየር ላይ የሚበተኑት ለመሬት ቀረብ ብለው ቢሆንም አንዳንዶቹ እስከ አንድ ኪሎ ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ተንሳፍፈው መቆየት ይችላሉ። አየር ላይ ተንሳፍፈው ለመቆየት የሚረዳቸው ምንድን ነው? ሳይንቲስቶች በዳንዴሊየን ዘር ላይ ምርምር በማድረግ አዲስ የበረራ ጥበብ አግኝተዋል። ዘሮቹ በኃይል አጠቃቀም ረገድ፣ ዘመኑ ካፈራቸው ፓራሹቶች በአራት እጥፍ የተሻሉ ናቸው፤ የተሻለ ተደላድሎ የመንሳፈፍ ችሎታም አላቸው።

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ እያንዳንዱ የዳንዴሊየን ዘር፣ በአንድ ግንድ ላይ የተንጠለጠለ ነው። የግንዱ ጫፍ ላይ ቀጫጭን በሆኑ ፀጉር የሚመስሉ ነገሮች የተሞላ እፉዬ ገላ የሚመስል ነገር አለ፤ ይህ ነገር ፓፐስ ተብሎ ይጠራል። ፓፐስ እንደ ፓራሹት ዘሩን ተሸክሞ አየር ላይ ይንሳፈፋል።

ዘሩ ቶሎ ወደ መሬት እንዳይወርድ የሚያግዘው፣ የአየር ሽክርክሪት እንደሆነ የምርምር ውጤቶች አሳይተዋል

 የፓፐስ ፀጉሮች፣ ዘሩ አየር ላይ ተንሳፍፎ እንዲቆይ የሚያደርጉበትን ዘዴ ሳይንቲስቶች ደርሰውበታል። አየር በፀጉሮቹ ዙሪያና በመሃላቸው ሲያልፍ አናታቸው ላይ ቀለበት መሰል ሽክርክሪት ይፈጠራል። የአየር ሽክርክሪቱ የተፈጠረበት ቦታ ላይ ግፊቱ አነስተኛ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ፓፐሱ ከፍ ከፍ እንዲል ያደርጋል። በመሆኑም ወደ መሬት የሚወርድበትን ፍጥነት ይቀንሰዋል።

 ፓፐስ፣ አየር እንደሚያሳልፍ ፓራሹት ነው ማለት ይቻላል፤ ለዚህም ሚስጥሩ ፀጉሮቹ የተቀመጡበት አስደናቂ መንገድ ነው። አየር ላይ ሲሆን ኃይል የሚጠቀምበት መንገድና ሳይናወጥ የመንሳፈፍ ችሎታው ግን ከፓራሹቶች የላቀ ነው! የሚገርመው ደግሞ ፓፐሱ 90 በመቶውን ክፍት ነው! በመሆኑም ብዙ ቁስ አካል አይጠቀምም።

 ሳይንቲስቶች የዳንዴሊየን ዘርን የበረራ ጥበብ የሚኮርጁባቸው መንገዶች እየፈለጉ ነው። ለምሳሌ፣ ተጨማሪ የኃይል ምንጭ የማያስፈልጋቸው ወይም ጥቂት ብቻ የሚያስፈልጋቸው ትናንሽ ድሮኖችን ለመሥራት አስበዋል። እነዚህ ድሮኖች የአየር ብክለትን መቆጣጠርን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች ሊውሉ ይችላሉ።

 የዳንዴሊየን ዘር አየር ላይ ሲንሳፈፍ ተመልከት

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? ከፍተኛ ቅልጥፍና የሚታይበት የዳንዴሊየን ዘር የመንሳፈፍ ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?