በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ትችላለህ

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ጥረት ማድረግ ምን ጥቅም አለው?

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ጥረት ማድረግ ምን ጥቅም አለው?

“መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው የሚታወቅ የሃይማኖት መጽሐፍ ነው። ይሁንና የሌላ አገር መጽሐፍ ስለሆነ ለቻይናውያን ምንም አይጠቅምም።”—ሊን፣ ቻይና

“የራሴን የሂንዱ ሃይማኖት ቅዱስ መጻሕፍት እንኳ መረዳት አቅቶኛል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ሊገባኝ ይችላል?”—ኧሚት፣ ሕንድ

“መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ መጽሐፍ ስለሆነ ለመጽሐፉ አክብሮት አለኝ፤ ደግሞም በብዛት በመሸጥ ረገድ ተወዳዳሪ እንደሌለው ሰምቻለሁ። ይሁንና መጽሐፉን በዓይኔ እንኳ አይቼው አላውቅም።”—ዩሚኮ፣ ጃፓን

በዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍ ያለ ግምት አላቸው። ሆኖም ስለ መጽሐፉ ይዘት የሚያውቁት ነገር የለም፤ አወቁ ቢባል እንኳ እውቀታቸው ቁንጽል ነው። ይህ አባባል በእስያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሁኔታ በትክክል ይገልጻል፤ መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት በሚሰራጭበት ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ሁኔታም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም።

ያም ሆኖ ‘መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ጥረት ማድረግ የሚኖርብኝ ለምንድን ነው?’ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ። ይህን ቅዱስ መጽሐፍ መረዳትህ የሚከተሉትን ጥቅሞች ያስገኝልሃል፦

  • እውነተኛ እርካታና ደስታ

  • የቤተሰብ ችግሮችን መቋቋም የሚቻልበት ጥበብ

  • ጭንቀትን የምትቋቋምበት ጥንካሬ

  • ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት

  • ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም መቻል

ለምሳሌ ያህል፣ በጃፓን የምትኖረውን የዮሺኮን ሁኔታ ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ ስለፈለገች መጽሐፉን በግሏ ለማንበብ ወሰነች። ይህስ ምን አስገኘላት? እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ እንድገነዘብ እና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ተስፋ እንዲኖረኝ ረድቶኛል። አሁን የባዶነት ስሜት አይሰማኝም።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኧሚት መጽሐፍ ቅዱስን በግሉ ለመመርመር ወሰነ። ከዚያም “በጣም የገረመኝ ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ሁሉ የሚጠቅም መረጃ የያዘ መሆኑ ነው” ብሏል።

መጽሐፍ ቅዱስ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። አንተስ መጽሐፉን በመመርመር እንዴት ሊጠቅምህ እንደሚችል ለምን አታይም?