በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

የሰው ልጆች ምድርን ለዘለቄታው ያጠፏት ይሆን?

የሰው ልጆች ምድርን ለዘለቄታው ያጠፏት ይሆን?

“ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—ንጉሥ ሰሎሞን፣ 11ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. *

በጥንት ዘመን የኖረው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ፣ ጠዋት ታይቶ ቀን ላይ እንደሚጠፋ ጤዛ የሆነው የሰው ልጅ ዕድሜ ከምድር ዘላለማዊነት አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። በእርግጥም ላለፉት ሺህ ዓመታት ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ ቆይቷል፤ ፕላኔቷ ምድራችን ግን እስከ አሁን ድረስ የተለያዩ አደገኛ ሁኔታዎችን ተቋቁማ በውስጧ ያሉትን ሕያዋን ፍጥረታት ማኖር ችላለች።

አንዳንዶች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ባሉት ዓመታት ዓለማችን በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጠች እንደሆነ ይናገራሉ። የአንድ ሰው የሕይወት ዘመን በሚያክል ጊዜ ብቻ እንኳ በትራንስፖርት፣ በመገናኛ አውታሮችና በሌሎች የቴክኖሎጂ መስኮች ታላቅ እመርታ የታየ ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አስከትሏል። ብዙዎች በአንድ ወቅት ፈጽሞ የማይታሰብ የነበረ የቅንጦት ሕይወት እየመሩ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ የዓለም የሕዝብ ብዛት በሦስት እጥፍ ያህል አድጓል።

ይህ ሁሉ ለውጥ ግን ያስከተለው ጉዳት አለ። የሰው ልጆች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለሕይወት አስፈላጊ በሆኑ የምድር ተፈጥሯዊ ዑደቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ይነገራል። እንዲያውም አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት፣ የሰው ልጆች ባለፉት ጥቂት መቶ ዓመታት ያደረጉት እንቅስቃሴ በምድር ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያስከተለ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሰው ልጆች ‘ምድርን የሚያጠፉበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ራእይ 11:18) አንዳንዶች፣ የምንኖረው እንዲህ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ያስባሉ።  ወደፊት በምድር ላይ ምን ያህል ጉዳት ይደርስ ይሆን? ደግሞስ ጉዳቱ፣ ሊቀለበስ የማይችል ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል? በእርግጥ የሰው ልጆች ምድርን ለዘለቄታው ያጠፏት ይሆን?

ሊቀለበስ የማይችል ደረጃ ላይ ይደርሳል?

ምድር ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ሊቀለበስ የማይችል ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው? አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት፣ በምድር ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት የሚያስከትለውን ውጤት አስቀድሞ መተንበይ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ይሰማቸዋል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት፣ ድንገተኛና ያልተጠበቁ የአየር ንብረት ለውጦች አውዳሚ የሆነ ውጤት የሚያስከትሉበት ጊዜ ቀርቧል የሚል ስጋት አላቸው።

ለምሳሌ ያህል፣ በምዕራብ አንታርክቲካ የሚገኘውን የበረዶ ንጣፍ እንመልከት። የምድር ሙቀት መጨመር በዚሁ ከቀጠለ የበረዶው ንጣፍ ሊቀለበስ በማይችል ሁኔታ መቅለጥ እንደሚጀምር አንዳንዶች ያምናሉ። ምክንያቱም በረዶ በተፈጥሮው የፀሐይን ጨረሮች አንጥሮ የመመለስ ችሎታ አለው። ይሁን እንጂ የበረዶ ንጣፉ እየሳሳና መጠኑ እየቀነሰ ሲሄድ ከሥር ያለው የውቅያኖሱ ክፍል ውሎ አድሮ ለፀሐይ ጨረር ይጋለጣል፤ የውቅያኖስ ውኃ ደግሞ የፀሐይ ጨረሮችን አንጥሮ የመመለስ ችሎታው አነስተኛ ነው። ጠቆር ያለው ላይኛው የውቅያኖስ ክፍል ከፀሐይ የሚመጣውን ሙቀት ይዞ ስለሚያስቀር በረዶው ይበልጥ እንዲቀልጥ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ማቆሚያ የሌለው አውዳሚ ዑደት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። የበረዶው መቅለጥ የባሕር ውኃ ከፍታ እንዲጨምር ያደርጋል፤ በዚህም የተነሳ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ።

እየተባባሰ የሚሄደው የሥነ ምህዳር ቀውስ

ፕላኔታችን በአሁኑ ወቅት የተጋረጠባትን ጊዜ የማይሰጥ አደጋ ለመጋፈጥ የተለያዩ ፖሊሲዎች ተነድፈዋል። ለረጅም ጊዜ ሲሠራበት የቆየው አንዱ ፖሊሲ ‘ዘላቂነት ያለው ልማት’ የሚባለው ነው፤ ይህ ፖሊሲ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ምድር ካላት አቅም ጋር የሚጣጣም መሆን እንዳለበት ይገልጻል። ታዲያ ይህ ፖሊሲ ምን ውጤት አስገኝቷል?

የሚያሳዝነው ግን እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ቀውስ ሁሉ በምድራችን ሥነ ምህዳር ላይ የሚደርሰው ቀውስም ከዕለት ወደ ዕለት ማሻቀቡን ቀጥሏል። ሰዎች የምድርን ሀብት የሚጠቀሙት ተፈጥሮ መልሶ ከሚተካው በላይ ነው። ታዲያ ማድረግ የምንችለው ነገር ይኖር ይሆን? አንድ የሥነ ምህዳር ባለሙያ “ፕላኔቷን እንዴት መያዝ እንዳለብን መላው ጠፍቶናል ማለት ይቻላል” በማለት ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ሁኔታው መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰው አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል’ ከገለጸው ሐሳብ ጋር በጣም የሚስማማ ነው።—ኤርምያስ 10:23

 በሌላ በኩል ደግሞ ፈጣሪ፣ ሰዎች የምድርን የተፈጥሮ ሀብት ሙሉ በሙሉ እንዲያራቁቱ እንደማይፈቅድ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። መዝሙር 115:16 “[አምላክ] ምድርን . . . ለሰው ልጆች ሰጣት” ይላል። በእርግጥም ምድር፣ የሰማዩ አባታችን የሰጠን “መልካም ስጦታ” ናት። (ያዕቆብ 1:17) ታዲያ የአምላክ ስጦታ፣ ለተወሰነ ጊዜ አገልግሎት ከሰጠ በኋላ እንደሚበላሽ ዕቃ ሊሆን ይችላል? እንዲህ እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው! የምድር አሠራር በራሱ ይህን የሚጠቁም ነው።

የፈጣሪ ዓላማ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የዘፍጥረት መጽሐፍ አምላክ ምድርን እንዴት በጥንቃቄ እንደሠራት በዝርዝር ይነግረናል። መጀመሪያ ላይ ምድር “ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች። የምድርን ጥልቅ ስፍራ ሁሉ ጨለማ ውጦት ነበር።” ሆኖም ለሕይወት አስፈላጊ የሆነው ‘ውኃ’ በወቅቱ በምድር ላይ እንደነበር ዘገባው ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:2) ከዚያም አምላክ “ብርሃን ይሁን” አለ። (ዘፍጥረት 1:3) ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው በዚህ ጊዜ የፀሐይ ብርሃን ከባቢ አየሩን ሰንጥቆ ገባ፤ በመሆኑም በምድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ብርሃን ታየ። ከዚያም ደረቅ ምድርና ባሕር እንደተፈጠረ ዘገባው ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:9, 10) ቀጥሎም ምድር ‘ዕፀዋትን፣ ዘር የሚሰጡ ተክሎችንና ፍሬ የሚያፈሩ ዛፎችን’ አበቀለች። (ዘፍጥረት 1:12) ከዚያም እንደ ፎቶሲንተሲስ ያሉ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ተፈጥሯዊ ሂደቶችና ዑደቶች ጀመሩ። አምላክ ምድርን እንዲህ አድርጎ ያዘጋጃት ለምን ዓላማ ነበር?

የጥንቱ ነቢይ ኢሳይያስ፣ አምላክ ‘ምድርን እንዳበጃት፣ እንደሠራትና እንደመሠረታት እንዲሁም የሰው መኖሪያ እንጂ ባዶ እንድትሆን እንዳልፈጠራት’ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 45:18) የአምላክ ዓላማ ምድር ለዘላለም የሰው መኖሪያ እንድትሆን እንደነበር ከዚህ ማየት ይቻላል።

የሚያሳዝነው ነገር፣ የሰው ልጆች አምላክ የሰጣቸውን ውብ ስጦታ በአግባቡ ባለመጠቀማቸው ምድርን አበላሽተዋታል። ሆኖም የፈጣሪ ዓላማ አልተለወጠም። በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ይዋሽ ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፤ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፤ ተናግሮ አያደርገውምን?” (ዘኍልቍ 23:19) አምላክ ምድር ስትበላሽ ዝም ብሎ አያይም፤ እንዲያውም ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን የሚያጠፋበት’ ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ ነው።—ራእይ 11:18

የሰው ልጅ የዘላለም መኖሪያ የሆነችው ምድር

ኢየሱስ ክርስቶስ ታዋቂ በሆነው የተራራው ስብከቱ ላይ “ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” ብሏል። (ማቴዎስ 5:5) ኢየሱስ በዚሁ ስብከት ላይ ምድርን ከጥፋት  የሚታደጋት ምን እንደሆነ ገልጿል። ተከታዮቹ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯል። አዎን፣ የአምላክ መንግሥት ወይም መስተዳድር አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል።—ማቴዎስ 6:10

ይህ መንግሥት የሚያመጣቸውን አስደናቂ ለውጦች በተመለከተ አምላክ “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” ብሏል። (ራእይ 21:5) ታዲያ አምላክ ይህችን ምድር በሌላ አዲስ ምድር ይተካታል ማለት ነው? አይደለም፣ ምክንያቱም ምድር ምንም ዓይነት የአፈጣጠር እንከን የለባትም። ስለዚህ አምላክ “ምድርን እያጠፉ ያሉትን” ይኸውም በምድር ላይ ለደረሰው ቀውስ ተጠያቂ የሆኑትን በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ ያጠፋቸዋል። በምትኩ አምላክ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” እንዲኖሩ ያደርጋል፤ በሌላ አባባል በሰማይ የተቋቋመው የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ የሚኖረውን አዲስ ማኅበረሰብ ያስተዳድራል።—ራእይ 21:1

አምላክ፣ የሰው ልጆች በምድር ሥነ ምህዳር ላይ ያስከተሉትን ቀውስ ለማስተካከል እርምጃ ይወስዳል። መዝሙራዊው፣ አምላክ ምን እንደሚያደርግ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ሲገልጽ “ምድርን ትጐበኛለህ፤ ታጠጣለህም፤ እጅግ ታበለጽጋታለህም” ብሏል። ምድር የተስተካከለ የአየር ንብረት ስለሚኖራት፣ በተለይ ደግሞ አምላክ ስለሚባርካት የተትረፈረፈ ምግብ የምታፈራ ገነት ትሆናለች።—መዝሙር 65:9-13

የሕንድ መንፈሳዊ መሪ የነበሩት ሞሃንዳስ ጋንዲ “ምድር የእያንዳንዱን ሰው ፍላጎት ማርካት ብትችልም የስግብግቦችን ምኞት ሁሉ የማርካት አቅም የላትም” ብለው መናገራቸውን ጸሐፊያቸው ፒያሬላል ገልጸዋል። የአምላክ መንግሥት ለምድር ችግሮች ዋነኛ መንስኤ የሆነውን ነገር ያስተካክላል፤ ይኸውም የሰዎች ልብ እንዲለወጥ ያደርጋል። ነቢዩ ኢሳይያስ፣ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሚኖሩ ሰዎች በሌሎች ሰዎችም ሆነ በምድር ላይ ‘ጉዳት ወይም ጥፋት እንደማያደርሱ’ ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 11:9) እንዲያውም በዛሬው ጊዜም እንኳ የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክ ያወጣቸውን ላቅ ያሉ መሥፈርቶች እየተማሩ ነው። እነዚህ ሰዎች ለአምላክና ለሌሎች ሰዎች ፍቅር እንዲኖራቸው፣ አመስጋኝ እንዲሆኑ፣ አካባቢያቸውን እንዲንከባከቡ፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚስማማ ሕይወት እንዲመሩ ትምህርት እየተሰጣቸው ነው። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለሚኖረው ሕይወት ራሳቸውን እያዘጋጁ ነው።—መክብብ 12:13፤ ማቴዎስ 22:37-39፤ ቆላስይስ 3:15

እንዲህ ያለችው ውብ ምድር በሥነ ምህዳር ቀውስ የተነሳ አትጠፋም

በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሰፈረው የፍጥረት ዘገባ የሚደመደመው “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ” በሚሉት ቃላት ነው። (ዘፍጥረት 1:31) በእርግጥም እንዲህ ያለችው ውብ ምድር በሥነ ምህዳር ቀውስ የተነሳ አትጠፋም። የምድር የወደፊት ዕጣ በአፍቃሪው ፈጣሪያችን በይሖዋ አምላክ እጅ መሆኑን ማወቃችን ያጽናናናል። “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት አምላክ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 37:29) አንተም በምድር ላይ ለዘላለም ከሚኖሩት “ጻድቃን” መካከል አንዱ እንድትሆን ምኞታችን ነው።

^ አን.3 ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከመክብብ 1:4 ላይ የተወሰደ።