በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሕይወት ታሪክ

ከድክመቴ ጥንካሬ ማግኘት

ከድክመቴ ጥንካሬ ማግኘት

ክብደቴ 29 ኪሎ ግራም ሲሆን የምንቀሳቀሰው በተሽከርካሪ ወንበር ነው፤ ኮስማና የሆነ ሰውነቴን ያየ ሰው ጠንካራ ናት ብሎ ሊያስብ አይችልም። ይሁን እንጂ ሰውነቴ እየተዳከመ ቢሄድም መንፈሴ ጠንካራ መሆኑ ብርታት ሰጥቶኛል። ጥንካሬና ድካም በሕይወቴ ላይ ስላሳደሩት ተጽዕኖ እስቲ ልግለጽላችሁ።

በአራት ዓመቴ

የልጅነት ዘመኔን ሳስብ በደቡብ ፈረንሳይ በሚገኝ ገጠራማ አካባቢ ከወላጆቼ ጋር ያሳለፍኩት አስደሳች ጊዜ ትዝ ይለኛል። አባቴ ዥዋዥዌ መጫወቻ ሠርቶልኝ የነበረ ሲሆን በአትክልት ቦታው መሯሯጥ ደስ ይለኝ ነበር። በ1966 የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን መጡና ከአባቴ ጋር ረጅም ውይይት አደረጉ። በሰባት ወር ጊዜ ውስጥ አባቴ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። እናቴም ብዙም ሳይቆይ የእሱን ፈለግ ተከትላ የይሖዋ ምሥክር ሆነች፤ በመሆኑም ያደግሁት ደስተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው።

አሁን ያሉብኝ ችግሮች የጀመሩት የወላጆቼ የትውልድ አገር ወደሆነችው ወደ ስፔን እንደተመለስን አካባቢ ነበር። እጆቼና ቁርጭምጭሚቶቼ ላይ የሚወጋ ሕመም ይሰማኝ ጀመር። ለሁለት ዓመታት ብዙ ሐኪሞች ካዩኝ በኋላ አንድ የታወቀ የሩማቶሎጂ ሐኪም ጋ ሄድን፤ እሱም በአዘኔታ ስሜት “ዘገያችሁ” አለን። እናቴ ማልቀስ ጀመረች። ሐኪሙ፣ በሰውነቴ ውስጥ ያሉት በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ሌሎች ሕዋሳትን እያጠቁ እንደሆነና በዚህም የተነሳ በልጆች ላይ የሚከሰት ጁቬኒል ፖሊአርትራይተስ * የተባለ በሽታ እንደያዘኝ ሲናገር ሰማሁ። በወቅቱ የአሥር ዓመት ልጅ ስለነበርኩ ሐኪሙ የተናገረው ነገር ብዙም አልገባኝም፤ ጥሩ ዜና እንዳልሆነ ግን ተረድቼ ነበር።

ሐኪሙ፣ በልጆች የሕክምና ተቋም ውስጥ እየኖርኩ ሕክምና እንድከታተል ሐሳብ አቀረበ። እዚያ ደርሼ ደስ የማይል መልክ ያለውን ሕንፃ ስመለከት ፍርሃት ለቀቀብኝ። ሥርዓቱ ጥብቅ ነበር፤ ሴት መነኮሳት ፀጉሬን ቆርጠው የሚያስጠላ ዩኒፎርም አለበሱኝ። ‘በዚህ ዓይነት ሁኔታ እንዴት ነው የምዘልቀው?’ ብዬ በማሰብ አለቀስኩ።

ይሖዋ እውን ሆነልኝ

ወላጆቼ ይሖዋን እንዳገለግል አስተምረውኝ ስለነበረ በመኖሪያ ተቋሙ በሚደረጉት የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ ለመካፈል ፈቃደኛ አልሆንኩም። መነኮሳቱ ለምን እምቢ እንዳልኩ መረዳት ከበዳቸው። በመሆኑም ይሖዋ እንዳይተወኝ ተማጸንኩት፤ እሱም ወዲያውኑ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት በክንዶቹ እቅፍ ያደረገኝ ያህል ተሰማኝ።

ወላጆቼ ቅዳሜ ቅዳሜ ለአጭር ጊዜ እየመጡ እንዲጠይቁኝ ተፈቅዶላቸው ነበር። እምነቴ ጠንካራ እንዲሆን የሚረዱኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ይዘውልኝ መጡ። በተቋሙ ውስጥ ያሉት ልጆች የራሳቸው መጻሕፍት እንዲኖሯቸው ባይፈቀድላቸውም መነኮሳቱ ጽሑፎቹን ከመጽሐፍ ቅዱሴ ጋር እንዳስቀምጥ  ፈቀዱልኝ፤ እኔም በየቀኑ አነብባቸው ነበር። እንዲሁም ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ ማንም ሰው ሳይታመም ለዘላለም እንደሚኖር ያለኝን ተስፋ ለሌሎች ልጆች እነግራቸው ነበር። (ራእይ 21:3, 4) አንዳንድ ጊዜ ሐዘንና የብቸኝነት ስሜት ቢሰማኝም በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነትና መተማመን እየተጠናከረ በመሄዱ ደስ አለኝ።

ለእኔ ረጅም ጊዜ ሆነው የታዩኝ ስድስት ወራት ሲያበቁ ሐኪሞቹ ወደ ቤት ላኩኝ። ሕመሙ ባይሻለኝም ተመልሼ ከወላጆቼ ጋር መሆን በመቻሌ ደስ አለኝ። መገጣጠሚያዎቼ አካባቢ ያለው ቅርጽ ይበልጥ እየተበላሸ የሄደ ሲሆን የሚሰማኝ ሥቃይም ጨመረ። አቅመ ቢስ እንደሆንኩ ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ገባሁ። ያም ሆኖ በ14 ዓመቴ የተጠመቅሁ ሲሆን በሰማይ ያለውን አባቴን የቻልኩትን ያህል ለማገልገል ቆርጬ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋን ያማረርኩባቸው ወቅቶች ነበሩ። “ይህ በእኔ ላይ የደረሰው ለምንድን ነው? እባክህ ፈውሰኝ። ምን ያህል እየተሠቃየሁ እንዳለሁ አታይም?” እያልኩ እጸልይ ነበር።

የጉርምስና ዕድሜ ለእኔ ከባድ ነበር። ከሕመሜ እንደማልድን አምኜ መቀበል ነበረብኝ። ሳልፈልግ ራሴን ከጓደኞቼ ጋር አወዳድር ነበር፤ እነሱ በጣም ጤናማና በሕይወታቸውም ደስተኞች ናቸው። በዚህም የተነሳ የዝቅተኝነት ስሜት ስለሚሰማኝ ከሰዎች ጋር ስሆን እሸማቀቅ ነበር። ይሁን እንጂ ቤተሰቤና ጓደኞቼ ደግፈውኛል። ለምሳሌ በ20 ዓመት የምትበልጠኝ አሊሲያ ያደረገችልኝን ነገር ፈጽሞ አልረሳውም፤ ለእኔ እውነተኛ ጓደኛ ሆናልኛለች። አሊሲያ፣ በራሴ ችግሮች ከመቆዘም ይልቅ ስለ ሌሎች ከልብ የማስብ እንድሆን ረድታኛለች፤ ይህም ሕመሜ ላይ እንዳላተኩር አድርጎኛል።

ሕይወቴ ትርጉም ያለው እንዲሆን መጣር

ዕድሜዬ 18 ዓመት ሲሞላ ሕመሙ ክፉኛ አገረሸብኝ፤ እንዲያውም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንኳ ያደክመኝ ጀመር። ይሁን እንጂ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን አጠና ነበር። የኢዮብና የመዝሙር መጻሕፍት፣ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ አምላክ እንክብካቤ የሚያደርግልን በዋነኝነት በመንፈሳዊ እንጂ በአካላዊ ሁኔታ አለመሆኑን እንድረዳ አስቻሉኝ። አዘውትሬ መጸለዬ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ እና ‘ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ እንዳገኝ ረድቶኛል።—2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ሃያ ሁለት ዓመት ሲሆነኝ መንቀሳቀስ የምችለው በተሽከርካሪ ወንበር ብቻ ሆነ፤ ይህን አምኖ መቀበል ከብዶኝ ነበር። ሰዎች የሚሰጡኝ ቦታ ይቀንሳል እንዲሁም ካለተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ የማትችል አቅመ ቢስ ሴት አድርገው ይቆጥሩኛል የሚለው ሐሳብ አስፈራኝ። ይሁን እንጂ ተሽከርካሪ ወንበሩ በተወሰነ መጠን ራሴን ችዬ እንድንቀሳቀስ የረዳኝ ሲሆን መጥፎ ይሆናል ብዬ ያሰብኩት ነገር ለበጎ ሆነልኝ። ኢዛቤል የምትባል አንዲት ጓደኛዬ ለአንድ ወር ያህል ከእሷ ጋር በስብከቱ ሥራ 60 ሰዓት ለማሳለፍ ግብ እንዳወጣ ሐሳብ አቀረበችልኝ።

መጀመሪያ ላይ ሐሳቡ የማይሆን መስሎኝ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋን እንዲረዳኝ ጠየቅሁት፤ እንዲሁም ቤተሰቤና ጓደኞቼ ባደረጉልኝ ድጋፍ ተሳካልኝ። ወሩን በሥራ ተጠምጄ ስላሳለፍኩ ጊዜው ሳላስበው ሄደ፤ በተጨማሪም የፍርሃትና የመሸማቀቅ ስሜቴ እንደጠፋ ተረዳሁ። በዚህ በጣም በመደሰቴ በ1996 የዘወትር አቅኚ በመሆን በየወሩ በአገልግሎት ረዘም ያለ ሰዓት ለማሳለፍ ወሰንኩ። ይህም እስካሁን ካደረግኳቸው ጥሩ ውሳኔዎች አንዱ ሲሆን ወደ አምላክ ይበልጥ እንድቀርብና ሰውነቴም እንዲጠነክር ረድቶኛል። በአገልግሎት መካፈሌ እምነቴን ለብዙ ሰዎች የመንገርና አንዳንዶቹም የአምላክ ወዳጆች እንዲሆኑ የመርዳት አጋጣሚ አስገኝቶልኛል።

ይሖዋ ደግፎ ይዞኛል

በ2001 ክረምት ላይ በደረሰብኝ ከባድ የመኪና አደጋ የተነሳ ሁለቱም እግሮቼ ተሰበሩ። ሆስፒታል ውስጥ አልጋ ላይ ተኝቼ በሥቃይ ላይ እያለሁ ድምፄን ሳላሰማ “እባክህ ይሖዋ አትተወኝ!” ብዬ አጥብቄ ጸለይኩ። በዚህ ጊዜ አጠገቤ የተኛች ሌላ ሴት “የይሖዋ ምሥክር ነሽ?” ብላ ጠየቀችኝ። እኔም ቃል ለማውጣት ኃይል ስላልነበረኝ ራሴን በመነቅነቅ አዎንታዬን ገለጽኩ። “የይሖዋ ምሥክሮችን አውቃችኋለሁ! መጽሔቶቻችሁን ብዙ ጊዜ አነባለሁ” አለችኝ። ይህን ስሰማ በጣም ተጽናናሁ። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኜም እንኳ ስለ ይሖዋ መመሥከር ቻልኩ። ይህ ለእኔ ትልቅ ክብር ነው!

ትንሽ ሳገግም የበለጠ ለማገልገል ወሰንኩ። ሁለቱም እግሮቼ እንደታሸጉ እናቴ በሆስፒታሉ ክፍሎች ውስጥ በተሽከርካሪ ወንበር እየገፋች ታዘዋውረኝ ነበር። በየቀኑ ጥቂት ሕመምተኞችን ሄደን በመጠየቅ ስለ ጤንነታቸው ካነጋገርናቸው በኋላ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን እንዲያነቡ እንተውላቸዋለን። እንዲህ ማድረግ ለእኔ በጣም አድካሚ ቢሆንም ይሖዋ አስፈላጊውን ጥንካሬ ሰጥቶኛል።

በ2003 ከወላጆቼ ጋር

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ቁርጥማቱና ሥቃዩ የጨመረብኝ ሲሆን አባቴን በሞት ሳጣ ደግሞ ሐዘኑ ተደራረበብኝ። ያም ሆኖ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት አደርጋለሁ። እንዴት? በሚቻልበት ጊዜ ሁሉ ከጓደኞቼና ከዘመዶቼ ጋር ለመሆን ጥረት  አደርጋለሁ፤ ይህም ችግሮቼን እንድረሳ ረድቶኛል። ብቻዬን በምሆንበት ጊዜ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን አነብባለሁ ወይም አጠናለሁ፤ አሊያም ለሌሎች በስልክ እሰብካለሁ።

ብዙ ጊዜ ዓይኖቼን እጨፍንና “መስኮቴን” ከፍቼ ማለትም በዓይነ ሕሊናዬ አምላክ ቃል የገባውን አዲስ ዓለም ለመመልከት እሞክራለሁ

በተጨማሪም ቀላል በሚመስሉ ነገሮች ለመደሰት ጥረት አደርጋለሁ፤ ለምሳሌ ያህል፣ ነፋሱ ፊቴ ላይ ሽው ሲልብኝ ወይም የአበቦች መዓዛ ሲያውደኝ ደስ ይለኛል። እነዚህ ነገሮች አመስጋኝ እንድሆን ያደርጉኛል። መሳቅ መቀለድም አስገራሚ ወጤት አለው። አንድ ቀን ለስብከት ወጥቼ ሳለሁ ተሽከርካሪ ወንበሬን እየገፋችልኝ የነበረችው ጓደኛዬ ማስታወሻ ለመጻፍ ቆም አለች። መንገዱ ቁልቁለት ስለነበር እየተንደረደርኩ ወርጄ ከቆመ መኪና ጋር ተላተምኩ። በዚህ ጊዜ ሁለታችንም ደነገጥን፤ ነገር ግን ምንም የከፋ ጉዳት እንዳልደረሰ ስናይ ከት ብለን ሳቅን።

አሁን ማድረግ የማልችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እነዚህን ነገሮች በይደር ያስቀመጥኳቸው ምኞቶቼ እንደሆኑ አድርጌ አስባለሁ። ብዙ ጊዜ ዓይኖቼን እጨፍንና “መስኮቴን” ከፍቼ ማለትም በዓይነ ሕሊናዬ አምላክ ቃል የገባውን አዲስ ዓለም ለመመልከት እሞክራለሁ። (2 ጴጥሮስ 3:13) ጤናማ ሆኜ፣ እንደ ልቤ ስራመድና በሕይወቴ ሙሉ በሙሉ ደስተኛ ስሆን ይታየኛል። “እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ በርታ” የሚሉት የንጉሥ ዳዊት ቃላት ምንጊዜም በልቤ አሉ። (መዝሙር 27:14) ሰውነቴ እያደር እየደከመ ቢሄድም ይሖዋ ጥንካሬ ሰጥቶኛል። ከድካሜ ብርታት ማግኘቴን እቀጥላለሁ።

^ አን.6 ይህ በሽታ ልጆችን የሚያጠቃ ከባድ የአርትራይተስ በሽታ ነው። የሰውነት በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ጤናማ የሆኑ ሕብረ ሕዋሳትን ስለሚያጠቁ በመገጣጠሚያዎች ላይ ሥቃይና እብጠት ያስከትላል።