በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ፦ ከጭፍን ጥላቻ የጸዳ ዓለም—ይመጣ ይሆን?

ጭፍን ጥላቻ—ዓለም አቀፍ ችግር

ጭፍን ጥላቻ—ዓለም አቀፍ ችግር

ከኮሪያዊ ቤተሰብ የተወለደው አሜሪካዊው ጆናታን ከልጅነቱ ጀምሮ ጭፍን ጥላቻ ይደርስበት ነበር። እያደገ ሲሄድ ግን በመልኩ ወይም በዘሩ ምክንያት የጭፍን ጥላቻ ሰለባ የማይሆንበትን ቦታ ማፈላለግ ጀመረ። በኋላም ጆናታን በሰሜናዊ አላስካ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ አንድ ከተማ የሕክምና ዶክተር ሆነ፤ ብርዳማ በሆነው በዚህ አካባቢ የሚኖሩ አብዛኞቹ ታካሚዎች ከእሱ ጋር የሚመሳሰል የፊት ገጽታ ስላላቸው ከአካባቢው ቅዝቃዜ ከባሰው ጭፍን ጥላቻ እንደሚገላገል ተስፋ አድርጎ ነበር።

ይሁንና ለአንዲት የ25 ዓመት ሴት የሕክምና እርዳታ በሰጠበት ጊዜ ይህ ተስፋው በንኖ ጠፋ። ይህች በሽተኛ ከኮማ ነቅታ የጆናታንን ፊት ስታይ ለኮርያውያን ያላትን ሥር የሰደደ ጥላቻ የሚያሳይ የንቀት አነጋገር ተናገረች። ይህ አሳዛኝ አጋጣሚ ጆናታን የእሱ ዓይነት የፊት ገጽታ ያላቸውን ሰዎች ፈልጎ ለመኖር ያደረገው ጥረት የጭፍን ጥላቻ ሰለባ ከመሆን እንዳላዳነው አስገንዝቦታል።

የጆናታን ተሞክሮ አንድን አሳዛኝ እውነታ አጉልቶ የሚያሳይ ነው። ጭፍን ጥላቻ ያልዳሰሰው የምድር ክፍል የለም። ሰዎች ባሉበት ቦታ ሁሉ ጭፍን ጥላቻ አለ ማለት ይቻላል።

ጭፍን ጥላቻ የተስፋፋ ቢሆንም እንዲህ ያለውን ድርጊት የሚያወግዙ ብዙ ሰዎች አሉ። ነገሩ በእርግጥ ግራ የሚያጋባ ነው።  በጣም የተጠላ ነገር ይህን ያህል ሊስፋፋ የቻለው ለምንድን ነው? በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጭፍን ጥላቻን የሚቃወሙ ብዙ ሰዎች ጥላቻው በውስጣቸው እንዳለ አያውቁም። እንዲህ ያለው ጥላቻ በአንተስ ውስጥ ይኖር ይሆን? ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ?

በግለሰብ ደረጃ ራስን መመርመር

ተቀበልነውም አልተቀበልነው፣ ጭፍን ጥላቻ በተወሰነ መጠንም እንኳ በልባችን ውስጥ መኖሩን ለይቶ ማወቅ አስቸጋሪ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ” ወይም አታላይ እንደሆነ ይናገራል። (ኤርምያስ 17:9) በመሆኑም ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር ተቻችለን እንደምንኖር በማሰብ ራሳችንን ልናታልል እንችላለን። ወይም ደግሞ ስለተወሰኑ የሰዎች ቡድኖች አሉታዊ አመለካከት የያዝነው በቂ ምክንያት ስላለን እንደሆነ በማሰብ ራሳችንን ለማሳመን እንሞክር ይሆናል።

እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ ምን ታስባለህ?

ስውር የሆነ ጭፍን ጥላቻ በውስጣችን መኖሩን ማወቅ ቀላል እንዳልሆነ በምሳሌ ለማስረዳት ቀጥሎ የቀረበውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት፦ ምሽት ላይ ብቻህን በእግር እየሄድክ ነው እንበል። ከዚህ በፊት አይተሃቸው የማታውቃቸው ሁለት ወጣቶች ወደ አንተ እየቀረቡ ነው። ፈርጣማ ሰውነት ያላቸው ሲሆን አንደኛው ወጣት በእጁ የሆነ ነገር የያዘ ይመስላል።

እነዚህ ወጣቶች ጥቃት ሊሰነዝሩብኝ ነው ብለህ ታስባለህ? እርግጥ ነው፣ ከዚህ በፊት ካሳለፍከው ተሞክሮ በመነሳት ጠንቃቃ መሆን እንዳለብህ ይሰማህ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ያሳለፍከው ተሞክሮ በእርግጥ እነዚህ ወጣቶች አደገኛ ናቸው የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ በቂ ነው? ይበልጥ የሚያሳስበው ጥያቄ ግን ‘እነዚህ ወጣቶች ከየትኛው ዘር ወይም ጎሣ ናቸው ብለህ አሰብክ?’ የሚለው ነው። ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ በልብህ ውስጥ ያለውን ነገር የሚገልጥ ሊሆን ይችላል። የሰጠኸው መልስ በትንሹም ቢሆን የጭፍን ጥላቻ እርሾ በውስጥህ እንዳለ ሊያመለክት ይችላል።

ለራሳችን ሐቀኞች ከሆንን፣ ሁላችንም መጠኑ ይለያይ እንጂ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ጭፍን ጥላቻ በልባችን ጓዳ ተደብቆ እንደሚገኝ አምነን እንቀበላለን። መጽሐፍ ቅዱስም “ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል” በማለት በጣም የተለመደውን ዓይነት መድልዎ ይገልጻል። (1 ሳሙኤል 16:7) ሁላችንም ፊትን አይቶ የመፍረድ አባዜ ተጠናውቶናል፤ እንዲያውም ብዙውን ጊዜ መጥፎ ውጤት ያስከትልብናል። ታዲያ ጭፍን ጥላቻን ማሸነፍ ወይም ከናካቴው ማስወገድ የምንችልበት ተስፋ ይኖረን ይሆን? ደግሞስ ከጭፍን ጥላቻ የጸዳ ዓለም የምናይበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?