በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ

“ከልጄ ጋር ያለምንም ችግር እንነጋገር ነበር። አሁን ግን፣ 16 ዓመት የሆነው ሲሆን እኔም ሆንኩ ባለቤቴ የሚያስበውን ነገር ማወቅ አስቸጋሪ ሆኖብናል። ብቻውን መኝታ ክፍሉ ውስጥ መሆንን የሚመርጥ ከመሆኑም በላይ ሊያነጋግረን ፈቃደኛ አይደለም!”—ሚርያም፣ ሜክሲኮ

“በአንድ ወቅት፣ ልጆቼ የምነግራቸውን ሁሉ በጉጉት ያዳምጡና እሺ ብለው ይቀበሉ ነበር። አሁን ግን በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሲገቡ ሁኔታቸውን እንደማልረዳላቸው አድርገው ማሰብ ጀመሩ።”—ስካት፣ አውስትራሊያ

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ካለህ ከላይ የተጠቀሱት ወላጆች የተናገሩትን መረዳት አያዳግትህም። ልጅህ ከመጎርመሱ በፊት ከእሱ ጋር መነጋገር በሁለቱም አቅጣጫ መኪኖች እንደልብ ከሚሄዱበት አውራ መንገድ ጋር ይመሳሰል ነበር ለማለት ይቻላል። አሁን ግን መንገዱ የተዘጋ ይመስላል። በጣሊያን የምትኖር አንጀላ የተባለች እናት እንዲህ ትላለች:- “ልጄ ትንሽ ሳለ በጥያቄዎች ያጣድፈኝ ነበር። አሁን ግን ጭውውቱን የምጀምረው እኔው ሆኛለሁ። እንዲህ ካላደረግሁ ምንም የረባ ነገር ሳንነጋገር ቀናት ሊያልፉ ይችላሉ።”

አንጀላ እንደገጠማት ሁሉ አንተም በአንድ ወቅት ተጫዋች የነበረው ልጅህ መጎርመስ ሲጀምር ዝምተኛና ባሕርይው ተለዋዋጭ ሆኖብህ ይሆናል። ጭውውት ለመጀመር አስበህ ለምታነሳቸው ጥያቄዎች አጭር መልስ ይሰጥህ ይሆናል። ልጅህን “ውሎ እንዴት ነበር?” ስትለው “ደህና” ይልህ ይሆናል። ወይም ደግሞ ሴት ልጅህን “ዛሬ በትምህርት ቤት ምን አዲስ ነገር ነበር?” ብለህ ስትጠይቃት ትከሻዋን ነቅነቅ አድርጋ “ምንም” ትልህ ይሆናል። ውይይቱን ለማርዘም በማሰብ “ለምን በደንብ አትነግሪኝም?” ብትላት ደግሞ ጭራሹኑ ዝም ልትልህ ትችላለች።

እርግጥ ነው፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ልጆች የሚያሳስባቸውን ነገር በግልጽ መናገር አይቸግራቸውም። ይሁንና የሚናገሩት ነገር ለወላጆቻቸው የማይጥም ሊሆን ይችላል። በናይጄሪያ የምትገኘው ኤድና የተባለች እናት እንዲህ ብላለች:- “ልጄ አንድ ነገር እንድትሠራ ሳዛት አብዛኛውን ጊዜ ‘እስቲ ተዪኝ’ ትለኛለች።” በሜክሲኮ የሚኖረው ራሞን የ16 ዓመት ልጁ ተመሳሳይ ነገር እንደሚያደርግ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ሳንጨቃጨቅ የዋልንበት ቀን የለም ለማለት ይቻላል። አንድ ነገር እንዲሠራ ባዘዝኩት ቁጥር የተጠየቀውን ነገር ላለመፈጸም ሰበብ ይደረድራል።”

ለሚቀርብለት ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆነ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኝ ልጅ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ መሞከር የወላጆችን ትዕግሥት ይፈትን ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል” ይላል። (ምሳሌ 15:22) አና የተባለች በሩሲያ የምትገኝ ነጠላ ወላጅ “ልጄ ስለምን እንደሚያስብ ሳላውቅ ስቀር በጣም ከመበሳጨቴ የተነሳ ጩኺ ጩኺ ይለኛል” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ሆኖ ሳለ ወላጆች በወጣትነት ዕድሜ ላይ ካሉ ልጆቻቸው ጋር መግባባት የሚቸግራቸው ለምንድን ነው?

ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዳይኖር የሚያደርጉ እንቅፋቶችን ለይቶ ማወቅ

የሐሳብ ልውውጥ ሲባል መነጋገር ብቻ ማለት አይደለም። ኢየሱስ “ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራል” ብሏል። (ሉቃስ 6:45) በመሆኑም ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ፣ ከሌሎች ለመማርና ማንነታችንን ለማሳወቅ ይረዳናል። በጉርምስና ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች በልባቸው ውስጥ ያለውን ነገር ለሌሎች መናገር ከባድ ይሆንባቸዋል፤ በመሆኑም ተጫዋች የነበረ ልጅ እንኳ ወደዚህ የዕድሜ ክልል ሲደርስ ዝምተኛና ዓይን አፋር ሊሆን ይችላል። በጉርምስና ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች፣ መድረክ ላይ እንዳለ ተዋናይ የሚያደርጉትንና የሚናገሩትን ነገር በሙሉ ሰዎች እንደሚከታተሏቸው አድርገው እንደሚያስቡ ምሑራን ይገልጻሉ። በመሆኑም ስለ ራሳቸው ከሚገባው በላይ የሚጨነቁ ልጆች ይከታተሉናል ብለው ከሚያስቧቸው ተመልካቾች ለመደበቅ ሲሉ በመድረኩ መጋረጃ ሊሸፈኑ ማለትም ወላጆች በቀላሉ ሊገቡበት የማይችሉ የራሳቸው ዓለም ይፈጥሩ ይሆናል።

የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ እንቅፋት የሚሆነው ሌላው ነገር ደግሞ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ራሳቸውን ለመቻል ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ነው። ራስን የመቻል ፍላጎት የእድገት አንዱ ገጽታ በመሆኑ ልጃችሁ እንዲህ ዓይነቱ ፍላጎት እንዳይኖረው ማድረግ አትችሉም። ይህ ሲባል ግን ልጃችሁ ራሱን ችሎ ከቤት መውጣት ይችላል ማለት አይደለም። ልጃችሁ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ የእናንተን እርዳታ ይፈልጋል። ራስን የመቻል ሂደት የሚጀምረው አንድ ሰው አዋቂ ከመሆኑ ከዓመታት በፊት ነው። ራስን መቻል የጉልምስና ሂደት አንዱ ክፍል በመሆኑ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ በርካታ ልጆች የሚያሳስባቸውን ነገር ለሌሎች ከመናገራቸው በፊት ብቻቸውን ሆነው በጉዳዩ ላይ ማሰብ ይፈልጋሉ።

እርግጥ ነው፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ሚስጢሮቻቸውን ከጓደኞቻቸው አይደብቁ ይሆናል። በሜክሲኮ የምትገኝ ጄሲካ የተባለች እናት ያጋጠማት ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። እንዲህ ትላለች:- “ልጄ፣ ትንሽ ሳለች ያጋጠማትን ችግር ምንም ሳታስቀር ትነግረኝ ነበር። አሁን ግን የሆነ ነገር ሲያጋጥማት የምትሄደው ወደ ጓደኞቿ ነው።” አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ልጅህ ከወላጅነት “እንደሰረዘህ” ሆኖ አይሰማህ። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የወላጆቻቸው እርዳታ እንደማያስፈልጋቸው ቢናገሩም እንኳ ከጓደኞቻቸው ይልቅ የወላጆቻቸውን ምክር ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ ጥናቶች ያሳያሉ። ታዲያ የሐሳብ ግንኙነት መስመሩ ክፍት ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

ስኬታማ ለመሆን ቁልፉ—እንቅፋቶችን ማስወገድ ነው

ረጅም በሆነና ቀጥ ባለ አውራ ጎዳና ላይ መኪና እያሽከረከርክ ነው እንበል። የመኪናህን መሪ እምብዛም ማስተካከል ሳይኖርብህ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘሃል። ሆኖም በድንገት ኃይለኛ ኩርባ አጋጠመህ። በዚህ ጊዜ መኪናህ መንገድ ስቶ እንዳይወጣ ለማድረግ መሪውን ከማስተካከል የተሻለ አማራጭ አይኖርህም። ልጅህ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ሲደርስ የሚያጋጥምህም ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። ልጅህን በምትይዝበት መንገድ ላይ ለረጅም ዓመታት እምብዛም ማስተካከያ ማድረግ አላስፈለገህ ይሆናል። አሁን ግን በልጅህ ሕይወት ውስጥ ከኃይለኛ ኩርባ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ስለተከሰተ ‘መሪህን ማስተካከል’ ማለትም ከእሱ ጋር የሐሳብ ልውውጥ በምታደርግበት መንገድ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልግሃል። ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ።

‘ልጄ ሊያናግረኝ በሚፈልግበት ጊዜ እሱን ለመስማት ፈቃደኛ ነኝ?’ መጽሐፍ ቅዱስ “የወርቅ እንኮይ በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜው ቃል እንዲሁ ነው” ይላል። (ምሳሌ 25:11 የ1954 ትርጉም) ይህ ጥቅስ፣ የጊዜ ጉዳይ በቁም ነገር ሊታሰብበት እንደሚገባ በግልጽ ያሳያል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ገበሬ የመከር ወቅትን ከትክክለኛው ጊዜ አስቀድሞ ወይም ዘግይቶ እንዲጀምር ማድረግ አይችልም። ማድረግ የሚችለው ነገር ቢኖር ወቅቱ ሲደርስ ጊዜውን በጥሩ ሁኔታ መጠቀም ነው። በተመሳሳይም በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጅህ ሐሳቡን ለመግለጽ የሚፈልግበት ጊዜ ይኖረው ይሆናል። ይህንን አጋጣሚ ተጠቀምበት። በአውስትራሊያ የምትገኝ ፍራንሲስ የተባለች ነጠላ ወላጅ እንዲህ ትላለች:- “ልጄ አብዛኛውን ጊዜ ከመሸ በኋላ ወደ መኝታ ቤቴ የምትመጣ ሲሆን አንዳንዴም ለአንድ ሰዓት ያህል ታዋራኛለች። ቶሎ መተኛት ስለምፈልግ ይህ ለእኔ ቀላል አልነበረም። ይሁንና በእነዚህ ጊዜያት ስለ ብዙ ነገሮች ተጫውተናል።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክር:- በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጅህ ሐሳቡን ለመግለጽ ፈቃደኛ በማይሆንበት ጊዜ አንድ ነገር አብራችሁ ለመሥራት ሞክሩ። ምናልባት በእግር ወይም በመኪና መንሸራሸር፣ መጫወት ወይም ደግሞ የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራት ትችሉ ይሆናል። እንዲህ ያለውን ጊዜ አብራችሁ ማሳለፋችሁ ልጃችሁ ስሜቱን እንዲገልጽ ሊገፋፋው ይችላል።

‘ልጄ ከሚናገረው ሐሳብ በስተጀርባ ያለውን ነገር ለማስተዋል እሞክራለሁ?’ ኢዮብ 12:11 “ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ፣ ጆሮ ቃላትን አይለይምን?” ይላል። ልጅህ የሚናገረውን ነገር ‘ለመለየት’ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ እነሱ ብቻ ትክክል እንደሆኑ አድርገው ማውራት ይቀናቸዋል። ለአብነት ያህል፣ ልጅህ “ሁልጊዜ እንደ ሕፃን ትመለከተኛለህ!” ወይም “አንድም ቀን እኔ የምለውን ሰምተኸኝ አታውቅም!” ይል ይሆናል። “ሁልጊዜ” እና “አንድም ቀን” የሚሉትን ቃላት አንስተህ ከልጅህ ጋር ክርክር ከመግጠም ይልቅ ለማለት የፈለገውን ነገር ለመረዳት መጣር ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል፣ ልጅህ “ሁልጊዜ እንደ ሕፃን ትመለከተኛለህ” ሲል “እንደማትተማመንብኝ ይሰማኛል” እንዲሁም “አንድም ቀን እኔ የምለውን ሰምተኸኝ አታውቅም” ሲል ደግሞ “ምን እንደሚሰማኝ ልነግርህ እፈልጋለሁ” ማለቱ ሊሆን ይችላል። ልጅህ ከሚናገረው ሐሳብ በስተጀርባ ያለውን ነገር ለማስተዋል ሞክር።

እንዲህ ለማድረግ ሞክር:- በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅህ በኃይለ ቃል ሲናገር እንደሚከተለው ለማለት ትችል ይሆናል:- “በጣም እንደተበሳጨህ ይገባኛል፤ የምትለውን በደንብ ለመስማት እፈልጋለሁ። እንደ ልጅ እንደምመለከትህ ሆኖ የሚሰማህ ለምን እንደሆነ እስቲ ንገረኝ።” ከዚያም ንግግሩን ሳታቋርጠው በጥሞና አዳምጠው።

‘በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ልጄን ሐሳቡን እንዲናገር በማስገደድ ሳይታወቀኝ በመካከላችን ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዳይኖር እያደረግሁ ይሆን?’

መጽሐፍ ቅዱስ “የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉ በሰላም ይዘራል” ይላል። (ያዕቆብ 3:18) በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጅህ ሐሳቡን ለመግለጽ እንዲገፋፋ በንግግርህም ሆነ በባሕርይህ ‘ሰላማዊ’ ሁኔታ ለመፍጠር መጣር ይኖርብሃል። የልጅህ ጠበቃ መሆንህን አትርሳ። ስለሆነም ስለ አንድ ጉዳይ በምትወያዩበት ወቅት የአንድን ምሥክር ቃል ዋጋ ለማሳጣት ሲል መስቀለኛ ጥያቄዎች እንደሚጠይቅ አቃቤ ሕግ መሆን የለብህም። በኮሪያ የሚኖር አን የተባለ አባት እንዲህ ብሏል:- “አንድ ጥበበኛ አባት ‘መቼ ይሆን የምታድገው?’ ወይም ‘ቢነግሩህ ቢነግሩህ አይገባህም!’ እንደሚሉት ያሉ አባባሎች አይጠቀምም። በዚህ ረገድ ብዙ ስህተት ከፈጸምኩ በኋላ የምናገርበት መንገድ ብቻ ሳይሆን የምናገረውም ነገር ልጆቼን እንደሚያበሳጫቸው ተገነዘብኩ።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክር:- ልጅህ ለሚጠየቀው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር የተለየ ዓይነት አቀራረብ ለመጠቀም ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ ሴት ልጅህን ውሎዋ እንዴት እንደነበር በቀጥታ ከመጠየቅ ይልቅ ቀኑን እንዴት እንዳሳለፍክ መንገርና የምትሰጠውን ምላሽ መስማት ትችላለህ። አሊያም ደግሞ በአንድ ጉዳይ ላይ ያላትን አመለካከት ለማወቅ ስትፈልግ ጉዳዩን ትንሽ ዞር አድርገህ ለመጠየቅ ሞክር። ለአብነት ያህል፣ ጓደኛዋ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚሰማትና ምን ምክር ልትሰጣት እንደምትችል ልትጠይቃት ትችላለህ።

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ፈጽሞ የማይቻል ነገር አይደለም። ከልጅህ ጋር በምትነጋገርበት መንገድ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን አድርግ። በዚህ ረገድ የተሳካላቸውን ወላጆች ምክር ጠይቅ። (ምሳሌ 11:14) ከልጅህ ጋር ስትነጋገር ‘ለመስማት የፈጠንክ፣ ለመናገርና ለቊጣ ደግሞ የዘገየህ ሁን።’ (ያዕቆብ 1:19) ከሁሉም በላይ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘውን ልጅህን “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” ለማሳደግ በምታደርገው ጥረት ተስፋ አትቁረጥ።—ኤፌሶን 6:4.

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ . . .

  • ልጄ በጉርምስና የዕድሜ ክልል ውስጥ ከገባ በኋላ ምን ዓይነት ለውጥ አይቼበታለሁ?

  • የሐሳብ ልውውጥ በማደርግበት መንገድ ላይ ምን ማሻሻያዎችን ማድረግ እችላለሁ?