በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቃለ ምልልስ | ዶክተር ጂን ህዋንግ

አንድ የሒሳብ ሊቅ ስለሚያምኑበት ነገር ምን ይላሉ?

አንድ የሒሳብ ሊቅ ስለሚያምኑበት ነገር ምን ይላሉ?

ታይዋን ውስጥ በምትገኘው ታይናን ከተማ በ1950 የተወለዱት ዶክተር ጂን ህዋንግ፣ ታይዋን ከሚገኘው ቾንግ ቸንግ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ጡረታ የወጡ የሒሳብ ፕሮፌሰር ናቸው። በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ በፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሠርተዋል፤ በዚያም ስታትስቲክስና ፕሮባቢሊቲ ያስተምሩ እንዲሁም ምርምር ያደርጉ ነበር። ለብዙ ዓመታት በስታትስቲክስ መስክ አንቱ ከተባሉ ባለሙያዎች አንዱ ነበሩ፤ አሁንም በዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ። ወጣት በነበሩበት ጊዜ፣ ሕይወት የጀመረው በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ ያምኑ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን አመለካከታቸውን ቀይረዋል። ንቁ! መጽሔት ስለ ሥራቸውና ስለ እምነታቸው ቃለ ምልልስ አድርጎላቸው ነበር።

በልጅነትዎ ምን ትምህርቶች ተምረው ነበር?

የተማርኩበት ትምህርት ቤት የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ያስተምር የነበረ ቢሆንም ሕይወት እንዴት እንደጀመረ የሚያብራራ ሰው ግን አልነበረም። ወላጆቼ የታኦይዝም እምነት ተከታዮች በሆኑበት ጊዜ ደግሞ የሃይማኖት አስተማሪዎቻቸው የሚያስተምሩትን ነገር ማዳመጥና ብዙ ጥያቄዎች መጠየቅ ጀመርኩ። ይሁንና የማገኘው መልስ አጥጋቢ አልነበረም።

የሒሳብ ትምህርት ማጥናት የመረጡት ለምንድን ነው?

የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ሒሳብ በጣም ያስደምመኝ ነበር። ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላም ቢሆን ለሒሳብ ያለኝ አድናቆት አልቀነሰም፤ በተለይ ሒሳብና ፕሮባቢሊቲ መማር ያስደስተኝ ነበር። አንድ ነገር አጭርና ግልጽ በሆነ የሒሳብ ቀመር ሲቀመጥ ለእኔ ውብና ማራኪ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመር ያነሳሳዎት ምንድን ነው?

በ1978 ባለቤቴ ጂንግሁዌ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች፤ አልፎ አልፎ እኔም በውይይቱ እሳተፍ ነበር። በዚህ ጊዜ የምንኖረው በዩናይትድ ስቴትስ ነበር። ጂንግሁዌ በፊዚክስ ዶክትሬት ዲግሪዋን የያዘችው በዚሁ ወቅት ሲሆን እኔ ደግሞ ኢንዲያና በሚገኘው ፐርድዩ ዩኒቨርሲቲ ስታትስቲክስ እማር ነበር።

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን አስተያየት አለዎት?

ምድር ለሰው ሕይወት እንዴት ምቹ ሆና እንደተዘጋጀች የሚገልጸው ሐሳብ አስደንቆኛል። በዘፍጥረት ላይ ስለ ስድስቱ የፍጥረት ቀናት የሚናገረው ዘገባ ውስብስብ ባልሆነ መንገድ የቀረበ ቢሆንም እንኳ ከጥንታዊ አፈ ታሪኮች በተለየ መልኩ እውነታውን የሚያንጸባርቅ ነው። * ያም ቢሆን በፈጣሪ ለማመን ብዙ ዓመታት ፈጅቶብኛል።

ይህን መቀበል የከበደዎት ለምን ነበር?

በፈጣሪ ካመንኩ ከልጅነቴ ጀምሮ የነበረኝን ሃይማኖት መተው ይኖርብኛል

ለእኔ በፈጣሪ ማመን የአመለካከት ለውጥ ከማድረግ ያለፈ ነገር ይጠይቅብኛል። በፈጣሪ ካመንኩ ከልጅነቴ ጀምሮ የነበረኝን ሃይማኖት መተው ይኖርብኛል፤ ምክንያቱም ታኦይዝም አንድ አምላክ ወይም ፈጣሪ እንዳለ አያስተምርም።

ታዲያ ከጊዜ በኋላ አመለካከትዎን የለወጡት ለምንድን ነው?

ስለ ሕይወት አመጣጥ ይበልጥ ሳስብ ‘የመጀመሪያው ሕያው ፍጥረት ውስብስብ መሆን አለበት’ ወደሚል መደምደሚያ ደረስኩ። ለምሳሌ ይህ ፍጥረት ዘር መተካት የሚኖርበት ሲሆን ለዚህ ደግሞ ጄኔቲካዊ መረጃና ይህንን መረጃ በትክክል ማስተላለፍ የሚችልበት ዘዴ ሊኖረው ይገባል። ውስብስብ ያልሆነ ሴል እንኳ አንድን አዲስ ሴል ለመገንባት እንዲሁም ኃይሉን በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል የሞለኪውል ማሽኖች ያስፈልጉታል። እንዲህ ያለው ውስብስብ ሂደት ሕይወት ከሌለው ነገር እንዲሁ በአጋጣሚ ሊገኝ ይችላል? የሒሳብ ባለሙያ እንደመሆኔ መጠን ይህን ሐሳብ ልቀበለው አልችልም። ምክንያቱም ይህ ሂደት እንዲሁ በአጋጣሚ ይከናወናል ብሎ ማሰብ ጨርሶ የማይታሰብ ነገር ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩትን ትምህርት ለመመርመር ያነሳሳዎት ምንድን ነው?

አልፎ አልፎ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እወያይ ነበር። ከዚያም በ1995 ታይዋን ሄጄ ሳለ በመታመሜ የሌሎች እርዳታ አስፈልጎኝ ነበር። በወቅቱ ዩናይትድ ስቴትስ የነበረችው ባለቤቴ፣ ታይዋን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲረዱኝ ጠየቀቻቸው። የሄድኩበት ሆስፒታል፣ አልጋዎቹ ሁሉ ተይዘው ስለነበር እነሱ ሲመጡ ከሆስፒታሉ ውጭ በጣም ተዳክሜ አገኙኝ። አንደኛው የይሖዋ ምሥክር ወስዶ ሆቴል አሳረፈኝ። ያለሁበትን ሁኔታ ይከታተል የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለሕክምና ወደ ክሊኒክ ወሰደኝ።

ያደረጉልኝ መልካም ነገር ልቤን ነካው፤ በሌሎች አጋጣሚዎች የይሖዋ ምሥክሮች ለቤተሰቤ ባደረጉት ነገር ላይም አሰላሰልኩ። እነሱን ልዩ የሚያደርጋቸው እምነታቸው እንደሆነ ስለተገነዘብኩ መጽሐፍ ቅዱስ መማሬን ቀጠልኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ተጠመቅኩ።

የሚያምኑበት ነገር ከተከታተሉት የቀለም ትምህርት ጋር ይጋጫል?

በፍጹም! ባለፉት ዓመታት፣ ጂን ስለሚሠራቸው ሥራዎች ለሚያጠኑ የሳይንስ ሊቃውንት ሙያዊ ድጋፍ ሳደርግ ቆይቻለሁ። የጄኔቲክስ ጥናት ሕይወት ባላቸው ነገሮች ውስጥ ስለሚከናወኑት ሂደቶች ብዙ ማብራሪያ ይሰጣል፤ ይህ ደግሞ ፈጣሪ ባለው ጥበብ እንድደነቅ አድርጎኛል።

ይህን ጥበብ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ሊጠቅሱልን ይችላሉ?

ዘር የሚተካበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንደ አሜባ ያሉ አንዳንድ ፍጥረታት የወንድና የሴት ፆታ የላቸውም። አንድ ሴል ብቻ ያላቸው እነዚህ ፍጥረታት ጄኔቲካዊ መረጃቸውን በመገልበጥ ለሁለት ይከፈላሉ፤ ይህ ሂደት ኢፆታዊ መራባት በመባል ይታወቃል። ሆኖም አብዛኞቹ እንስሳትና ዕፀዋት የሚራቡት በፆታዊ መንገድ፣ ይኸውም የወንዱንና የሴቷን ጄኔቲካዊ መረጃ በማዋሃድ ነው። ፆታዊ መራባትን አስገራሚ የሚያደርገው ምንድን ነው?

አንድ ሕይወት ያለው አካል በቀላሉ ለሁለት በመከፈል የሚራባበት ሥርዓት ያለምንም ችግር ለረጅም ጊዜ ቀጥሏል፤ ታዲያ ይህ ሥርዓት ሁለት ነገሮች ተጣምረው አንድ ነገር ወደሚያስገኙበት ሂደት መቀየር ያስፈለገው ለምንድን ነው? ግማሹን ጄኔቲካዊ መረጃ ከወንዱ፣ ግማሹን ደግሞ ከሴቷ ወስዶ የማዋሃድ ሂደት ውስብስብ መሆኑ በዝግመተ ለውጥ ለሚያምኑ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ራስ ምታት ሆኖባቸዋል። እንደኔ እንደኔ ፆታዊ መራባት ጥበበኛ የሆነ አምላክ መኖሩን በማያሻማ መንገድ ያረጋግጣል።

^ አን.11 ስለ ፍጥረት ቀናት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? የተባለውን ብሮሹር ተመልከት። ብሮሹሩ www.pr418.com/am ላይ ይገኛል።