በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጣም በሚያስፈልገኝ ወቅት ያገኘሁት ተስፋ

በጣም በሚያስፈልገኝ ወቅት ያገኘሁት ተስፋ

በድንገት እንደ በድን በውኃው ላይ መንሳፈፍ ጀመርኩ። ውኃው ላይ የተንሳፈፍኩት በደረቴ ስለነበር ጭንቅላቴን ቀና አድርጌ አየር ለማግኘት ሞከርኩ፤ ይሁንና አንገቴን ማንቀሳቀስ ተሳነኝ። በጣም ደነገጥኩ፤ ከዚያም ወደ ላይ ልገለበጥ ሞከርኩ፤ ይሁን እንጂ እጆቼንና እግሮቼን ማንቀሳቀስ አልቻልኩም። ውኃው ወደ ሳንባዬ መግባት ጀመረ። በ1991 በዚያ ሞቃት የበጋ ቀን ያጋጠመኝ ነገር ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ለወጠው።

የተወለድኩት በሴሬንክ ከተማ ሲሆን ያደግኩት በሰሜናዊ ምሥራቅ ሀንጋሪ በምትገኝ ቲሰለዳኒ የምትባል መንደር ነበር። ሰኔ 1991 ከጓደኞቼ ጋር በቲሳ ወንዝ ላይ ወደሚገኝ የማናውቀው ቦታ ሄድን። ውኃው ጥልቅ ነው ብዬ በማሰብ ዘልዬ ሶቶ ገባሁ። ይሁንና በጣም ተሳስቼ ነበር! በአንገቴ ላይ ያሉ ሦስት የአከርካሪ አጥንቶች የተሰበሩ ሲሆን በህብለ ሰረሰሬ ላይም ጉዳት ደረሰብኝ። ጓደኛዬ መንቀሳቀስ እንዳቃተኝ ሲመለከት በጥንቃቄ ከውኃው ውስጥ ጎትቶ አወጣኝ።

ሙሉ በሙሉ ራሴን ስላልሳትኩ አንድ ከባድ ችግር እንደደረሰብኝ ተረዳሁ። አንድ ሰው የድንገተኛ አደጋ እርዳታ ስለጠራ አንድ ሄሊኮፕተር መጥቶ ወደ ሆስፒታል ወሰደኝ፤ እዚያም ሐኪሞች አከርካሪዬ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስበት ቀዶ ጥገና አደረጉልኝ። በኋላም ከሕመሜ እንዳገግም ወደ ዋና ከተማዋ ማለትም ወደ ቡዳፔስት ተዛወርኩ። ለሦስት ወራት በጀርባዬ እንደተኛሁ ቆየሁ። ጭንቅላቴን ማንቀሳቀስ ብችልም ከትከሻዬ በታች ያሉትን ጡንቻዎች ማዘዝ አልችልም ነበር። ገና በ20 ዓመቴ ሙሉ በሙሉ የሌሎች ጥገኛ ሆንኩ። በወቅቱ በጣም ተስፋ ከመቁረጤ የተነሳ ሞትን ተመኝቼ ነበር።

በመጨረሻ ወደ ቤት ስመለስ ወላጆቼ እኔን ለመንከባከብ የሚያስችል ሥልጠና ተሰጣቸው። ይሁን እንጂ ሥራው ሰውነታቸውን አዝሎት እንዲሁም ስሜታቸውን ጎድቶት ነበር፤ በመሆኑም ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ የመንፈስ ጭንቀት ያዘኝ። በዚህ ጊዜ የባለሙያ እርዳታ ማግኘቴ ስለደረሰብኝ የአካል ጉዳት ያለኝን አመለካከት እንድለውጥ ረድቶኛል።

በተጨማሪም ስለ ሕይወት ብዙ ማሰብ ጀመርኩ። ሕይወት ዓላማ አለው? እንዲህ ያለ አሳዛኝ ነገር የደረሰብኝ ለምንድን ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት መጽሔቶችንና መጻሕፍትን አነበብኩ። መጽሐፍ ቅዱስንም ለማንበብ ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ለመረዳት አዳጋች ሆነብኝ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤን ተውኩ። ከአንድ ቄስ ጋር ተነጋግሬ የነበረ ቢሆንም የሰጠኝ መልስ አላረካኝም።

በ1994 የጸደይ ወቅት ላይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው አባቴን አነጋገሩት፤ እሱም እኔን እንዲያነጋግሩኝ ጠየቃቸው። አምላክ ወደፊት ምድርን ገነት እንደሚያደርግ እንዲሁም በሽታንና ሥቃይን እንደሚያስወግድ ሲገልጹልኝ አዳመጥኳቸው። የነገሩኝ ነገር ሁሉ በጣም ደስ የሚል ነበር፤ እኔ ግን እውነት የሚሆን አልመሰለኝም። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ሁለት መጻሕፍት ከእነሱ ወሰድኩ። መጻሕፍቱን ካነበብኩ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮቹ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ጋበዙኝ፤ እኔም በሐሳቡ ተስማማሁ። በተጨማሪም እንድጸልይ አበረታቱኝ።

አምላክ እንደሚያስብልኝ እርግጠኛ ሆንኩ

ውይይታችንን እየቀጠልን ስንሄድ  ለአብዛኞቹ ጥያቄዎቼ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ አገኘሁ። እንዲሁም አምላክ እንደሚያስብልኝ እርግጠኛ ሆንኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ለሁለት ዓመታት ካጠናሁ በኋላ መስከረም 13, 1997 ቤታችን ባለ የመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ተጠመቅሁ። ያ ቀን በሕይወቴ ውስጥ እጅግ ከተደሰትኩባቸው ቀኖች አንዱ ነው።

በ2007 በቡዳፔስት ወደሚገኝ ለአካል ጉዳተኞች የተዘጋጀ ቤት ገባሁ። ይህም የተማርኳቸውን በርካታ አስደናቂ ነገሮች ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችሉኝ ብዙ አጋጣሚዎች ከፍቶልኛል። በአገጬ ልነዳው የምችል ላለሁበት ሁኔታ ምቹ ሆኖ የተሠራ ባለሞተር ተሽከርካሪ ወንበር ስላለኝ ጥሩ የአየር ጠባይ በሚኖርበት ቀን ወደ ውጭ ወጥቼ ሰዎችን አነጋግራለሁ።

በጉባኤዬ ውስጥ ያለ አንድ ቤተሰብ በልግስና ባደረገልኝ የገንዘብ እርዳታ አማካኝነት የጭንቅላቴን እንቅስቃሴ ተከትሎ የሚሠራ አንድ ላፕቶፕ ማግኘት ቻልኩ። በዚህ መሣሪያ ተጠቅሜ በኢንተርኔት አማካኝነት ስልክ መደወል እንዲሁም የጉባኤዬ አባላት ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ ላላገኟቸው ሰዎች ደብዳቤ መጻፍ ችያለሁ። በዚህ መንገድ ሌሎችን መርዳት መቻሌ ከሰዎች ጋር የመነጋገር ችሎታዬን በጣም ያሻሻለልኝ ሲሆን በራሴ ችግር ላይ ብቻ ከማተኮር እንድቆጠብ ረድቶኛል።

የጭንቅላቴን እንቅስቃሴ ተከትሎ በሚሠራ መሣሪያ እየታገዝኩ በኢንተርኔት አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች አካፍላለሁ

ሌላው ቀርቶ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንኳ መገኘት ችያለሁ። ወደ መንግሥት አዳራሹ ስሄድ መንፈሳዊ ወንድሞቼ በጥንቃቄ ተሽከርካሪ ወንበሬን ተሸክመው ስብሰባው ወደሚደረግበት አንደኛ ፎቅ ላይ ያወጡኛል። ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ተሰብሳቢዎቹ ሐሳብ በመስጠት የሚሳተፉበት ጊዜ ሲኖር አጠገቤ የሚቀመጠው ወንድም እኔን ወክሎ እጁን ያወጣል። ሐሳብ ስሰጥ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሴን ወይም የማጥኛ ጽሑፉን ከፍ አድርጎ ይይዝልኛል።

ሕመሙ ሁልጊዜ ያሠቃየኛል፤ እንዲሁም ምንም ነገር ለማድረግ የሌሎች እርዳታ ያስፈልገኛል። በዚህም ምክንያት አሁንም ስሜቴ የሚጎዳበት ጊዜ አለ። ይሁን እንጂ ከይሖዋ አምላክ ጋር የመሠረትኩት ወዳጅነት ያጽናናኛል፤ ምክንያቱም የሚያስጨንቀኝን ነገር ግልጽልጽ አድርጌ ስነግረው እንደሚያዳምጠኝ አውቃለሁ። በተጨማሪም በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ እንዲሁም መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ የሚያደርጉልኝ ድጋፍ ብርታት ሰጥቶኛል። ከእነሱ ጋር ያለኝ ወዳጅነት፣ የሚያደርጉልኝ ስሜታዊ ድጋፍና ስለ እኔ የሚያቀርቡት ጸሎት በአእምሮዬም ሆነ በስሜቴ ላይ ዘላቂ ጉዳት እንዳይደርስብኝ ረድቶኛል።

ይሖዋ ልክ በሚያስፈልገኝ ወቅት መጽናኛ ሰጥቶኛል። በተጨማሪም በአዲሱ ዓለም ውስጥ ፍጹም ጤንነት የማግኘት ተስፋ አለኝ። በመሆኑም ‘እየተራመድኩና እየዘለልኩ’ አስደናቂ ስለሆነው ፍቅሩና ደግነቱ ‘እሱን ማመስገን’ የምችልበትን ያን ጊዜ እናፍቃለሁ።—የሐዋርያት ሥራ 3:6-9