በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሚጥል በሽታ—ልታውቀው የሚገባው ነገር

የሚጥል በሽታ—ልታውቀው የሚገባው ነገር

አንድ የምታውቀው ሰው በድንገት መሬት ላይ ወድቆ ራሱን ሳተ። ሰውነቱ ግትርትር ያለ ሲሆን ጭንቅላቱ እንዲሁም እግሮቹና እጆቹ መንዘፍዘፍ ጀመሩ። ይህ ግለሰብ የሚጥል በሽታ እንዳለበት ካወቅህ የሕክምና እርዳታ እስኪያገኝ ድረስ አንዳንድ እርምጃዎችን በመውሰድ ልትረዳው ትችላለህ። ብዙ ሰዎች ስለዚህ የጤና እክል የተሳሳተ አመለካከት አላቸው፤ እስቲ ይህን የጤና እክል አስመልክቶ አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮችን እንመልከት።

የሚጥል በሽታ ምንድን ነው? የሚጥል በሽታ አእምሯችን የሚሠራበትን መንገድ የሚነካ የጤና እክል ሲሆን የታማሚው ሰውነት ለአጭር ጊዜ እንዲንዘፈዘፍ ያደርጋል። ሰውነቱ የሚንዘፈዘፍበት ጊዜ በአብዛኛው ከአምስት ደቂቃ አይበልጥም። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ሁኔታ ግራንድ ማል ሲዠር ተብሎ የሚጠራው ዓይነት የሚጥል በሽታ ነው።

የሕመሙ መንስኤ ምንድን ነው? ሕመሙ የሚነሳው በአንጎል ሴሎች መካከል ያለው የኤሌክትሪክ ፍሰት ሲዛባ እንደሆነ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚከሰትበት ምክንያት አይታወቅም።

የሚጥል በሽታ ያለበት ሰው ወድቆ ሲንዘፈዘፍ ባይ ምን ማድረግ ይኖርብኛል? ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ዘ ብሬይን ኤንድ ብሬይን ዲስኦርደርስ እንዲህ ይላል፦ “በአካባቢው ያሉ ሰዎች፣ በግለሰቡ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነገር እንዳይኖር ከማድረግ እንዲሁም በአግባቡ እየተነፈሰ መሆኑን ከመከታተል ውጭ ሰውነቱ መንዘፍዘፉን እስኪያቆም ድረስ ምንም ሳያደርጉ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።” በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፉ እንደሚናገረው “ግለሰቡ ከአምስት ደቂቃ በላይ መንዘፍዘፉን ከቀጠለ፣ የመጀመሪያው ካቆመ ብዙም ሳይቆይ እንደ አዲስ መንዘፍዘፍ ከጀመረ ወይም ሰውነቱ መንዘፍዘፍ ካቆመ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ግለሰቡ ራሱን ካላወቀ አምቡላንስ ሊጠራለት ይገባል።”

ታዲያ በዚህ ወቅት ግለሰቡን ልረዳው የምችለው እንዴት ነው? ጭንቅላቱ እንዳይጎዳ ከጭንቅላቱ ሥር አንድ ነገር አድርግለት፤ እንዲሁም ሊወጉት የሚችሉ ነገሮችን ከአካባቢው አስወግድ። መንዘፍዘፉ ሲቆም፣ በቀጣዩ ገጽ ላይ ያለው ሥዕል እንደሚያሳየው ሕመምተኛውን በጎኑ አስተኛው።

ሕመምተኛው ከነቃ በኋላ ምን ማድረግ ይኖርብኛል? በመጀመሪያ፣ እንዳይደናገጥ አረጋጋው። ከዚያም ቀጥ ብሎ እንዲቆም እርዳውና አስፈላጊውን እረፍት ማድረግ ወደሚችልበት ቦታ ይዘኸው ሂድ። አብዛኞቹ ሰዎች ማንዘፍዘፉ ካቆመ በኋላ ግራ የሚጋቡ ከመሆኑም ሌላ እንቅልፍ እንቅልፍ ይላቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ሲነቁ ወዲያውኑ አገግመው ሕመሙ ከመነሳቱ በፊት ያከናውኑ የነበረውን ነገር መሥራታቸውን መቀጠል ይችላሉ።

የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች ሁሉ ሕመሙ ሲነሳባቸው ሰውነታቸው ይንዘፈዘፋል? አይንዘፈዘፍም። አንዳንድ ሕመምተኞች መሬት ላይ ባይወድቁም ለተወሰነ ቅጽበት ያህል ራሳቸውን ይስታሉ። ይኼኛው ዓይነት ሕመም ፔቲ ማል ሲዠር ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በአብዛኛው የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ነው፤ ስሜቱ ካለፈ በኋላም በግለሰቡ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አይታይም። የሚጥል በሽታ ያለባቸው አንዳንድ ሰዎች ፔቲ ማል ሲዠር ሲያጋጥማቸው  ረዘም ላለ ጊዜ ይኸውም ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሊቆይባቸው ይችላል። እንዲህ ባለው ሁኔታ ሕመምተኛው በክፍሉ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ሊል፣ ልብሱን ሊጎትት ወይም ሌላ እንግዳ የሆነ ነገር ሊያደርግ ይችላል። ይህ ስሜት ካለፈለት በኋላ ሊያዞረው ይችላል።

የሚጥል በሽታ ያለበት ሰው ሕይወት ምን ይመስላል? የሚጥል በሽታ ያለባቸው ብዙ ሰዎች፣ በሽታው አጉል ጊዜ ወይም ቦታ ላይ እንዳይነሳባቸው ሁልጊዜ እንደሚሰጉ ለመረዳት አያዳግትም። የሚያሳፍር ሁኔታ እንዳያጋጥማቸው ሲሉ ብዙ ሰዎች ባሉበት አካባቢ ላለመገኘት ሊመርጡ ይችላሉ።

የሚጥል በሽታ ላለበት ሰው ድጋፍ መስጠት የምችለው እንዴት ነው? ስሜቱን አውጥቶ እንዲገልጽ አበረታታው። ጥሩ አድማጭ ሁን። ሕመሙ ሲነሳበት ምን እንድታደርግለት እንደሚፈልግ ጠይቀው። የሚጥል በሽታ ያለባቸው ብዙ ሰዎች መኪና ስለማይነዱ አንተ በመኪና ልታደርሰው ወይም ልትላላከው እንደምትችል ልትነግረው ትችላለህ።

ሕመሙ ቶሎ ቶሎ እንዳይነሳ ለመከላከል ወይም ጨርሶ ለማስቀረት ማድረግ የሚቻል ነገር ይኖር ይሆን? እንደ ውጥረትና እንቅልፍ ማጣት ያሉ ነገሮች ሕመሙ የመነሳቱ አጋጣሚ ከፍ እንዲል ያደርጋሉ። በመሆኑም የሚጥል በሽታ ሕመምተኞች፣ አዘውትረው አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግና በቂ እረፍት በማግኘት ውጥረትን ለመቀነስ እንዲጥሩ ባለሙያዎች ያበረታታሉ። አንዳንድ ጊዜ፣ መድኃኒቶችም ሕመሙ እንዳይነሳ በመከላከል ረገድ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ።