በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትዕግሥት ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው?

ትዕግሥት ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው?

ያለፉትን ርዕሶች ካነበብክ በኋላ ትዕግሥት ማዳበርህ የተሻለ ጤንነትህ እንዲኖርህ ብሎም ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ እንዲሁም ጥሩ ወዳጆች ለማፍራት እንደሚረዳህ ሳትስማማ አትቀርም። ታዲያ ይበልጥ ትዕግሥተኛ መሆንን መማር የምትችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ልብ በል።

መንስኤዎቹን ለይተህ እወቅ፦

ትዕግሥት እንድታጣ የሚያደርጉ ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ይኖሩ ይሆናል። ትዕግሥት የሚያሳጣህ ምንድን ነው? አንዳንድ ሰዎች ናቸው? ምናልባት በዋነኝነት ትዕግሥትህን የምትፈታተነው የትዳር ጓደኛህ ናት? ወይስ ወላጆችህ ወይም ልጆችህ? በሌላ በኩል ደግሞ በአብዛኛው ትዕግሥት እንድታጣ የሚያደርጉህ ከጊዜ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ናቸው? ለምሳሌ ያህል፣ ሌሎችን መጠበቅ ሲኖርብህ ወይም ሰዓት ሲያልፍብህ ትዕግሥት ታጣለህ? ሲደክምህ፣ ሲርብህ፣ እንቅልፍ ሲጫጫንህ ወይም ውጥረት ሲያጋጥምህ ትዕግሥተኛ መሆን ይከብድሃል? ብዙውን ጊዜ ትዕግሥትህን የምታጣው ቤት ውስጥ ነው ወይስ በሥራ ቦታ?

ትዕግሥት የሚያሳጡህን ሁኔታዎች ወይም ነገሮች ለይቶ ማወቁ ትዕግሥት ለማዳበር ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? በጥንት ዘመን የኖረው ንጉሥ ሰለሞን “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 22:3) በዚህ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ መሠረት ትዕግሥት የሚያሳጡህን ሁኔታዎች ወይም ነገሮች አስቀድመህ ‘ካየሃቸው’ ወይም ካወቅሃቸው ልታስወግዳቸው ትችል ይሆናል። ትዕግሥት ለማዳበር መጀመሪያ ላይ የታሰበበት ጥረት ማድረግ ይኖርብህ ይሆናል፤ እያደር ግን ይህን ባሕርይ ማሳየት ቀላል እየሆነልህ ይሄዳል።

አኗኗርህን ቀላል አድርግ፦

በሚኒሶታ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሴንት ጆንስ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ኖሪን ኸርትስፌልድ እንዲህ ብለዋል፦ “እንደ እውነቱ ከሆነ ሰዎች በአንድ ጊዜ ብዙ ሥራዎችን መሥራት አይችሉም። አእምሯችን በአንድ ጊዜ በብዙ ነገሮች ላይ ማተኮር አይችልም።” እኚህ ሴት አክለውም እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “በአንድ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ለመሥራት መሞከር አእምሯችን በአንድ ነገር ላይ ትኩረት የማድረግ ችሎታው እያደር እንዲቀንስ ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ እንደ ትዕግሥትና ጽናት ያሉትን ባሕርያት እንዲሁም የማመዛዘንና ችግር የመፍታት ችሎታችንን እያደር እንድናጣ ያደርጋል።”

ብዙ ነገሮች ለመሥራት፣ ብዙ ቦታዎች ለመሄድ እንዲሁም የብዙ ሰዎች ወዳጅ ለመሆን መጣር ውጥረት ስለሚፈጥር በዚህ ወቅት ትዕግሥት ማዳበር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የጠቀስናቸው ዶክተር ጄኒፈር ሀርትሽታይን “ትዕግሥት እንድናጣ የሚያደርገን ዋነኛ መንስኤ ውጥረት ነው” በማለት ያስጠነቅቃሉ።

ረጋ ብለህ ሕይወትን ለማጣጣም ሞክር። ከብዙ ሰዎች ጋር ጥልቀት የሌለው ወዳጅነት ከመመሥረት ይልቅ ከጥቂት ሰዎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ይኑርህ። ጊዜህን እንዴት እንደምትጠቀምበት አስቀድመህ አስብ፤ እንዲሁም ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች በጥበብ ምረጥ። የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎችና የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ጊዜህን እንዳያባክኑብህ ተጠንቀቅ።

አኗኗርህን ቀላል ለማድረግ የዕለት ተዕለት ፕሮግራምህን ማጤን ሊያስፈልግህ ይችላል። ተረጋግተህ ማከናወን የምትችለው ወይም ከነጭራሹ ልትተወው የምትችለው ሥራ አለ? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ . . . ለማስቀመጥ ጊዜ አለው፤ አውጥቶ ለመጣልም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1, 6) በብዙ ነገሮች ተወጥረህ ትዕግሥትህ እንዳይሟጠጥ ጊዜ ሊወስዱ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን ማስወገድ ይኖርብህ ይሆናል።

እውነታውን ተቀበል፦

ስለ ሕይወት እውነታውን ያገናዘበ አመለካከት ይኑርህ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በሕይወት ውስጥ ነገሮች ሁልጊዜ በምንፈልገው ፍጥነት እንደማይከናወኑ መገንዘብ ያስፈልጋል። ነገሮች የሚከናወኑት በራሳቸው ጊዜ እንጂ አንተ በምትፈልገው ፍጥነት አይደለም። ትዕግሥተኛ ለመሆን ይህን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ሁለተኛ፣ በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ሁኔታዎች ሁልጊዜ መቆጣጠር እንደማትችል አስታውስ። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ፈጣን ርዋጮች ዘወትር በአሸናፊነት አይወጡም፤ ጀግኖችም በጦርነት ድል አያደርጉም፤ ጠቢባን ባለጸግነትን፣ የተማሩ ሰዎችም ሀብትን አያገኙም፤ ችሎታ ያላቸውም ሰዎች በማዕርግ አያድጉም፤ ነገር ግን ሁሉንም ጊዜና ዕድል ያጋጥማቸዋል፤ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሰው ይህ መጥፎ ዕድል መቼ እንደሚገጥመው አያውቅም።”—መክብብ 9:11, 12 የ1980 ትርጉም

ከአንተ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች ትዕግሥትህን እንዲያሟጥጡት ከመፍቀድ ይልቅ ልትቆጣጠራቸው የምትችላቸውን ነገሮች ለይተህ ለማወቅ ጣር። ለምሳሌ፣ ታክሲ ወይም አውቶቡስ በማጣትህ ከመናደድ ይልቅ ወደምትሄድበት ቦታ የምትደርስበት ሌላ አማራጭ ዘዴ ለማግኘት ሞክር። ትዕግሥትህ አልቆ በንዴት ከመብከንከን በእግር መሄድም እንኳ የተሻለ ሊሆን ይችላል። ያለህ አማራጭ መጠበቅ ብቻ ከሆነ ጊዜውን ጠቃሚ ነገሮችን ለማከናወን ለምሳሌ የሚጠቅም ነገር ለማንበብ ወይም ወደፊት ልትሠራቸው ስላሰብካቸው ነገሮች ዕቅድ ለማውጣት ተጠቀምበት።

ከቁጥጥርህ ውጭ ስለሆኑ ነገሮች መጨነቅ ምንም የሚፈይደው ነገር እንደሌለ የማይታበል ሐቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከእናንተ ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ደቂቃ መጨመር የሚችል ማነው?” በማለት ይናገራል።—ሉቃስ 12:25 አ.መ.ት

መንፈሳዊ ሰው ሁን፦

በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች መመሪያዎቹን በሥራ ማዋላቸው ትዕግሥት ለማዳበር እንደረዳቸው ተገንዝበዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው መንፈሳዊ የሆነ ሰው ትዕግሥትን ብቻ ሳይሆን እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ገርነትና ራስን መግዛት የመሳሰሉትን ጥሩ ባሕርያት ማሳየት ቀላል ይሆንለታል። (ገላትያ 5:22, 23) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ቃል ገብቷል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አንተም መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ጭንቀትን መቀነስና ይበልጥ ትዕግሥተኛ መሆን የምትችልበትን መንገድ እንድትማር እናበረታታሃለን።