በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ያህል ታውቃለህ?

ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ያህል ታውቃለህ?

በአደባባይ ስንሰብክ አይተኸን ታውቅ ይሆናል። ስለ እኛ የተጻፉ የዜና ዘገባዎችን አንብበህ ወይም ሌሎች የሚሉትን ነገር ሰምተህ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምን ያህል በትክክል ታውቃለህ?

እውቀትህን ፈትሽ

የሚከተሉትን ዓረፍተ ነገሮች እውነት ወይም ሐሰት በል።

እውነት ሐሰት

  1. የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያኖች ናቸው።

  2. የይሖዋ ምሥክሮች የፍጥረት አማኞች (ክሪኤሽኒስት) ናቸው።

  3. የይሖዋ ምሥክሮች በሕክምና አያምኑም።

  4. የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ይቀበላሉ።

  5. የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙት የራሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ብቻ ነው።

  6. የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ከእምነታቸው ጋር እንዲስማማ ለማድረግ ቀይረውታል።

  7. የይሖዋ ምሥክሮች በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አይካፈሉም።

  8. የይሖዋ ምሥክሮች የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችን በንቀት ያያሉ።

መልሶቹን በቀጣዮቹ ገጾች ላይ ማግኘት ትችላለህ።

  1. 1 እውነት። ኢየሱስ ያስተማራቸውን ትምህርቶችና የተወውን ፈለግ በጥብቅ ለመከተል እንጥራለን። (1 ጴጥሮስ 2:21) ሆኖም ክርስቲያን ተብለው ከሚጠሩ ሌሎች የሃይማኖት ቡድኖች በብዙ መንገዶች እንለያለን። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንጂ የሥላሴ ክፍል እንዳልሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተምረናል። (ማርቆስ 12:29) ‘ነፍስ አትሞትም’ ብለን አናምንም፤ እንዲሁም አምላክ ሰዎችን ለዘላለም በገሃነመ እሳት እንደሚያሠቃይ የሚገልጽ አንድም ጥቅስ እንደሌለ ተረድተናል። በተጨማሪም በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች አመራር የሚሰጡ ሰዎች ከሌሎች ልቀው እንዲታዩ የሚያደርግ የማዕረግ ስም ሊሰጣቸው እንደሚገባ አናምንም።—መክብብ 9:5፤ ሕዝቅኤል 18:4፤ ማቴዎስ 23:8-10

  2. 2 ሐሰት። አምላክ ሁሉንም ነገር እንደፈጠረ እናምናለን። ያም ቢሆን በክሪኤሽኒዝም የሚያምኑ ብዙ ሰዎች የሚያስተምሯቸውን ትምህርቶች አንቀበልም። ለምን? ምክንያቱም በርካታ የክሪኤሽኒዝም ጽንሰ ሐሳቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች ስድስቱ የፍጥረት ቀናት ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ እንዳላቸው ያምናሉ። ያም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቀን” የሚለው ቃል ረዘም ያለ ጊዜን ሊያመለክት ይችላል። (ዘፍጥረት 2:4፤ መዝሙር 90:4) አንዳንድ የክሪኤሽኒዝም አማኞች የምድር ዕድሜ ከጥቂት ሺህ ዓመታት እንደማይበልጥ ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ምድርም ሆነ ጽንፈ ዓለም የተፈጠሩት ስድስቱ የፍጥረት ቀናት ከመጀመራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት እንደሆነ ይጠቁማል። 1ዘፍጥረት 1:1

  3. 3 ሐሰት። የሕክምና እርዳታ እንቀበላለን። እንዲያውም አንዳንዶቻችን በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው እንደ ሉቃስ ሐኪሞች ነን። (ቆላስይስ 4:14) ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚጋጭ ማንኛውንም ዓይነት ሕክምና አንቀበልም። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ደምን ወደ ሰውነት ማስገባትን ስለሚከለክል ደም አንወስድም።—የሐዋርያት ሥራ 15:20, 28, 29

    በሌላ በኩል ግን ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን ከሁሉ የተሻለውን ሕክምና ማግኘት እንፈልጋለን። እንዲያውም የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሕሙማንን ለመርዳት ሲባል የተጀመሩ ደም እንዳይባክን የሚረዱ የሕክምና ዘዴዎች፣ መላውን ማኅበረሰብ እየጠቀሙ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ ታካሚዎች ደም ባለመውሰድ በደም ከሚተላለፉ በሽታዎች፣ ከአለርጂና የሕክምና ባለሙያዎች በሚሠሩት ስህተት ከሚመጣ ጉዳት መዳን ይችላሉ።

  4. 4 እውነት። መላው መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈና ጠቃሚ እንደሆነ’ እናምናለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህ ደግሞ በተለምዶ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ተብለው የሚጠሩትን ክፍሎች ያጠቃልላል። እኛ ግን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በማለት እንጠራቸዋለን። ይህ አሰያየም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው ወይም ጠቃሚ አይደሉም የሚል አመለካከት ከማስተላለፍ እንድንርቅ ያስችለናል።

  5. 5 ሐሰት። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ተጠቅመን የአምላክን ቃል እናጠናለን። መጽሐፍ ቅዱስአዲስ ዓለም ትርጉም በሚገኝባቸው ቋንቋዎች ግን ይህን ትርጉም መጠቀም እንመርጣለን፤ ምክንያቱም አዲስ ዓለም ትርጉም የአምላክን ስም የሚጠቀም ከመሆኑም ሌላ ትክክለኛና ግልጽ ነው። ይሖዋ የሚለውን የአምላክን ስም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጠቀምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መቅድም ላይ ለትርጉም ሥራው አስተዋጽኦ ያበረከቱ የ79 ሰዎች ስም ተዘርዝሯል። ያም ቢሆን ይህ ትርጉም የመጽሐፍ ቅዱስን ባለቤት ይኸውም የይሖዋ አምላክን ስም አንድም ቦታ ላይ አይጠቅስም! በአንጻሩ ግን አዲስ ዓለም ትርጉም የይሖዋ ስም በጥንታዊ ቅጂዎች ውስጥ በሚገኝባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ የአምላክን ስም መልሶ አስገብቷል። 2

  6. 6 ሐሰት። የምናምንባቸው ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር እንደማይስማሙ በተገነዘብንባቸው ጊዜያት ሁሉ ማስተካከያ አድርገናል። መጽሐፍ ቅዱስአዲስ ዓለም ትርጉም የተባለውን እትም በ1950 ከማዘጋጀታችን ከብዙ ዓመታት በፊት እንኳ በወቅቱ በነበሩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንጠቀም ነበር፤ ትምህርታችንም በእነዚያ ትርጉሞች ላይ የተመሠረተ ነበር።

  7. 7 ሐሰት። አገልግሎታችን ለማኅበረሰቡ ጥቅም ያስገኛል። ብዙዎች ከዕፅና ከአልኮል መጠጥ ሱስ ብሎም ከተለያዩ ጎጂ ልማዶች እንዲላቀቁ ረድተናል። መሠረተ ትምህርት ለማስተማር ያደረግነው ዝግጅት በዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ረድቷል። አደጋ ሲደርስ ለይሖዋ ምሥክሮችም ሆነ እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎች እርዳታ እንሰጣለን። በእነዚህ ወቅቶች በአደጋው የተጎዱ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ለመስጠት ጥረት እናደርጋለን። 3

  8. 8 ሐሰት። የሰዎች ሃይማኖት ምንም ይሁን ምን መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ” በማለት የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን። (1 ጴጥሮስ 2:17) ለምሳሌ በአንዳንድ አገሮች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ቢኖሩም፣ ፖለቲከኞች ወይም ሕግ አውጪዎች የሌሎች ሃይማኖቶችን እንቅስቃሴ እንዲገድቡ ወይም እንዲያግዱ ተጽዕኖ አናደርግም። አሊያም ደግሞ ሥነ ምግባራዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችንን በማኅበረሰቡ ላይ የሚጭኑ ሕጎች እንዲወጡ ዘመቻ አናካሂድም። ከዚህ ይልቅ ሌሎች ሃይማኖታችንን እንዲያከብሩልን እንደምንፈልግ ሁሉ እኛም የእነሱን መብት እናከብራለን።—ማቴዎስ 7:12

ይህ ርዕስ ሕጋዊ ድረ ገጻችን በሆነው jw.org ላይ የወጡ ሐሳቦችን የያዘ ነው። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ስለ እኛ > ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች የሚለውን ክፍል ተመልከት።

^ 1. በመሆኑም ከክሪኤሽኒስቶች በተለየ ምድር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዓመታት ዕድሜ ሊኖራት እንደሚችል የሚገልጹ ተአማኒነት ያላቸው ሳይንሳዊ ዘገባዎችን አንቃወምም።

^ 2. አዲስ ዓለም ትርጉምን ለየት የሚያደርገው ሌላም ነገር አለ፤ የሚሠራጨው ያለክፍያ ነው። በዚህም የተነሳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማንበብ ችለዋል። አዲስ ዓለም ትርጉም በአሁኑ ጊዜ 130 በሚያህሉ ቋንቋዎች ይገኛል። እንዲያውም ይህን ትርጉም www.pr418.com/am ላይ ማንበብ ትችላለህ።

^ 3. በአደጋ ለተጎዱ ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ የገንዘብ መዋጮዎችን እንጠቀማለን። (የሐዋርያት ሥራ 11:27-30) በሥራው ላይ የሚካፈሉት የበጎ ፈቃድ ሠራተኖች ገንዘብ ስለማይከፈላቸው የሚዋጣው ገንዘብስ በሙሉ የሚውለው በአደጋው የተጠቁትን ሰዎች ለመርዳት ነው፤ በአስተዳደር ሥራ ላይ ለሚሳተፉ የሚከፈል ደሞዝ የለም።