በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጭፍን ጥላቻ—አንተንም አጥቅቶህ ይሆን?

ጭፍን ጥላቻ—አንተንም አጥቅቶህ ይሆን?

ጭፍን ጥላቻ ልክ እንደ ቫይረስ ነው። ይህ ቫይረስ ጉዳት የሚያስከትል ሲሆን በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው እንኳ ላያውቁ ይችላሉ።

ሰዎች ጭፍን ጥላቻ የሚያድርባቸው ከእነሱ የተለየ ዜግነት፣ ብሔር፣ ጎሳ ወይም ቋንቋ ላላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ከእነሱ የተለየ ሃይማኖት፣ ፆታ ወይም የኑሮ ደረጃ ላላቸው ሰዎችም ጭምር ነው። አንዳንዶች ደግሞ የሰዎችን ዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የአካል ጉድለት ወይም ውጫዊ ገጽታ ተመልክተው አሉታዊ ፍርድ ይሰጣሉ። እንደዚያም ሆኖ ግን ጭፍን ጥላቻ እንዳለባቸው አይሰማቸውም።

ጭፍን ጥላቻ አንተንም አጥቅቶህ ይሆን? አብዛኞቻችን ሌሎች ጭፍን ጥላቻ እንዳለባቸው በቀላሉ ማስተዋል እንችላለን። እኛ ራሳችን ጭፍን ጥላቻ እንዳለብን ማስተዋል ግን ሊከብደን ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ መጠኑ ይነስም ይብዛ ሁላችንም በውስጣችን ጭፍን ጥላቻ አለብን። የኅብረተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ዴቪድ ዊልያምስ ስለ አንድ ቡድን አሉታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የዚያ ቡድን አባል የሆነ ሰው ሲያገኙ “ምንም ሳይታወቃቸው ያን ግለሰብ ከሌሎች በተለየ ዓይን” እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ ዮቪትሳ የሚኖረው በደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ በሚገኝ አገር ውስጥ ነው። በዚያ አገር አንድ አናሳ ቡድን አለ። ዮቪትሳ እንዲህ ሲል በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “በዚያ ቡድን ውስጥ ምንም ጥሩ ሰው እንደሌለ ይሰማኝ ነበር። ግን እንዲህ የሚሰማኝ በውስጤ ጭፍን ጥላቻ ስላለ ነው ብዬ አላስብም ነበር። ‘ይህ እኮ እውነታው ነው’ በማለት ለራሴ ሰበብ አቀርብ ነበር።”

በርካታ መንግሥታት ዘረኝነትን ጨምሮ ሌሎች የጭፍን ጥላቻ ዓይነቶችን ለመዋጋት ሕጎች ያወጣሉ። ያም ሆኖ ጭፍን ጥላቻን ማስወገድ አልቻሉም። ለምን? ምክንያቱም የሚያወጧቸው ሕጎች የአንድን ሰው ድርጊት ብቻ እንጂ አስተሳሰቡንና ስሜቱን መቆጣጠር አይችሉም። ጭፍን ጥላቻ የሚጀምረው ደግሞ በአእምሮና በልብ ውስጥ ነው። ታዲያ ከጭፍን ጥላቻ ጋር በሚደረገው ውጊያ ድል መቀዳጀት አይቻልም ማለት ነው? በእርግጥ ለጭፍን ጥላቻ ፍቱን መድኃኒት ይገኝለት ይሆን?

ቀጣዮቹ ርዕሶች በርካታ ሰዎች ጭፍን ጥላቻን ከአእምሯቸውና ከልባቸው እንዲያስወግዱ የረዷቸውን አምስት ጠቃሚ ምክሮች ይዘዋል።