በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደስታ የሚያስገኝ መንገድ

ጥሩ ጤንነትና ችግርን ተቋቁሞ የመኖር ችሎታ

ጥሩ ጤንነትና ችግርን ተቋቁሞ የመኖር ችሎታ

ሥር የሰደደ በሽታ ወይም የአካል ጉዳት በአንድ ሰው ሕይወት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በአንድ ወቅት ብርቱና ጤናማ የነበረ ኡልፍ የሚባል አንድ ሰው ሽባ ሆኖ መንቀሳቀስ ካቃተው በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “በከፍተኛ ሐዘን ተዋጥኩ። ቀድሞ የነበረኝን ብርታት፣ ድፍረትና ጉልበት አጣሁ። . . . ጨርሶ እንዳበቃልኝ ሆኖ ተሰማኝ።”

በኡልፍ ላይ የደረሰው ነገር እንደሚያሳየው ማናችንም ብንሆን የጤናችንን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አንችልም። ያም ሆኖ በበሽታ የመያዝ አጋጣሚያችንን ለመቀነስ ልንወስድ የምንችላቸው ምክንያታዊ እርምጃዎች አሉ። ሆኖም ጤንነታችን እያደር እያሽቆለቆለ ቢሄድስ? በሐዘን ተቆራምደን ከመኖር ውጭ ምንም አማራጭ የለንም ማለት ነው? በጭራሽ። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ በኋላ ላይ እንመለከታለን። መጀመሪያ ግን ጥሩ ጤንነት ለማግኘት የሚረዱ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን እንመልከት።

‘በልማዶችህ ልከኛ ሁን።’ (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 11) ከልክ በላይ የመብላትም ሆነ የመጠጣት ልማድ ጤናችንን ብቻ ሳይሆን ኪሳችንንም እንደሚጎዳው ግልጽ ነው! “ብዙ የወይን ጠጅ እንደሚጠጡ፣ ሥጋም ያለልክ እንደሚሰለቅጡ ሰዎች አትሁን፤ ሰካራምና ሆዳም ይደኸያሉና።”—ምሳሌ 23:20, 21

ሰውነትህን ከሚበክሉ ነገሮች ራቅ። “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።” (2 ቆሮንቶስ 7:1) ጫት የሚቅሙ፣ ትንባሆ የሚያጨሱም ሆነ የሚያኝኩ አሊያም አልኮል ወይም አደንዛዥ ዕፆችን አላግባብ የሚጠቀሙ ሰዎች ሰውነታቸውን እያረከሱ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል ሲጋራ ማጨስ “ለበሽታና ለአካል ጉዳት የሚዳርግ ከመሆኑም በላይ የማይጎዳው የሰውነት ክፍል የለም ማለት ይቻላል” በማለት ገልጿል።

ሰውነትህንና ሕይወትህን እንደ ውድ ስጦታ አድርገህ ተመልከታቸው። “ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው [በአምላክ] ነው።” (የሐዋርያት ሥራ 17:28) ይህን ሐቅ መገንዘባችን ሥራችንን በምናከናውንበትም ሆነ መኪና በምንነዳበት ወቅት እንዲሁም በመዝናኛ ምርጫችን ረገድ ለአደጋ ከሚያጋልጡ ነገሮች እንድንርቅ ያነሳሳናል። ቅጽበታዊ ደስታ ለማግኘት ብለን ዕድሜ ልካችንን አብሮን የሚዘልቅ የአካል ጉዳት ማትረፍ አንፈልግም!

አሉታዊ ስሜቶችን አስወግድ። አእምሮህና ሰውነትህ በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው። በመሆኑም አላስፈላጊ የሆነ ጭንቀትን፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣን፣ ቅናትንና ሌሎች ጎጂ ስሜቶችን ለማስወገድ ጥረት አድርግ። መዝሙር 37:8 “ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው” ይላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት” በማለት ይናገራል።—ማቴዎስ 6:34

አዎንታዊ በሆኑ ሐሳቦች ላይ ለማተኮር ጥረት አድርግ። ምሳሌ 14:30 “የሰከነ ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” ይላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኃኒት ነው” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 17:22) ይህ ሐሳብ ከሳይንስ አንጻርም ቢሆን ትክክል ነው። በስኮትላንድ የሚኖሩ አንድ ዶክተር “ደስተኛ የሆነ ሰው ደስተኛ ካልሆነ ሰው ጋር ሲነጻጸር ለበሽታ የሚዳረግበት አጋጣሚ አነስተኛ ነው” በማለት ተናግረዋል።

ችግርን ተቋቁሞ የመኖር ችሎታ አዳብር። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው እንደ ኡልፍ ሁሉ እኛም ቀጣይ የሆነ ችግርን ተቋቁሞ ከመኖር ውጭ ምንም አማራጭ ላይኖረን ይችላል። ችግሩን ተቋቁመን መኖር የምንችልባቸውን መንገዶች ግን መፈለግ እንችላለን። አንዳንዶች እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው በተስፋ መቁረጥ ስሜት ይዋጣሉ፤ ይህ ግን አብዛኛውን ጊዜ ችግሩን ከማባባስ በቀር ምንም የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ምሳሌ 24:10 “በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል” በማለት ይናገራል።

ሌሎች ደግሞ መጀመሪያ አካባቢ ተስፋ ይቆርጡ ይሆናል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን መልሰው በመበረታታት ራሳቸውን ከሁኔታው ጋር ለማስማማት ጥረት ያደርጋሉ፤ እንዲሁም ችግሩን መቋቋም የሚችሉባቸውን መንገዶች ይፈልጋሉ። ኡልፍም ያደረገው ይህንኑ ነው። ብዙ ከጸለየና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት አበረታች ሐሳቦች ላይ ካሰላሰለ በኋላ ‘ከእንቅፋቶች ይልቅ ባሉት ጥሩ አጋጣሚዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደጀመረ’ ተናግሯል። ከዚህም በላይ በሕይወታቸው ውስጥ ከባድ ፈተናዎች እንደደረሱባቸው በርካታ ሰዎች ሁሉ እሱም ርኅራኄ ማሳየትንና የሌሎችን ችግር እንደ ራሱ አድርጎ መመልከትን ተምሯል፤ በዚህ ረገድ ያገኘው ጠቃሚ ትምህርት ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን አጽናኝ መልእክት ለሌሎች እንዲናገር አነሳስቶታል።

ስቲቭ የተባለ ሰውም በሕይወቱ ውስጥ በጣም ከባድ ችግር አጋጥሞት ነበር። የ15 ዓመት ልጅ ሳለ በደረሰበት አደጋ ምክንያት ከአንገቱ በታች ሽባ ሆነ። በ18 ዓመቱ እጆቹን መልሶ ማንቀሳቀስ ቻለ። ከዚያም ዩኒቨርሲቲ የገባ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ፣ የአልኮል መጠጥ መጠጣትና የፆታ ብልግና መፈጸም ጀመረ። ስቲቭ ምንም ተስፋ የሌለው ሕይወት ይመራ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር ግን ለሕይወት ያለው አመለካከት የተለወጠ ከመሆኑም ሌላ መጥፎ ልማዶቹን እርግፍ አድርጎ ተወ። እንዲህ ብሏል፦ “ለረጅም ጊዜ ይሰማኝ የነበረው የባዶነት ስሜት አሁን የለም፤ ሰላም፣ ደስታና እርካታ ያለው ሕይወት እየመራሁ ነው።”

ስቲቭና ኡልፍ የሰጧቸው አስተያየቶች “የይሖዋ ሕግ ፍጹም ነው፤ ኃይልን ያድሳል። . . . የይሖዋ መመሪያዎች ትክክል ናቸው፤ ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ የይሖዋ ትእዛዝ ንጹሕ ነው፤ ዓይንን ያበራል” የሚለውን የመዝሙር 19:7, 8⁠ን ሐሳብ ያስታውሱናል።