በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

[ከግራ ወደ ቀኝ] ማርሴሎ፣ ዮማራ እና አይቨር። ሦስቱም በብሬይል የተዘጋጀውን የስፓንኛ አዲስ ዓለም ትርጉም በእጃቸው ይዘዋል

ፍቅር በተግባር ሲገለጽ አይተዋል

ፍቅር በተግባር ሲገለጽ አይተዋል

ዮማራ ማርሴሎና አይቨር ከተባሉ ወንድሞቿ ጋር በጓቴማላ ባለች ትንሽ መንደር ውስጥ ትኖራለች። ዮማራ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች፤ ከጊዜ በኋላ ወንድሞቿም ማጥናት ጀመሩ። ሆኖም ዮማራና ወንድሞቿ አንድ ተፈታታኝ ሁኔታ ነበረባቸው። ሦስቱም ዓይነ ስውር ከመሆናቸውም በላይ ብሬይል ማንበብ አይችሉም። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪያቸው የሚያጠኑትን ጽሑፍና በውስጡ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ያነብላቸው ነበር።

ዮማራና ወንድሞቿ ፈታኝ የሆነባቸው ሌላው ነገር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ነበር። በቅርባቸው ወዳለው የስብሰባ አዳራሽ ለመድረስ 40 ደቂቃ ያህል መጓዝ ነበረባቸው፤ ብቻቸውን ደግሞ ይህን ጉዞ ማድረግ አይችሉም። ሆኖም የጉባኤያቸው ወንድሞች በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲችሉ ዝግጅት አደረጉላቸው። በሳምንቱ መሃል በሚደረገው ስብሰባ ላይ የተማሪ ክፍል ማቅረብ ሲጀምሩ ደግሞ ወንድሞች ክፍላቸውን በቃላቸው መያዝ እንዲችሉ ይረዷቸው ነበር።

ግንቦት 2019 እነሱ በሚኖሩበት መንደር ውስጥ የጉባኤ ስብሰባዎች መካሄድ ጀመሩ። በወቅቱ በዘወትር አቅኚነት የሚያገለግሉ አንድ ባልና ሚስት ወደዚያ መንደር ተዛውረው ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት ዮማራንና ወንድሞቿን ብሬይል ማንበብና መጻፍ ለማስተማር ቆርጠው ተነሱ። ችግሩ ግን እነሱም ራሳቸው ብሬይል ማንበብና መጻፍ አይችሉም። ስለዚህ ስለ ብሬይልና ብሬይልን ለሌሎች ማስተማር ስለሚቻልበት መንገድ ለማወቅ ወደ ቤተ መጻሕፍት ሄዱ።

ማርሴሎ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ሐሳብ ሲሰጥ

በጥቂት ወራት ውስጥ ዮማራና ወንድሞቿ ብሬይል በደንብ ማንበብ ቻሉ፤ ይህም ተጨማሪ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። a አሁን ዮማራ፣ ማርሴሎና አይቨር ዘወትር አቅኚ ሆነው እያገለገሉ ነው። ማርሴሎ የጉባኤ አገልጋይ ሆኗል። ሳምንቱን ሙሉ የሚያሳልፉት በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተጠምደው ነው። ቅንዓታቸው ለሌሎች ጭምር የሚጋባ ነው።

ዮማራና ወንድሞቿ ጉባኤው ላደረገላቸው ፍቅራዊ እንክብካቤ በጣም አመስጋኝ ናቸው። ዮማራ እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ከእነሱ ጋር ከተገናኘንበት ከመጀመሪያው ጊዜ አንስቶ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር አሳይተውናል።” ማርሴሎ ደግሞ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል፦ “ጉባኤያችን ውስጥ ጥሩ ጓደኞች አሉን፤ ደግሞም እርስ በርሱ በፍቅር የተሳሰረ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ክፍል ነን።” ዮማራና ወንድሞቿ ምድር ወደ ገነትነት የምትለወጥበትን ጊዜ ለማየት ይናፍቃሉ።—መዝ. 37:10, 11፤ ኢሳ. 35:5

a ብሬይል ማንበብ ተማሩ (እንግሊዝኛ) የተባለው ብሮሹር ዓይነ ስውር ለሆኑ ወይም የማየት ችግር ላለባቸው ሰዎች ብሬይል ማንበብና መጻፍ ለማስተማር ታስቦ የተዘጋጀ ነው።