በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእምነታቸው ምሰሏቸው | ዳዊት

“ውጊያው የይሖዋ ነው”

“ውጊያው የይሖዋ ነው”

ዳዊት ከፊት ለፊቱ እየተጣደፉ የሚመጡ ወታደሮች ቢገፈታትሩትም ያን ተቋቁሞ ወደ ፊት እየተጓዘ ነው። በፍርሃት የራዱት እነዚህ ወታደሮች ከጦር ግንባሩ እየሸሹ ናቸው። ግን ይህን ያህል ያስፈራቸው ምንድን ነው? ዳዊት በፍርሃት የራዱት እነዚህ ወታደሮች በተደጋጋሚ አንድ ቃል ሲጠሩ ሰምቷቸው መሆን አለበት። የሚጠሩትም የአንድ ሰው ስም ነው። ከዚያም ዳዊት ሸለቆው ውስጥ ደረቱን ነፍቶ የቆመ ሰው ተመለከተ፤ ሰውየው ዳዊት ከዚህ በፊት ካያቸው ሰዎች ሁሉ እጅግ ግዙፉ ሳይሆን አይቀርም።

ይህ ሰው ጎልያድ ነበር! ዳዊት ወታደሮቹ ይህን ሰው ለምን እንደፈሩት ገባው፤ ሰውየው እጅግ ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ ተራራ ያክላል። የለበሰውን የጦር ትጥቅ ሳይጨምር ክብደቱ ከሁለት ትላልቅ ሰዎች ሳይበልጥ አይቀርም። ሰውየው ከባድ የጦር ትጥቅ የለበሰ ሲሆን እጅግ ጠንካራና ልምድ ያለው ተዋጊም ነው። ጎልያድ ድምፁን ከፍ አድርጎ መፎከር ጀመረ። በዚያ በሚያስገመግም ድምፁ በእስራኤል ሠራዊትና በንጉሣቸው በሳኦል ላይ ሲሳለቅ ድምፁ በኮረብቶቹ ላይ ሲያስተጋባ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ከእሱ ጋር ሊጋጠም የሚችል አንድ ሰው መርጠው ከላኩ ጦርነቱ በዚያው እንደሚቋጭ በመንገር እስራኤላውያንን ተገዳደራቸው!—1 ሳሙኤል 17:4-10

እስራኤላውያን በፍርሃት ርደዋል። ንጉሥ ሳኦልም ፈርቷል። ዳዊት እስራኤላውያን በዚህ ሁኔታ ከአንድ ወር በላይ እንደቆዩ ተገነዘበ! ጎልያድ በእስራኤላውያን ላይ በየቀኑ ሲሳለቅ የፍልስጤምና የእስራኤል ሠራዊት ባሉበት ተፋጠው ቆመው ነበር። ጉዳዩ ዳዊትን በጣም አበሳጨው። የዳዊትን ሦስት ታላላቅ ወንድሞች ጨምሮ የእስራኤል ንጉሥና ወታደሮቹ በፍርሃት ሲርበደበዱ ማየት እንዴት የሚያሳፍር ነው! በዳዊት አመለካከት ይህ አረማዊ ሰው የእስራኤልን ሠራዊት እያዋረደ ብቻ አልነበረም፤ የእስራኤልን አምላክ ይሖዋንም እየተሳደበ ነው! ታዲያ ገና ለጋ ወጣት የሆነው ዳዊት ምን ማድረግ ይችላል? እኛስ ዳዊት ካሳየው እምነት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?—1 ሳሙኤል 17:11-14

“ቀባው፤ የመረጥኩት እሱን ነው!”

እስቲ ይህ ከመሆኑ ከብዙ ወራት በፊት የተፈጸመን አንድ ሁኔታ እንመልከት። ዳዊት ቤተልሔም አቅራቢያ በሚገኙ ኮረብታዎች ላይ የአባቱን በጎች እየጠበቀ ፀሐይዋ መጥለቅ ጀመረች። ዳዊት የቀይ ዳማ፣ ዓይኑ የሚያምር፣ ንቁና መልከ መልካም ወጣት ነው። ጭር ሲል ጊዜውን የሚያሳልፈው በገና በመጫወት ነው። በአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ላይ የሚታየው ውበት ስለ እነዚህ ነገሮች እንዲዘምር ያነሳሳው ነበር፤ ለብዙ ሰዓታት ልምምድ ያደርግ ስለነበር የሙዚቃ ችሎታውም እየተሻሻለ ሄዷል። በዚህ ቀን አመሻሹ ላይ ዳዊት ወደ ቤት ተጠራ። አባቱ በአስቸኳይ ሊያገኘው ፈልጓል።—1 ሳሙኤል 16:12

ቤት ሲደርስ አባቱ እሴይ፣ ከአንድ አረጋዊ ሰው ጋር እያወራ ነበር። ይህ ሰው ታማኙ ነቢይ ሳሙኤል ነበር። ሳሙኤል የመጣው ከእሴይ ልጆች መካከል አንዱን ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባው ይሖዋ ስለላከው ነው! ሳሙኤል ሰባቱን የዳዊት ታላላቅ ወንድሞች ያያቸው ቢሆንም ይሖዋ አንዳቸውንም እንዳልመረጠ ለሳሙኤል በግልጽ ነገረው። ዳዊት ሲመጣ ግን ይሖዋ “ቀባው፣ የመረጥኩት እሱን ነው!” ብሎ ለሳሙኤል ነገረው። ከዚያም ሳሙኤል የዳዊት ታላላቅ ወንድሞች ሁሉ እያዩ በልዩ ዘይት የተሞላ አንድ ቀንድ ከፈተና ዘይቱን በዳዊት ራስ ላይ አፈሰሰው። ዳዊት ከተቀባ በኋላ ሕይወቱ ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከዚያም ቀን አንስቶ የይሖዋ መንፈስ ለዳዊት ኃይል ሰጠው” በማለት ይናገራል።—1 ሳሙኤል 16:1, 5-11, 13

ዳዊት የዱር አራዊቶችን ለማሸነፍ የረዳው ይሖዋ እንደሆነ በትሕትና አምኗል

ታዲያ ዳዊት ሥልጣኑን ወዲያውኑ ለማግኘት ጓጉቶ ይሆን? በፍጹም፤ ዳዊት ከፍተኛ ኃላፊነት መቀበል የሚችልበትን ትክክለኛ ጊዜ የይሖዋ መንፈስ እስኪያሳውቀው ድረስ ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነበር። እስከዚያው ድረስ ግን ዝቅ ተደርጎ የሚታየውን ሥራ ማለትም እረኝነቱን ቀጠለ። ዳዊት ድፍረት የሚጠይቀውን ይህን ሥራ በትጋት ያከናውን ነበር። የአባቱ በጎች ከአንዴም ሁለቴ ይኸውም አንድ ጊዜ በአንበሳ ሌላ ጊዜ ደግሞ በድብ ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ነበር። ዳዊት በጎቹን ለመንጠቅ የመጡትን እነዚህን አውሬዎች ከሩቅ በማባረር ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ የአባቱን ምስኪን በጎች ለመታደግ ፊት ለፊት ተጋፍጧል። በሁለቱም ጊዜያት እነዚያን አስፈሪ አራዊት ብቻውን ታግሎ ገድሏቸዋል!—1 ሳሙኤል 17:34-36፤ ኢሳይያስ 31:4

ከጊዜ በኋላ ዳዊት እንደገና ተጠራ። ዝናው ንጉሥ ሳኦል ጆሮ ደርሶ ነበር። ሳኦል አሁንም ኃይለኛ ተዋጊ ቢሆንም አምላክ የሰጠውን መመሪያ በመጣሱ የይሖዋን ሞገስ አጥቷል። ይሖዋ መንፈሱን ስለወሰደበት ንጉሡን ክፉ መንፈስ ብዙ ጊዜ ያሠቃየው ነበር፤ ይህ መንፈስ ቁጡ፣ ተጠራጣሪና ዓመፀኛ ያደርገዋል። ይህ ክፉ መንፈስ ሲመጣበት ዘና የሚያደርገው ሙዚቃ ብቻ ነበር። ከሳኦል አገልጋዮች አንዳንዶቹ ዳዊት ሙዚቃ በመጫወትና በመዋጋት ረገድ ያተረፈውን ዝና ሰምተው ነበር። ስለዚህ ዳዊት ተጠርቶ ወደ ቤተ መንግሥቱ መጣ፤ ብዙም ሳይቆይ ዳዊት ከሳኦል ቤተ መንግሥት ሙዚቀኞችና ጋሻ ጃግሬዎች አንዱ ሆነ።—1 ሳሙኤል 15:26-29፤ 16:14-23

በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች ዳዊት በዚህ ረገድ ካሳየው እምነት ብዙ መማር ይችላሉ። ዳዊት ትርፍ ጊዜውን ወደ ይሖዋ እንዲቀርብ የሚረዱትን ነገሮች በመከታተል ያሳልፍ እንደነበር ልብ በል። በተጨማሪም አስፈላጊ የሆኑ ችሎታዎችን በትዕግሥት ያዳበረ ሲሆን ይህም በቀላሉ ሥራ እንዲያገኝ ረድቶታል። ከሁሉ በላይ ግን የይሖዋ መንፈስ ለሚሰጠው አመራር ቀና ምላሽ ሰጥቷል። ሁላችንም ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ነው!—መክብብ 12:1

“በዚህ ሰው የተነሳ የማንም ሰው ልብ አይቅለጥ”

ዳዊት ንጉሥ ሳኦልን እያገለገለ በነበረበት ወቅት፣ በጎቹን ለመጠበቅ ወደ ቤቱ የሚመለስበት ጊዜ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ በጎቹን እየጠበቀ ረዘም ያለ ጊዜ ይቆይ ነበር። እሴይ፣ በሳኦል ሠራዊት ውስጥ እያገለገሉ የነበሩትን ሦስቱን ታላላቅ ልጆቹን እንዲጠይቅ ዳዊትን የላከው በዚህ ጊዜ ነበር። ዳዊትም በታዛዥነት ለወንድሞቹ የሚሆን ስንቅ ይዞ ወደ ኤላ ሸለቆ ሄደ። እዚያ ሲደርስ ሁለቱ ሠራዊቶች በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው ተፋጥጠው አገኛቸው። ሠራዊቱ ሰፊ በሆነው ሸለቆ አናት ላይ በተለያየ አቅጣጫ ሰፍረው ነበር።—1 ሳሙኤል 17:1-3, 15-19

ዳዊት ይህን ሁኔታ በቸልታ አላለፈውም። ሕያው አምላክ የሆነው የይሖዋ ሠራዊት አንድን ሰው፣ ያውም ጣዖት አምላኪ የሆነን ሰው ፈርቶ እንዴት ይሸሻል? ዳዊት የጎልያድን ግድድር የተመለከተው በቀጥታ በይሖዋ ላይ እንደተሰነዘረ ስድብ አድርጎ ነው። ስለዚህ ጎልያድን ማሸነፍ እንደሚቻል ከወታደሮቹ ጋር በጋለ ስሜት ማውራት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ የዳዊት ታላቅ ወንድም የሆነው ኤልያብ ዳዊት የተናገረው ቃል ጆሮው ውስጥ ጥልቅ አለ። ከዚያም ታናሽ ወንድሙ ዳዊት የመጣው፣ ውጊያውን ለማየት እንደሆነ በቁጣ ተናገረ። ይሁን እንጂ ዳዊት “ቆይ አሁን ምን አጠፋሁ? ጥያቄ እኮ ነው የጠየቅኩት!” በማለት መለሰለት። ከዚያም ጎልያድን ማሸነፍ እንደሚቻል በእርግጠኝነት መናገሩን ቀጠለ፤ ይህን የሰማ አንድ ሰው ለሳኦል ነገረው። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ዳዊትን ወደ እሱ እንዲያመጡት ትእዛዝ አስተላለፈ።—1 ሳሙኤል 17:23-31

ዳዊት ጎልያድን አስመልክቶ “በዚህ ሰው የተነሳ የማንም ሰው ልብ አይቅለጥ” በማለት ለሳኦል አበረታች ሐሳብ ተናገረ። ደግሞም ሳኦልና አብረውት ያሉት ሰዎች በጎልያድ የተነሳ ወኔ ከድቷቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ከዚያ ግዙፍ ሰው ጋር አወዳድረው ይሆናል፤ ምናልባትም ቁመታቸው ሆዱ ወይም ደረቱ ጋር እንኳ እንደማይደርስ ተሰምቷቸው በፍርሃት ሳይርዱ አልቀረም። የጦር ልብስ የለበሰው ይህ ግዙፍ ሰው በቀላሉ እንደሚጨፈልቃቸው ተሰምቷቸዋል። ዳዊት ግን እንደዚህ አላሰበም። በኋላ ላይ እንደምንመለከተው እሱ ሁኔታውን ያየው ፈጽሞ በተለየ መንገድ ነው። በመሆኑም ጎልያድን መግጠም እንደሚፈልግ ተናገረ።—1 ሳሙኤል 17:32

“ሳኦል ግን ዳዊትን ‘አንተ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነህ፤ እሱ ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነው፤ ስለዚህ ይህን ፍልስጤማዊ ልትገጥመው አትችልም’” በማለት ተቃወመው። በእርግጥ ዳዊት አንድ ፍሬ ልጅ ነበር? አልነበረም፤ ሳኦል ይህን የተናገረው ዳዊት ሠራዊቱን ለመቀላቀል ዕድሜው ስላልደረሰ ወይም ሲታይ በጣም ትንሽ ልጅ ስለሚመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ ዳዊት ከዚህ ቀደም ኃያል ተዋጊ በመሆኑ ይታወቅ ስለነበር በዚያ ወቅት ዕድሜው በአሥራዎቹ መጨረሻ ላይ ሊሆን ይችላል።—1 ሳሙኤል 16:18፤ 17:33

ዳዊት ከአንበሳና ከድብ ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ተሞክሮ በመናገር ሳኦልን ለማሳመን ሞከረ። ታዲያ ዳዊት ጉራ እየነዛ ነበር? በጭራሽ። ዳዊት ከአራዊት ጋር ሲታገል እንዲያሸንፍ የረዳው ማን እንደሆነ በሚገባ ያውቃል። በመሆኑም “ከአንበሳና ከድብ ጥፍር የታደገኝ ይሖዋ አሁንም ከዚህ ፍልስጤማዊ እጅ ይታደገኛል” በማለት ተናገረ። በመጨረሻም ሳኦል በዳዊት ሐሳብ በመስማማት “እሺ ሂድ፤ ይሖዋ ከአንተ ጋር ይሁን” ብሎ አሰናበተው።—1 ሳሙኤል 17:37

እንደ ዳዊት ያለ እምነት እንዲኖርህ ትፈልጋለህ? ዳዊት እምነቱን የገነባው በምናባዊ ነገር ወይም በምኞት ላይ እንዳልሆነ ልብ በል። ዳዊት በአምላኩ ላይ እምነት ሊኖረው የቻለው እውቀትና ተሞክሮ ስለነበረው ነው። ይሖዋ ለሕዝቡ ከለላ የሚሆንና የገባውን ቃል የሚፈጽም አፍቃሪ አምላክ መሆኑን አውቆ ነበር። እኛም እንዲህ ያለ እምነት እንዲኖረን ከፈለግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገለጸው አምላክ ትምህርት መቅሰማችንን መቀጠል ይኖርብናል። በተማርነው መሠረት ስንኖር የምናገኛቸው መልካም ውጤቶች ደግሞ እምነታችንን ያጠናክሩታል።—ዕብራውያን 11:1

“ይሖዋ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጥሃል”

መጀመሪያ ላይ ሳኦል፣ ዳዊት የእሱን የጦር ትጥቅ እንዲለብስ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። የጦር ትጥቁ የጎልያድ ዓይነት ይመስላል፤ ጥሩሩ ከተነባበሩ ጠፍጣፋ መዳቦች የተሠራ ሳይሆን አይቀርም። ዳዊት ይህን ትልቅና የማይመች የጦር ትጥቅ ለብሶ ለመራመድ ሲሞክር እንደማያዋጣው ተገነዘበ። ወታደራዊ ሥልጠና ስላልወሰደ እንዲህ ያለ ልብስ ለብሶ አያውቅም፤ በተለይ ደግሞ በእስራኤል ውስጥ ካሉት ሰዎች ሁሉ ረጅም የሆነው የሳኦል ትጥቅ ሊሆነው አይችልም። (1 ሳሙኤል 9:2) ስለዚህ ሁሉንም አወላልቆ የራሱን ልብስ በመልበስ በጎቹን ለመጠበቅ የሚጠቀምባቸውን መሣሪያዎች አነሳ።—1 ሳሙኤል 17:38-40

ዳዊት ኮረጆውን ትከሻው ላይ አንግቶ የእረኛ በትሩንና ወንጭፉን ያዘ። ወንጭፍ ብዙ የሚጠቅም መሣሪያ ባይመስልም ኃይለኛ የጦር መሣሪያ ነው። ወንጭፍ በድንጋይ ማስቀመጫው ጫፍና ጫፍ ላይ ሁለት ረጃጅም ጠፈሮች ያሉት መሣሪያ ነው፤ እረኞች ይህን መሣሪያ አዘውትረው ይጠቀሙበታል። እረኛው ድንጋዩን መሃል ላይ ያደርግና እጁን ከፍ አድርጎ ያሽከረክረዋል፤ ከዚያም አንዱን ጠፍር ሲለቀው ድንጋዩ በከፍተኛ ፍጥነት ተወርውሮ ዒላማውን ይመታል። ይህ መሣሪያ በጣም ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ ወንጭፍ የሚያስወነጭፉ ቡድኖች በጦር ሠራዊት ውስጥ ይካተቱ ነበር።

ዳዊት ትጥቁን ከታጠቀ በኋላ ጠላቱን ለመግጠም ገሰገሰ። ዳዊት በደረቅ ሸለቆ ውስጥ አጎንብሶ አምስት ትንንሽ ድንጋዮችን እየለቀመ ከልብ የመነጨ ጸሎት ሲያቀርብ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ከዚያም ወደ ፍልሚያው ሜዳ እየተራመደ ሳይሆን እየሮጠ ሄደ!

ጎልያድ ሊገጥመው የመጣውን ሰው ሲያይ ምን ተሰማው? “ዳዊትን ትኩር ብሎ ሲያየው ዳዊት የቀይ ዳማና መልከ መልካም የሆነ አንድ ፍሬ ልጅ ስለነበር ናቀው።” ጎልያድ በሚያስገመግም ድምፅ “በትር ይዘህ ወደ እኔ የምትመጣው እኔ ውሻ ነኝ?” አለው። ጎልያድ የዳዊትን በትር እንጂ የያዘውን ወንጭፍ ልብ እንዳላለው ግልጽ ነው። ዳዊትን በፍልስጤማውያን አማልክት ስም ረገመው፤ ከዚያም የዳዊትን ሬሳ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እንደሚሰጥ ዛተ።—1 ሳሙኤል 17:41-44

ዳዊት ለጎልያድ የሰጠው መልስ እስከ ዛሬ ድረስ ታላቅ የእምነት መግለጫ ሆኖ ይጠቀሳል። ይህ ወጣት ጎልያድን “አንተ ሰይፍ፣ ጭሬና ጦር ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተሳለቅክበት፣ የእስራኤል ተዋጊዎች አምላክ በሆነው በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ስም እመጣብሃለሁ” ብሎ ሲናገረው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ዳዊት የሰው አቅምም ሆነ የጦር መሣሪያ በይሖዋ ዘንድ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ተገንዝቧል። ጎልያድ ይሖዋ አምላክን ስለናቀ መልስ የሚሰጠው ይሖዋ ነበር። ዳዊት እንደተናገረው “ውጊያው የይሖዋ ነው።”—1 ሳሙኤል 17:45-47

ዳዊት የጎልያድን ግዝፈት ወይም የጦር መሣሪያዎች ሳያይ ቀርቶ አይደለም። ሆኖም ዳዊት እነዚህ ነገሮች ወኔውን እንዲሰልቡበት አልፈቀደም። ሳኦልና ሠራዊቱ የፈጸሙትን ስህተት አልደገመም። ራሱን ከጎልያድ ጋር አላነጻጸረም። ከዚህ ይልቅ ጎልያድን የተመለከተው ከይሖዋ አንጻር ነው። ጎልያድ ቁመቱ 2.9 ሜትር በመሆኑ ከሰዎች ጋር ሲወዳደር ተራራ ሊመስል ይችላል፤ ያም ቢሆን ከአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በእርግጥም ጎልያድ ከይሖዋ ጋር ሲወዳደር እንደማንኛውም ሰው ከአንዲት ትንኝ አይበልጥም፤ በመሆኑም ይሖዋ በቀላሉ ሊጨፈልቀው ይችላል!

ዳዊት ከኮረጆው ውስጥ ድንጋይ እያወጣ ወደ ጠላቱ ሮጠ። ድንጋዩን ወንጭፉ ላይ በማስቀመጥ እጁን ከፍ አድርጎ ወንጭፉን በኃይል ማሽከርከር ጀመረ። ጎልያድም ምናልባትም ከጋሻ ጃግሬው ኋላ ሆኖ ወደ ዳዊት ገሰገሰ። ጎልያድ ቁመቱ ረጅም መሆኑ ሳይጎዳው አልቀረም፤ ምክንያቱም ጋሻ ጃግሬው ቁመቱ እንደማንኛውም ሰው ስለሆነ በያዘው ጋሻ የጎልያድን ራስ መከለል አልቻለም። ዳዊት ያነጣጠረውም በጎልያድ ራስ ላይ ነበር።—1 ሳሙኤል 17:41

ዳዊት የትኛውም ግዙፍ ሰው ቢሆን ከይሖዋ ጋር ሲወዳደር ኢምንት እንደሆነ ተገንዝቧል

ከዚያም ዳዊት ድንጋዩን ወነጨፈው። ድንጋዩ ወደ ዒላማው በሚምዘገዘግበት ወቅት የነበረው ፀጥታ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ዳዊት ሁለተኛ መወንጨፍ እንዳያስፈልገው ያደረገው ይሖዋ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ድንጋዩ የጎልያድን ግንባር በርቅሶ በመግባት ዒላማውን መታ። ግዙፉ ሰው በአፍጢሙ ተደፋ! ጋሻ ጃግሬው ይህን ሲያይ በድንጋጤ ሳይፈረጥጥ አልቀረም። ዳዊት ወደ ፊት ቀርቦ የጎልያድን ሰይፍ በማንሳት የዚያን ግዙፍ ሰው አንገት ቆረጠው።—1 ሳሙኤል 17:48-51

በመጨረሻም ሳኦልና ወታደሮቹ ድፍረት አገኙ። በኃይል እየጮኹ ፍልስጤማውያንን ለመግጠም ገሰገሱ። ውጊያው ዳዊት አስቀድሞ እንደተናገረው ሆነ፤ ጎልያድን “ይሖዋ . . . ሁላችሁንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣችኋል” ብሎት ነበር።—1 ሳሙኤል 17:47, 52, 53

በዛሬው ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች ቃል በቃል በጦርነት አይካፈሉም። ጦርነት የሚደረግበት ዘመን አብቅቷል። (ማቴዎስ 26:52) ያም ሆኖ ዳዊትን በእምነቱ መምሰል ይኖርብናል። እንደ ዳዊት ሁሉ እኛም ይሖዋ እውን ሆኖ ሊታየን ይገባል፤ እንዲሁም ሊገለገልና አክብሮታዊ ፍርሃት ልናሳየው የሚገባ አምላክ እሱ ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ ችግሮቻችን በጣም ገዝፈው ይታዩን ይሆናል፤ ያም ቢሆን እነዚህ ችግሮች ገደብ የለሽ ኃይል ባለው በይሖዋ ፊት እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። ይሖዋ አምላካችን እንዲሆን ከመረጥንና ዳዊት እንዳደረገው በእሱ ላይ እምነት ካሳደርን ምንም ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ወይም ችግር ሊያስፈራን አይችልም። ከይሖዋ አቅም በላይ የሆነ ምንም ነገር የለም!