በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለጎብኚዎች ክፍት የሆነው “በዓለት” ላይ ያለ ቤት

ለጎብኚዎች ክፍት የሆነው “በዓለት” ላይ ያለ ቤት

የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የኅትመት ሥራ የሚካሄድባቸው 15 ቅርንጫፍ ቢሮዎች አሏቸው። ከእነዚህ መካከል አንዱ በሴልተርስ፣ ጀርመን ውስጥ ሽታይንፌልስ (በጀርመንኛ “የድንጋይ ዓለት” ማለት ነው) በተባለ ቦታ የሚገኘው የመካከለኛው አውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮ ነው።

ግንቦት 23-25, 2014 የመካከለኛው አውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች፣ ነጋዴዎችና ባለሥልጣናት ቢሮውን እንዲጎበኙ ጋብዞ ነበር። ቅርንጫፍ ቢሮው በይፋ የተመረቀው ሚያዝያ 21, 1984 ስለነበር ለጎብኚዎች የተደረገው ዝግጅት “30 ዓመታት በሴልተርስ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር።

በዚህ ወቅት ከ3,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቅርንጫፍ ቢሮውን ጎብኝተዋል። ወደ 30 ለሚጠጉ ዓመታት በከተማው አስተዳደር ውስጥ የሠሩት ከንቲባ “የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮ መጎብኘት ሁሌም ቢሆን አስደሳች ነው” ብለዋል። አክለውም “በሽታይንፌልስ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ከ1979 እስከ 1984 ባሉት ዓመታት በፍጥነት ተሠርቶ መጠናቀቁ አሁንም ድረስ ያስገርመኛል” ብለዋል።

የጉብኝቱ ዋና ዋና ገጽታዎች

በጉብኝቱ ወቅት ከሚታዩት ክፍሎች አንዱ “የይሖዋ ሕዝቦች በመካከለኛው አውሮፓ” የሚል ርዕስ ነበረው። ጎብኚዎቹ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ አካባቢ ላለፉት 120 ዓመታት ያከናወኑትን ሥራ ተመልክተዋል። ታሪካዊ ክንውኖች የሚታዩበት በቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኘው ይህ ክፍል በአሁኑም ወቅት ለጉብኝት ክፍት ነው።

ሌላኛው ክፍል ደግሞ እንደ ልብ የማይገኙና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው መጽሐፍ ቅዱሶች የሚታዩበት ነበር። ከእነዚህ መካከል በ1534 የታተመው ሙሉው የጀርመንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ እትምና በ1599 በኤሊአስ ሁተ የተዘጋጀው በርካታ ቋንቋዎችን ይኸውም 12 ቋንቋዎችን የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰነ ክፍል ይገኙበታል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በዛሬው ጊዜ ያላቸውን ጥቅም የሚያጎሉ ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ ሰንጠረዦችና ቪዲዮዎች ተዘጋጅተው ነበር።

ጎብኚዎቹ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ የሚኖሩትና የሚሠሩት ከ1,000 በላይ የሚሆኑ ወንዶችና ሴቶች በየዕለቱ ምን እንደሚያከናውኑም ተመልክተዋል። “አኗኗራችን ምን ይመስላል?” የሚል ስያሜ በተሰጠው በጉብኝቱ የመጀመሪያ ክፍል ላይ እንግዶቹ አንዳንዶቹን የመኖሪያ ክፍሎች ጎብኝተዋል። ከዚያም በመመገቢያ አዳራሹ ውስጥ ምግብ የተጋበዙ ሲሆን በኋላም በአትክልቱ ቦታ ዘና ብለዋል። አንድ ጎብኚ “አካባቢው ያለው ውበት ለማመን ያዳግታል” በማለት አድናቆቱን ገልጿል።

“ኅትመት” የሚል ርዕስ ባለው በቀጣዩ የጉብኝቱ ክፍል ደግሞ የማተሚያ፣ የመጠረዣና የጽሑፍ መላኪያ ክፍሎችን ጎብኝተዋል። ጎብኚዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች የሚታተሙት፣ የሚጠረዙትና ከ50 ወደሚበልጡ አገሮች የሚላኩት እንዴት እንደሆነ ተመልክተዋል። አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ነው ብዬ አላስብም ነበር። ጽሑፎቻቸው በመላው ዓለም ከዳር እስከ ዳር ይሰራጫሉ። ይህን ሥራ የሚያከናውኑት ደግሞ ፈቃደኛ ሠራተኞች መሆናቸው ያስገርማል።”

ጎብኚዎቹ ስለ jw.org ጥሩ ግንዛቤ አግኝተዋል

ሌላው ልዩ ገጽታ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ ድረ ገጽ የሚያሳየው jw.org የተለጠፈበት ሰሌዳ ነው። ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ለማስጎብኛ የሚያገለግሉትን መረጃዎች እንዲሁም ቪዲዮዎችን ተመልክተዋል፤ ለበርካታ ጥያቄዎቻቸውም መልስ አግኝተዋል።

አብዛኞቹ ጎብኚዎች ዓለም አቀፍ ይዘት ያለውን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በተመለከተ አዲስ ግንዛቤ በማግኘታቸው ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ለሥራው ከፍተኛ አድናቆት እንዳደረባቸው የገለጹ ሲሆን ፊታቸውም ላይ ፈገግታ ይታይ ነበር። ከጎብኚዎቹ መካከል አንዱ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቷል፦ “ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ የተሳሳቱ አመለካከቶች ነበሩኝ። አስተሳሰቤን ማስተካከል እንዳለብኝ ምንም ጥያቄ የለውም።” አንዲት ሴት ደግሞ በተደጋጋሚ “ይህ ቀን የነበረብኝን ጭፍን ጥላቻ እንዳስወግድ ረድቶኛል” ብላለች።

a እስከ 2014 ያለው አኃዝ

b እስከ 2014 ያለው አኃዝ

c እስከ 2014 ያለው አኃዝ