በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አምላክ ጽንፈ ዓለምን መፍጠር የጀመረው መቼ ነው?

አምላክ ጽንፈ ዓለምን መፍጠር የጀመረው መቼ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ጽንፈ ዓለምን መፍጠር የጀመረው መቼ እንደሆነም ሆነ ይህ ሂደት ምን ያህል ጊዜ እንደፈጀ አይናገርም። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚናገረው ነገር ቢኖር ‘በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን እንደፈጠረ’ ብቻ ነው። (ዘፍጥረት 1:1) መጽሐፍ ቅዱስ “መጀመሪያ” የተባለው ጊዜ የትኛውን ጊዜ እንደሚያመለክት አይናገርም። ሆኖም በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ በቅደም ተከተል ተመዝግበው በሚገኙት ክንውኖች መሠረት ይህ ጊዜ ከስድስቱ ክፍለ ጊዜያት ወይም የፍጥረት “ቀናት” በፊት ያለ ጊዜ ነው።

 ስድስቱ የፍጥረት ቀናት ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ ያላቸው ቀናት ናቸው?

 አይደሉም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቀን” የሚለው ቃል እንደየአገባቡ የተለያዩ የጊዜ ርዝማኔዎችን ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ አንድ ዘገባ የፍጥረት ሥራዎች የተከናወኑበትን ጊዜ በአጠቃላይ እንደ አንድ ቀን አድርጎ ገልጾታል።—ዘፍጥረት 2:4

 በስድስቱ የፍጥረት ቀናት ውስጥ ምን ተከናውኗል?

 አምላክ “ቅርጽ አልባና ባድማ” የነበረችውን ምድርን ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሊኖሩ ወደሚችሉባት አመቺ ፕላኔት ቀየረ። (ዘፍጥረት 1:2) ከዚያም በምድር ላይ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ፈጠረ። መጽሐፍ ቅዱስ በፍጥረት ቀናት ወይም ክፍለ ጊዜያት ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች በስድስት ቡድኖች ይከፍላቸዋል፦

  •  አንደኛ ቀን፦ አምላክ ብርሃን ወደ ምድር ገጽ እንዲደርስ በማድረግ ቀንና ሌሊት እንዲፈራረቅ አደረገ።—ዘፍጥረት 1:3-5

  •  ሁለተኛ ቀን፦ አምላክ ጠፈርን ፈጠረ፤ ይህን ያደረገው በምድር ገጽ ላይ ያለውን ውኃ ከምድር ገጽ በላይ ካለው ውኃ በመለየት ነው።—ዘፍጥረት 1:6-8

  •  ሦስተኛ ቀን፦ አምላክ ደረቅ መሬት እንዲገለጥ አደረገ። በተጨማሪም ተክሎችን ፈጠረ።—ዘፍጥረት 1:9-13

  •  አራተኛ ቀን፦ አምላክ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ብርሃን ሰጪ አካላት ሆነው ከምድር ገጽ እንዲታዩ አደረገ።—ዘፍጥረት 1:14-19

  •  አምስተኛ ቀን፦ አምላክ ውኃ ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታትንና የሚበርሩ ፍጥረታትን ፈጠረ።—ዘፍጥረት 1:20-23

  •  ስድስተኛ ቀን፦ አምላክ መሬት ላይ የሚኖሩ እንስሳትንና ሰዎችን ፈጠረ።—ዘፍጥረት 1:24-31

 ስድስተኛው ቀን ካበቃ በኋላ አምላክ ከዚህ ሥራ አረፈ፤ ማለትም መፍጠሩን አቆመ።—ዘፍጥረት 2:1, 2

 የዘፍጥረት ዘገባ ከሳይንስ አንጻር ትክክል ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ዓለም ስለተፈጠረበት መንገድ የያዘው ዘገባ ዝርዝር ሳይንሳዊ ትንታኔ አይሰጥም። ከዚህ ይልቅ በጥንት ዘመን የኖሩ ሰዎች እንኳ አምላክ የተለያዩ ነገሮችን የፈጠረበትን መሠረታዊ ቅደም ተከተል በቀላሉ እንዲረዱ የሚያስችል መረጃ ይዟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የፍጥረት ዘገባ በሳይንስ ከተረጋገጡ እውነታዎች ጋር አይጋጭም። የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት ሮበርት ጃስትሮ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “መጽሐፍ ቅዱስና ሥነ ፈለክ ስለ ፍጥረት አመጣጥ የሚሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ ቢለያይም መሠረታዊ ሐሳባቸው ግን ተመሳሳይ ነው፤ እስከ ሰው ልጅ መገኘት ድረስ ያሉት ተከታታይ ክንውኖች የጀመሩበት ቁርጥ ያለ ጊዜ አላቸው።”

 ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የተፈጠሩት መቼ ነው?

 ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት “በመጀመሪያ . . . ሰማያት” ሲፈጠሩ አብረው ተፈጥረዋል። (ዘፍጥረት 1:1) ሆኖም ከሁኔታዎች መረዳት እንደምንችለው፣ ከባቢ አየሩ ጥቅጥቅ ያለ ስለነበር ብርሃናቸው ወደ ምድር ገጽ አይደርስም ነበር። (ዘፍጥረት 1:2) ስለዚህ በአንደኛው ቀን ላይ ከባቢ አየሩን ሰንጥቆ የሚገባው ብርሃን መታየት ቢጀምርም የብርሃኑ ምንጭ ገና አልታወቀም ነበር። በአራተኛው ቀን ላይ ከባቢ አየሩ የጠራ ይመስላል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጊዜ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ‘በምድር ላይ ማብራት’ እንደጀመሩ ይናገራል፤ ይህ አገላለጽ እነዚህን አካላት ከምድር ላይ ሆኖ ማየት እንደተቻለ የሚያመለክት መሆን አለበት።—ዘፍጥረት 1:17

 በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የምድር ዕድሜ ምን ያህል ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምድር ዕድሜ የሚናገረው ነገር የለም። ዘፍጥረት 1:1 የሚናገረው ምድርን ጨምሮ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም መጀመሪያ እንዳለው ብቻ ነው። ይህ ሐሳብ በሳይንስ ከተረጋገጡ እውነታዎችም ሆነ ሳይንቲስቶች ስለ ምድር ዕድሜ ከሚሰጧቸው መላ ምቶች ጋር አይጋጭም።