በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ዘፀአት 20:12—“አባትህንና እናትህን አክብር”

ዘፀአት 20:12—“አባትህንና እናትህን አክብር”

 “አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር።”—ዘፀአት 20:12 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።”—ዘፀአት 20:12 የ1954 ትርጉም

የዘፀአት 20:12 ትርጉም

 አምላክ በጥንት ጊዜ የነበሩትን እስራኤላውያን ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ አዟቸው ነበር። ይህን ትእዛዝ ከፈጸሙ ዕድሜያቸው እንደሚረዝም ቃል ገብቶላቸዋል፤ ይህም ትእዛዙን ለመፈጸም የሚያነሳሳ ተጨማሪ ምክንያት ይሆናቸዋል። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠውን ሕግ ማለትም የሙሴን ሕግ መታዘዝ አይጠበቅባቸውም፤ ሆኖም የአምላክ መሥፈርት ዛሬም አልተለወጠም። ከሕጉ በስተጀርባ ያለው መሠረታዊ ሐሳብ አሁንም ስለሚሠራ ክርስቲያኖች ለዚህ ሕግ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል።—ቆላስይስ 3:20

 ሁሉም ልጆች፣ ወጣትም ይሁኑ አዋቂ ወላጆቻቸውን በመታዘዝ እነሱን እንደሚያከብሩ ያሳያሉ። (ዘሌዋውያን 19:3፤ ምሳሌ 1:8) ልጆች አድገው የራሳቸውን ልጆች ከወለዱ በኋላም እንኳ ወላጆቻቸውን መውደዳቸውንና መንከባከባቸውን መቀጠል አለባቸው። ለምሳሌ ወላጆቻቸው ሲያረጁ ሊጦሯቸው አልፎ ተርፎም አስፈላጊውን ቁሳዊ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል።—ማቴዎስ 15:4-6፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8

 እስራኤላውያን ልጆች አባታቸውን እና እናታቸውን እንዲያከብሩ ይጠበቅባቸው እንደነበር አስታውስ፤ አባታቸውን ብቻ ሳይሆን እናታቸውን ጭምር በማክበር፣ እናት በቤተሰብ ውስጥ ያላትን ወሳኝ ሚና እንደተገነዘቡ ያሳያሉ። (ምሳሌ 6:20፤ 19:26) በዛሬው ጊዜ ያሉ ልጆችም እንዲህ ሊያደርጉ ይገባል።

 ወላጆችን ስለማክበር የተሰጠው ትእዛዝ ገደብ አለው። እስራኤላውያን ልጆች የአምላክን ትእዛዝ የሚያስጥሳቸው ከሆነ ወላጆቻቸውንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ሰው እንዲታዘዙ አይጠበቅባቸውም ነበር። (ዘዳግም 13:6-8) ዛሬም በተመሳሳይ ክርስቲያኖች ‘ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያቸው አድርገው ሊታዘዙ ይገባል።’—የሐዋርያት ሥራ 5:29

 አምላክ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ ወላጆቻቸውን የሚያከብሩ ልጆች እሱ በሰጣቸው ምድር ላይ ‘ዕድሜያቸው እንደሚረዝምና መልካም እንደሚሆንላቸው’ ቃል ገብቷል። (ዘዳግም 5:16) የአምላክን ሕግ ችላ በማለት በወላጆቻቸው ላይ የሚያምፁ ነፍስ ያወቁ ልጆች ከሚጠብቃቸው ቅጣት ያመልጣሉ። (ዘዳግም 21:18-21) ከእነዚህ ሕጎች በስተጀርባ ያለው መሠረታዊ ሐሳብ ዛሬም አልተለወጠም። (ኤፌሶን 6:1-3) ወጣቶችም ሆንን አዋቂዎች በፈጣሪያችን ፊት ተጠያቂ ነን። በሌላ በኩል፣ አምላክንና ወላጆቻቸውን የሚታዘዙ ልጆች አምላክ ቃል በገባው መሠረት ረጅም ዕድሜ ይኖራሉ። እንዲያውም ለዘላለም የመኖር ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8፤ 6:18, 19

የዘፀአት 20:12 አውድ

 በዘፀአት 20:12 ላይ ያለው ትእዛዝ፣ በአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ የሚገኝበት ቦታ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዘፀአት 20:1-17) ከዚህ ትእዛዝ በፊት ያሉት ትእዛዛት እስራኤላውያን ከአምላክ ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ግዴታ፣ ለምሳሌ እሱን ብቻ ማምለክ እንዳለባቸው የሚናገሩ ናቸው። ከዚህ ትእዛዝ በኋላ የተጠቀሱት ትእዛዛት ደግሞ እስራኤላውያን ከሰዎች ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ግዴታ፣ ለምሳሌ ለትዳር ጓደኛቸው ታማኝ መሆን እንዳለባቸውና መስረቅ እንደሌለባቸው የሚናገሩ ናቸው። ከዚህ አንጻር “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚለው ትእዛዝ በእነዚህ ትእዛዛት መካከል እንዳለ መሸጋገሪያ ድልድይ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።

ዘፀአት ምዕራፍ 20 አንብብ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የግርጌ ማስታወሻዎቹንና ማጣቀሻዎቹን ተመልከት።