በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ቆላስይስ 3:23—“የምታደርጉትን ሁሉ . . . በሙሉ ልባችሁ አድርጉት”

ቆላስይስ 3:23—“የምታደርጉትን ሁሉ . . . በሙሉ ልባችሁ አድርጉት”

 “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ እንደምታደርጉት በማሰብ በሙሉ ነፍሳችሁ አድርጉት።”—ቆላስይስ 3:23 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት።”—ቆላስይስ 3:23 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የቆላስይስ 3:23 ትርጉም

 ክርስቲያኖች ታታሪ ሠራተኞች ለመሆን ጥረት ማድረግ አለባቸው፤ ምክንያቱም ሥራቸውን የሚያከናውኑበት መንፈስ ለይሖዋ አምላክ ከሚያቀርቡት አምልኮ ጋር ተያያዥነት አለው።

 “የምታደርጉትን ሁሉ።” ይሖዋን ማምለክ የሚፈልጉ ሰዎች በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፎች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ ይከተላሉ። ቤት ውስጥም ይሁን በሥራ ቦታ አሊያም በትምህርት ቤት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን ሲያከናውኑ ታታሪ፣ ሐቀኛና እምነት የሚጣልባቸው ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ።—ምሳሌ 11:13፤ ሮም 12:11፤ ዕብራውያን 13:18

 “በሙሉ ልባችሁ አድርጉት።” “በሙሉ ልባችሁ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ “አንድ ሰው የአምላክን ፈቃድ በሙሉ ኃይሉ ለመፈጸም ወይም ለማከናወን ያለውን ቁርጠኝነት” ያመለክታል። a

 እንዲህ ያለው ሰው የተሰጠውን ኃላፊነት ሲወጣ አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ችሎታውን በሙሉ ይጠቀማል። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን አገላለጽ ‘ከልባችሁ’ (የ1879 ትርጉም) ወይም “በትጋት” (የ1954 ትርጉም) ብለው ተርጉመውታል።—“⁠ ቆላስይስ 3:23 በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች” የሚለውን ተመልከት።

 “ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ እንደምታደርጉት በማሰብ።” ክርስቲያኖች ሥራቸውን የሚያከናውኑበት መንፈስ ከይሖዋ አምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና እንደሚነካው ስለሚገነዘቡ የተሰጣቸውን ማንኛውንም ሥራ በቁም ነገር ይመለከቱታል። በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ይሖዋን ማስደሰታቸው እንጂ አሠሪያቸውን ወይም ሌሎች ሰዎችን ማስደሰታቸው አይደለም። አንድ ክርስቲያን ያለው መልካም የሥራ ባሕልና አዎንታዊ አመለካከት ስለ እሱ ብቻ ሳይሆን ስለሚያመልከው አምላክም የሚናገረው ነገር አለ። ስለዚህ ክርስቲያኖች “የአምላክ ስም . . . ፈጽሞ እንዳይሰደብ” አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ።—1 ጢሞቴዎስ 6:1፤ ቆላስይስ 3:22

የቆላስይስ 3:23 አውድ

 የቆላስይስ መጽሐፍን የጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ ሲሆን መልእክቱ የተጻፈውም በጥንቷ ቆላስይስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ነው።  b ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው በ60-61 ዓ.ም. ገደማ በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ በታሰረበት ወቅት በእስር ጊዜው መገባደጃ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም።

 የቆላስይስ መጽሐፍ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች በአንድነት አምላክን እንዲያመልኩ የሚረዳ ምክር ይዟል። (ቆላስይስ 3:11) እንደ ፍቅር፣ ደግነትና ምሕረት ያሉትን የአምላክን ባሕርያት እንዲያንጸባርቁ በመጽሐፉ ላይ ተበረታተዋል። (ቆላስይስ 3:12-14) በተጨማሪም አንድ ሰው የሚያቀርበው አምልኮ ከሁሉም የሕይወቱ ዘርፎች ጋር የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።—ቆላስይስ 3:18 እስከ 4:1

 ቆላስይስ 3:23 በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች

 “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት።”—የ1954 ትርጉም

 ‘ያደረጋችሁትም ሁሉ ከልባችሁ ይሁን፤ ለእግዚአብሔር እንዲደረግ ለሰውም አይደለም።’—የ1879 ትርጉም

 “ሰውን ሳይሆን ጌታን እንደምታገለግሉ በመቁጠር፣ የተሰጣችሁን ሥራ በትጋት ፈጽሙ።”—ሕያው ቃል

 የቆላስይስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ኤክሰጀቲካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት፣ 1993 ጥራዝ 3 ገጽ 502

b የምትገኘው በአሁኗ ቱርክ ነው።