በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

የውሾች የማሽተት ችሎታ

የውሾች የማሽተት ችሎታ

 አንዳንድ ተመራማሪዎች ውሾች የማሽተት ችሎታቸውን ተጠቅመው የሌሎች ውሾችን ዕድሜ፣ ፆታና ስሜት ማወቅ እንደሚችሉ ይናገራሉ። ውሾች ፈንጂዎችንና ዕፆችን ጭምር አሽትተው እንዲለዩ ሥልጠና ሊያገኙ ይችላሉ። ሰዎች በአካባቢያቸው ያለውን ነገር ለማወቅ በዋነኝነት የማየት ችሎታቸውን እንደሚጠቀሙ ሁሉ ውሾች ይህን የሚያደርጉት የማሽተት ችሎታቸውን ተጠቅመው ነው። በአፍንጫቸው እንደሚያዩ ሊቆጠር ይችላል።

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የውሾች የማሽተት ችሎታ ከእኛ በብዙ ሺህ እጥፍ ይበልጣል። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የደረጃና የቴክኖሎጂ ተቋም እንደገለጸው ከሆነ ውሾች “አንዳንድ ንጥረ ነገሮችን ከአንድ ትሪሊዮን አንድ እጅ ቢኖር እንኳ መለየት ይችላሉ። ይህም በኦሎምፒክ የዋና ገንዳ ውስጥ የሟሟን አንድ አራተኛ የሻይ ማንኪያ ስኳር ከመቅመስ ጋር ሊወዳደር ይችላል።”

 ውሾች የላቀ የማሽተት ችሎታ ሊኖራቸው የቻለው ለምንድን ነው?

  •   የውሾች አፍንጫ እርጥበት ያለው ስለሆነ የሚሸቱ ነገሮችን በቀላሉ መያዝ ይችላል።

  •   የውሾች አፍንጫ ሁለት የአየር መተላለፊያ ቧንቧዎች አሉት፤ አንዱ ለመተንፈስ ሌላኛው ደግሞ ለማሽተት ያገለግላል። ውሾች አንድን ነገር ሲያሸትቱ አየሩ ሽታ የሚለዩ ሕዋሳት ወደሚገኙበት የአፍንጫቸው ክፍል ይሄዳል።

  •   ሽታ የሚለየው የውሾች አፍንጫ ክፍል 130 ካሬ ሴንቲ ሜትር ወይም ከዚያ የሚበልጥ ስፋት አለው፤ በአንጻሩ ግን ሽታ የሚለየው የሰዎች አፍንጫ ክፍል ስፋት 5 ካሬ ሴንቲ ሜትር ያህል ብቻ ነው።

  •   ውሾች ያሏቸው ሽታ የሚለዩ ሕዋሳት ቁጥር ከሰዎች ጋር ሲነጻጸር በ50 እጥፍ ገደማ ሊበልጥ ይችላል።

 በእነዚህ ነገሮች የተነሳ ውሾች አንድ ነገር ሲያሸትቱ ያ ነገር የተሠራባቸውን ንጥረ ነገሮች በሙሉ መለየት ይችላሉ። ለምሳሌ ሰዎች ሾርባ ማሽተት ቢችሉም ውሾች ግን ሾርባው የተሠራባቸውን ንጥረ ነገሮች በሙሉ መለየት እንደሚችሉ አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

 የካንሰር ምርምር ተቋም የሆነው የፓይን ስትሪት ፋውንዴሽን ተመራማሪዎች እንደገለጹት የውሾች አፍንጫና የአንጎላቸው ቅንጅት “በምድራችን ላይ ካሉ በጣም ውስብስብ የሆኑ ሽታ የሚለዩ መሣሪያዎች አንዱን” ይፈጥራል። የሳይንስ ሊቃውንት ፈንጂዎችን፣ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን እንዲሁም ካንሰርን ጨምሮ አንዳንድ በሽታዎችን የሚለይ ኤሌክትሮኒክ “አፍንጫ” ለመሥራት ጥረት እያደረጉ ነው።

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? የውሾች የማሽተት ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የመጣ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?