በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

በጆሮዋ “የምታየው” የሌሊት ወፍ

በጆሮዋ “የምታየው” የሌሊት ወፍ

 የሌሊት ወፎች በዓይናቸው ማየት ቢችሉም አብዛኞቹ ዝርያዎች በጨለማ አካባቢያቸውን “ለማየት” የገደል ማሚቶ ይጠቀማሉ፤ ድምፅ አንድ ነገር ላይ ነጥሮ ለመመለስ የሚፈጅበትን ጊዜ በመለካት የዚያን ነገር ምንነትና የሚገኝበትን ርቀት ማወቅ ይችላሉ። ለምሳሌ አንዳንድ የሌሊት ወፎች በዚህ ዘዴ ተጠቅመው ቢንቢን ከጢንዚዛ መለየት ይችላሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ነፍሳቱ ክንፋቸውን የሚያርገበግቡበትን ፍጥነት በመለካት ነው።

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አብዛኞቹ የሌሊት ወፎች ማንቁርታቸው ውስጥ ድምፅ ከፈጠሩ በኋላ በአፋቸው ወይም በአፍንጫቸው አማካኝነት ድምፁን ያወጡታል። ከዚያም ትላልቅ ጆሮዎቻቸውን ተጠቅመው፣ የድምፁ ሞገዶች በዙሪያቸው ባሉት ነገሮች ላይ ነጥረው ሲመለሱ የሚፈጥሩትን የገደል ማሚቶ ይሰማሉ። እንዲህ ያለው የገደል ማሚቶ የሌሊት ወፎቹ አካባቢያቸውን በአእምሯቸው እንዲሥሉ ያስችላቸዋል። አንዲት የሌሊት ወፍ በዙሪያዋ ያሉ ሌሎች የሌሊት ወፎች የሚፈጥሩት ድምፅ፣ አንድ ነገር የሚገኝበትን ቦታ፣ ከፍታና ርቀት ከማወቅ አያግዳትም።

 የሌሊት ወፎች የገደል ማሚቶን የሚጠቀሙበት መንገድ በጥንቃቄ የተቃኘ ነው፤ ምክንያቱም የአንድ ሚሊ ሴኮንድ (የሴኮንድ 1/1,000) ስህተት እንኳ ቢፈጠር የሌሊት ወፎቹ ቦታውን በ17 ሴንቲ ሜትር ይስቱታል። አንዳንድ ተመራማሪዎች የሌሊት ወፎች ይህን ያህል የተቃኘ ችሎታ ሊኖራቸው እንደማይችል በመግለጽ ይከራከራሉ። ያም ቢሆን አንዳንድ የቤተ ሙከራ ውጤቶች እንደሚጠቁሙት የሌሊት ወፎች በገደል ማሚቶ ላይ የ10 ናኖ ሴኮንድ (የሴኮንድ 1/100,000,000) ልዩነት እንኳ ማወቅ ይችላሉ፤ ይህም ርቀት ሲለኩ የአንድ ሚሊ ሜትር ወይም ከዚያ የሚያንስ ስህተት እንኳ እንዳይፈጠር ያደርጋል!

 ተመራማሪዎች የገደል ማሚቶን በመጠቀም ዓይነ ስውራን አካባቢያቸውን በአእምሯቸው እንዲሥሉና ከመሬት ከፍ ካሉ ነገሮች (ለምሳሌ ከዛፍ ቅርንጫፍ) ጋር እንዳይጋጩ የሚረዳ ኤሌክትሮኒክ ዘንግ አዘጋጅተዋል። የዚህን ዘንግ ንድፍ ካወጡት ባለሙያዎች መካከል ሁለቱ፣ ይኸውም ብራያን ሆይል እና ዲን ዎተርስ እንደገለጹት “ለዚህ ሥራ ዋነኛ መነሻ የሆነው የሌሊት ወፎች አካባቢያቸውን ለማወቅ የገደል ማሚቶን ስለሚጠቀሙበት አስደናቂ መንገድ የተገኘው እውቀት ነው።”

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? የሌሊት ወፎች የገደል ማሚቶን ተጠቅመው አካባቢያቸውን “የሚያዩበት” አስደናቂ ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?