በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

ካቤጅ ኋይት ቢራቢሮ ክንፏን የምትዘረጋበት መንገድ

ካቤጅ ኋይት ቢራቢሮ ክንፏን የምትዘረጋበት መንገድ

 ቢራቢሮዎች መብረር ከመጀመራቸው በፊት የበረራ ጡንቻዎቻቸውን በፀሐይ ብርሃን ያሞቃሉ። አየሩ ደመናማ በሚሆንበት ጊዜ ግን ካቤጅ ኋይት የተባለችው ቢራቢሮ ከሌሎች ቢራቢሮዎች ቀድማ ለበረራ ዝግጁ ትሆናለች። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ብዙ ቢራቢሮዎች መብረር ከመጀመራቸው በፊት ክንፋቸውን ገጥመው ወይም ሙሉ በሙሉ ዘርግተው ፀሐይ ይሞቃሉ። ይሁንና ካቤጅ ኋይት ቢራቢሮ ፀሐይ የምትሞቀው ክንፎቿን በ“V” ቅርጽ ዘርግታ ነው። ቢራቢሮዋ በተሻለ መንገድ ሙቀት መሰብሰብ የምትችለው የተገጠሙትን ክንፎቿን ከቋሚ መስመር 17 ዲግሪ ላይ ስትከፍት ነው። ክንፏን በዚህ መንገድ መዘርጋቷ የፀሐይ ኃይል በደረቷ አካባቢ የሚገኙትን የበረራ ጡንቻዎች በቀጥታ እንዲያገኛቸውና እንዲያሞቃቸው ያስችላል።

 እንግሊዝ በሚገኘው ኤክሲተር ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተመራማሪዎች የቢራቢሮዋን “V” ቅርጽ የክንፍ አዘረጋግ በመኮረጅ የፀሐይ ኃይል መቀበያ መሣሪያዎችን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ ይቻል እንደሆነ ምርምር አድርገው ነበር። በውጤቱም ከእነዚህ መሣሪያዎች የሚገኘው ኃይል በ50 በመቶ እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል።

 ተመራማሪዎቹ የቢራቢሮዋ ክንፍ በእጅጉ አንጸባራቂ እንደሆነም አስተውለዋል። የቢራቢሮዋን ክንፍ አዘረጋግና አንጸባራቂነት በመኮረጅ ክብደታቸው ቀላል የሆነና ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ የፀሐይ ኃይል መቀበያ መሣሪያዎችን መሥራት ችለዋል። በዚህም የተነሳ ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፍሬንች ኮንስታንት ይህች ቢራቢሮ “ከፀሐይ ብርሃን ኃይል በማምረት ረገድ የተካነች” እንደሆነች ገልጸዋል።

 ታዲያ ምን ይመስልሃል? የካቤጅ ኋይት ቢራቢሮ “V” ቅርጽ የክንፍ አዘረጋግ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?