በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሚያዝያ 25, 2024
ፓራጓይ

በፓራጓይ በተካሄደ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ቃል ለእይታ አቀረቡ

በፓራጓይ በተካሄደ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ቃል ለእይታ አቀረቡ

ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 10, 2024 አሱንሲዮን፣ ፓራጓይ ውስጥ ሊብሮፌሪያ ካፔል የተሰኘ ዓመታዊ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ተካሂዷል። በየዓመቱ በዚህ ዝግጅት ላይ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ 10,000 የንባብ አፍቃሪያን እንደሚገኙ ይገመታል። የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ቃል እና jw.org ላይ የሚገኙ ልዩ ልዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መሣሪያዎችን ለእይታ ያቀረቡ ሲሆን ከ160 በላይ ወንድሞችና እህቶች ተራ በተራ ኪዮስኩ ላይ ሠርተዋል። በስፓንኛ፣ በግዋራኒ እና በፓራጓይ ምልክት ቋንቋ የታተሙም ሆኑ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት የተዘጋጁ ጽሑፎች ቀርበዋል።

አንድ ሰው፣ ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርስ የሚያስተዋውቀውን ፖስተር ካየ በኋላ ወደ ኪዮስካችን መጣ። ወንድሞች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርሱ የሚሰጠው እንዴት እንደሆነ ካስረዱት በኋላ ለዘላለም በደስታ ኑር! ብሮሹራችንን አሳዩት። ሰውየው ብሮሹሩን ከቃኘ በኋላ “መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ እንዳለው አላውቅም ነበር” በማለት ግርምቱን ገልጿል። የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ሲነገረውም በጣም ተደሰተ። በቀጣይ ለመገናኘትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር በቀጠሮ ተለያይተዋል።

በሌላ ጊዜ ላይ ደግሞ አንድ ሰው ኪዮስኩ ላይ ትሠራ የነበረች እህታችንን አነጋገራት። በግዋራኒ፣ በግዋራኒ (ምቢያ) እና በኒቫክሌ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ልዩ ልዩ መረጃዎች ድረ ገጻችን ላይ በማየቱ በጣም እንደተደሰተ ገለጸ። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በተለያዩ አገር በቀል ቋንቋዎች ለማዘጋጀት ለሚያከናውኑት ሥራም ምስጋናውን ገለጸ።

በምሥክርነት ዘመቻው ላይ ከተካፈሉ ወንድሞችና እህቶች አንዳንዶቹ

ሥራውን ያስተባበረው ወንድም ዳንዬሌ ሳርኮኔ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ጉጉት ከነበራቸው ብዙ ሰዎች ጋር የመነጋገር አጋጣሚ በማግኘታችን ተደስተናል።” በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ቢያንስ 13 ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በግላቸው መማር ስለሚችሉበት መንገድ መረጃ ጠይቀዋል።

ፓራጓይ ውስጥ እውነትን መስማት ያለባቸው ብዙ ሰዎች አሉ፤ በመሆኑም እንዲህ ያለ ጥሩ ምሥክርነት በመሰጠቱ ተደስተናል።​—መዝሙር 119:160