በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ኸርሚን ሽሚት

ሚያዝያ 18, 2024
ጀርመን

ኸርሚን ሽሚት፣ ከናዚ ማጎሪያ ካምፖች ከተረፉት የይሖዋ ምሥክሮች የመጨረሻዋ በ98 ዓመቷ አረፈች

ኸርሚን ሽሚት፣ ከናዚ ማጎሪያ ካምፖች ከተረፉት የይሖዋ ምሥክሮች የመጨረሻዋ በ98 ዓመቷ አረፈች

ኸርሚን ወደ ስቱትሆፍ ማጎሪያ ካምፕ ከመላኳ በፊት

መጋቢት 31, 2024 እህት ኸርሚን ሽሚት በ98 ዓመቷ አርፋለች። በእምነታቸው ምክንያት በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ሥቃይ ከደረሰባቸው የይሖዋ ምሥክሮች በሕይወት የቀረችው እሷ እንደነበረች ይታመናል።

ኸርሚን ኅዳር 13, 1925 ግዳይንስክ ከተማ (አሁን የፖላንድ ክፍል ነች) ውስጥ ተወለደች። ወላጆቿ ኦስካር እና ፍሪዳ ኮሽሚደር የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ከልጅነቷ ጀምሮ ጠንካራ እምነት እንድታዳብር ረድተዋታል። በ1939 የናዚ ሠራዊት ግዳይንስክ ከተማን ተቆጣጠራት፤ ይህን ተከትሎም በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከባድ ስደት ተነሳ። በዚሁ ጊዜ አካባቢ ኸርሚን በ16 ዓመቷ ግንቦት 2, 1942 ራሷን ለይሖዋ ወስና ተጠመቀች።

በቀጣዩ ዓመት ማለትም ሰኔ 1943 ናዚዎች የ17 ዓመቷን ኸርሚንን አሰሯት። በኋላ ላይ ሚያዝያ 1944 ድጋሚ ተያዘች፤ በዚህ ጊዜ ግን ወደ ስቱትሆፍ ማጎሪያ ካምፕ ተላከች። ኸርሚን ያንን ሰቆቃ መለስ ብላ ስታስታውስ በአንድ ወቅት እንዲህ ብላለች፦ “በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግር ነገር ነው የሆነው። የደረሰብን ውርደትና የስሜት መጎዳት ይህ ነው ለማለት ይከብደኛል። ጌስታፖዎቹ አቋሜን ለማስቀየር ያላደረጉት ጥረት የለም። እኔ ከሰው የተለየ ጥንካሬ ኖሮኝ አይደለም። ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግን ቅንጣት ታክል ተጠራጥሬ አላውቅም። ታማኝ ለመሆንና ሕሊናዬ የሚለኝን ለመስማት ቆርጬ ነበር። ሕሊናህን ስትሰማ ሰላም ታገኛለህ፤ ከራስህም ሆነ ከአምላክ ጋር ሰላም ይኖርሃል።”

ሆርስት እና ኸርሚን፣ መጋቢት 1995

ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ሚያዝያ 1945 የሩሲያ ሠራዊት ወደ ስቱትሆፍ ካምፕ ተጠጋ። የጀርመን የኤስ ኤስ ጠባቂዎች እስረኞቹ በሩሲያ ሠራዊት ነፃ እንዲወጡ ስላልፈለጉ ጀልባዎች ላይ ጭነው መሃል ባሕር ላይ ተዉኣቸው። ኸርሚን እና 370 እስረኞች የተጫኑበት አንደኛው ጀልባ ግንቦት 1945 እየተጎተተ ሞን ወደተባለች የዴንማርክ ደሴት ደረሰ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኸርሚን ከወላጆቿ ጋር ተገናኘች።

በ1947 ኸርሚን ከሆርስት ሽሚት ጋር ትዳር መሠረተች። የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በታገደበት ወቅት ሆርስት ጦር ሠራዊቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች ከቦታ ቦታ ያደርስ ነበር። ችሎት ፊት ቀርቦ ሞት ተፈረደበት፤ ከዚያም ብራንደንቡርግ ጎርደን ማረሚያ ቤት ውስጥ ታሰረ። የሚገደልበት ቀን ከመድረሱ ጥቂት ቀደም ብሎ ሚያዝያ 27, 1945 እስር ቤቱ ነፃ ወጣ። ሆርስት በ2010 ሕይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ከኸርሚን ጋር በትዳር 63 ዓመታት ቆይተዋል።

ኸርሚን እና ባለቤቷ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ መድረኮች ተሞክሯቸውን በማካፈል ይታወቃሉ። ኸርሚን በ1998 በተደረገላት ቃለ መጠይቅ ላይ የተከተለችውን የታማኝነት ጎዳና በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “ይህ የሕይወት ጎዳና ቀላል ነው አልልም፤ ነገር ግን እጅግ ያማረ ነው። በምንም አልለውጠውም።”

ኸርሚን ስደት ባጋጠማት ጊዜ ያሳየችውን ታማኝነት እናደንቃለን። እኛም እሷን በእምነቷ ለመምሰል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ ይሖዋ ታማኞቹን ምንጊዜም እንደሚጠብቅ በመተማመን ደፋር እንሁን፤ ልባችንም ይጽና።​—መዝሙር 31:23, 24