በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በኖርዌይ፣ የኦስሎ አውራጃ ፍርድ ቤት ጉዳያችን በተሰማበት ወቅት የነበሩት ዳኛ እና ጠበቆች

መጋቢት 28, 2024
ኖርዌይ

የይሖዋ ምሥክሮች በኖርዌይ የተላለፈውን ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ ብይን ይግባኝ ሊሉ ነው

የይሖዋ ምሥክሮች በኖርዌይ የተላለፈውን ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ ብይን ይግባኝ ሊሉ ነው

መጋቢት 4, 2024 የኦስሎ አውራጃ ፍርድ ቤት፣ የኖርዌይ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ ምዝገባ ለመሰረዝ ያደረገውን ውሳኔ አጽድቆታል። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ውሳኔ ይግባኝ እንደሚሉ ታውቋል።

የኦስሎ አውራጃ ፍርድ ቤት ከውጭ

የኦስሎ እና የቪከን አስተዳዳሪ፣ በ2022 መገባደጃ ላይ ፈቃዳችንን አንስተው ነበር። ታኅሣሥ 30, 2022 የኦስሎ አውራጃ ፍርድ ቤት፣ ተጨማሪ ምርመራ እስኪካሄድ ድረስ የአስተዳዳሪው ውሳኔ በጊዜያዊነት እንዲታገድ ወስኖ ነበር። አሁን ያለው የመንግሥት አቋም፣ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን ከጉባኤው ከምናስወግድበት ሥርዓት ጋር በተያያዘ የምንከተለውን አካሄድ ካልቀየርን በአገሪቱ ያገኘነው እውቅና መሰረዝ አለበት የሚል ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች ፈቃድ እንዲሰረዝ የተደረገው ውሳኔ፣ በአገሪቱ እንደተመዘገቡት ከ700 በላይ ሃይማኖታዊ ተቋማት ሁሉ ከመንግሥት የምናገኘውን የገንዘብ እርዳታና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንድናጣ ያደርጋል። ይህ ውሳኔ የሚያስከትላቸው ሌሎች ችግሮችም አሉ፤ ለምሳሌ የይሖዋ ምሥክር አገልጋዮች ሙሽሮችን የማፈራረም ሥልጣናቸው ይሰረዛል።

የይግባኙን ውጤት ስንጠባበቅ “ነገሥታትንና በሥልጣን ላይ ያሉትን ሁሉ በተመለከተ” መጸለያችንን እንቀጥል፤ “ይህም . . . በጸጥታና በተረጋጋ ሁኔታ መኖራችንን እንቀጥል ዘንድ ነው።”​—1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2