በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ስም አዲስ ኪዳን ውስጥ መልሰው ያስገቡ ሁለት ተርጓሚዎች

የአምላክን ስም አዲስ ኪዳን ውስጥ መልሰው ያስገቡ ሁለት ተርጓሚዎች

 ብዙ ሰዎች ጸሎት ሲማሩ መጀመሪያ የሚያጠኑት አንድ ጸሎት አለ፤ ይህም በተለምዶ አቡነ ዘበሰማያት ተብሎ የሚጠራውና ኢየሱስ ለተከታዮቹ ያስተማረው ጸሎት ነው። ጸሎቱ የሚገኘው ብዙ ጊዜ አዲስ ኪዳን ተብሎ በሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ነው። “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” በሚሉት ቃላት ይጀምራል። (ማቴዎስ 6:9) ይሁን እንጂ በእንግሊዝኛ “ጀሆቫ” ወይም አንዳንድ ጊዜ “ያህዌ” ተብሎ የሚቀመጠው የአምላክ ስም በእንግሊዝኛ በተዘጋጁ የአዲስ ኪዳን ትርጉሞች ውስጥ የሚገኘው ከስንት አንዴ ነው። በሌላ በኩል ግን እነዚህ ትርጉሞች እንደ ዙስ፣ ሄርሜስ እና አርጤምስ ያሉ የሐሰት አማልክትን ስም ከማካተት ወደኋላ አይሉም። ታዲያ እውነተኛ የሆነውንና መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈውን አምላክ ስም አለማካተታቸው ያስኬዳል?የሐዋርያት ሥራ 14:12፤ 19:35፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16

አዲስ ኪዳን ላይ የተለያዩ የሐሰት አማልክት ስም ተጠቅሷል፤ ታዲያ የእውነተኛው አምላክ ስም መጠቀሱስ ተገቢ አይሆንም?

 ላንሴሎት ሻድዌል እና ፍሬድሪክ ፓርከር የተባሉት የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች፣ የአምላክ ስም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተመልሶ መግባት ይኖርበታል የሚል እምነት ነበራቸው። “ተመልሶ” የሚለውን ቃል መጠቀም ለምን አስፈለገ? ምክንያቱም ተርጓሚዎቹ በደረሱበት መደምደሚያ መሠረት የአምላክ ስም በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ እንዲወጣ ተደርጓል። እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት ለምንድን ነው?

 ሻድዌል እና ፓርከር የሚያውቁት አንድ ነገር ነበር፤ በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብለው የሚጠሩትን መጻሕፍት (በዋነኝነት የተጻፉት በዕብራይስጥ ነው) የያዙ በወቅቱ የነበሩ ጥንታዊ የእጅ ግልባጮች የአምላክን የግል ስም በሺዎች የሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ አካትተዋል። ታዲያ በእጅ የተጻፉት የአዲስ ኪዳን ግልባጮች የአምላክን ሙሉ ስም ያላካተቱት ለምንድን ነው የሚለው ጉዳይ እነዚህን ተርጓሚዎች ግራ አጋባቸው። a በተጨማሪም ሻድዌል ያስተዋለው አንድ ነገር ነበር፤ ይኸውም የግሪክኛው የአዲስ ኪዳን ገልባጮች “የይሖዋ መልአክ” እንደሚለው ያሉ ብሉይ ኪዳን ውስጥ የተለመዱ አባባሎችን ሲያስቀምጡ የአምላክን የግል ስም አልተጠቀሙም፤ ከዚህ ይልቅ “ጌታ” የሚል ትርጉም ባለው ኪርዮስ የተባለው ቃል የተኩት ይመስላል።—2 ነገሥት 1:3, 15፤ የሐዋርያት ሥራ 12:23

የአምላክ ስም በዕብራይስጥ

 ሻድዌል እና ፓርከር የየራሳቸውን የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ከማሳተማቸው በፊትም የአምላክን ስም በእንግሊዝኛ ወደተዘጋጁ የአዲስ ኪዳን ትርጉሞች ውስጥ መልሰው ያካተቱ ሌሎች ተርጓሚዎች አልጠፉም፤ ሆኖም ይህን ያደረጉት ጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ ነው። b ፓርከር የአዲስ ኪዳን ቃል በቃል ትርጉም (እንግሊዝኛ) የተባለውን ትርጉሙን ያዘጋጀው በ1863 ነው፤ ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ከዚያ በፊት የአምላክን ስም አዲስ ኪዳን ውስጥ የእሱን ያህል መልሶ በስፋት ያስገባ ሌላ እንግሊዝኛ ተርጓሚ አልነበረም። ለመሆኑ ላንሴሎት ሻድዌል እና ፍሬድሪክ ፓርከር እነማን ናቸው?

ላንሴሎት ሻድዌል

 ላንሴሎት ሻድዌል (1808-1861) የእንግሊዝ ምክትል ቻንስለር የሆኑት የሰር ላንሴሎት ሻድዌል ልጅና ጠበቃ ነበር። ይህ ሰው የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አባል ነበር። በሥላሴ ቢያምንም ለአምላክ ስም አክብሮት ነበረው፤ “የይሖዋ ክብራማ ስም” ሲልም ገልጾታል። የማቴዎስ እና የማርቆስ ወንጌሎች (እንግሊዝኛ) በተባለው ትርጉሙ ላይ “ጀሆቫ” የሚለውን ስም በዋናው ጽሑፍ ላይ 28 ጊዜ፣ በተጨማሪ ማስታወሻዎቹ ላይ ደግሞ 465 ጊዜ ያህል አካትቷል።

 ሻድዌል ስለ አምላክ ስም ያወቀው በጥንታዊው ዕብራይስጥ የተዘጋጀውን ብሉይ ኪዳን አይቶ መሆን አለበት። ወደ ግሪክኛ በተተረጎመው ብሉይ ኪዳን ላይ የአምላክን ስም ኪርዮስ በተባለው ቃል ስለተኩት ሰዎች ሲናገር “ሐቀኛ ተርጓሚዎች አልነበሩም” ብሏል።

The Gospel according to Matthew rendered into English with notes, by L. Shadwell (1859), provided by the Bodleian Libraries. Licensed under CC BY-NC-SA 2.0 UK. Modified: Text highlighted

ማቴዎስ 1:20 በሻድዌል ትርጉም ላይ

 ሻድዌል በትርጉሙ ላይ “ጀሆቫ” የሚለውን ስም መጀመሪያ የተጠቀመው ማቴዎስ 1:20 ላይ ነው። ለዚህ ጥቅስ ባዘጋጀው ማስታወሻ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “እዚህ ላይም ሆነ በሌሎች በርካታ የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች ላይ የገባው [ኪርዮስ] የሚለው ቃል ይሖዋ ማለት ነው፤ የአምላክ መጠሪያ ስም ነው። ይህን ስም በእንግሊዝኛ ትርጉም ላይ መልሶ ማስገባት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክ ታላቅ ክብር ይህ እንዲሆን ግድ ይላል። ስሙ ይሖዋ እንደሆነ የተናገረው ራሱ ነው፤ በመሆኑም ስለ እሱ ስንናገር በዚህ ስም ከመጠቀም የተሻለ ነገር የለም።” ከዚያም ስለ ኪንግ ጄምስ ትርጉም ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “[በዚህ] መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይሖዋ የሚለው ስም አለ ለማለት ያዳግታል። . . . በአምላክ የመጠሪያ ስም ምትክ የምናገኘው ጌታ የሚለውን ነው።” ሻድዌል እንደተናገረው በአምላክ ስም ምትክ የገባው “ጌታ” የሚለው ቃል “አምላክን ፈጽሞ የማይመጥነው ማዕረግ ነው።” ሻድዌል እሱም እንኳ በቤቱ “ጌታ” ተብሎ እንደሚጠራ አክሎ ተናግሯል።

“ስሙ ይሖዋ እንደሆነ የተናገረው [አምላክ] ራሱ ነው፤ በመሆኑም ስለ እሱ ስንናገር በዚህ ስም ከመጠቀም የተሻለ ነገር የለም።”—ላንሴሎት ሻድዌል

 ሻድዌል የማቴዎስ ትርጉሙን በ1859፣ ማቴዎስንና ማርቆስን አጣምሮ የያዘውን ትርጉሙን ደግሞ በ1861 አሳተመ። የሚያሳዝነው ግን ሥራው ከዚህ አልዘለለም። ጥር 11, 1861 በ52 ዓመቱ ሕይወቱ አለፈ። ያደረገው ጥረት ግን ከንቱ አልቀረም።

ፍሬድሪክ ፓርከር

 ሻድዌል ያዘጋጀው የማቴዎስ ትርጉም የፍሬድሪክ ፓርከርን (1804-1888) ትኩረት መሳቡ አልቀረም፤ በለንደን የሚኖረው ይህ ሀብታም ነጋዴ 20 ዓመት ገደማ ሲሆነው አዲስ ኪዳንን ለመተርጎም ቆርጦ ተነሳ። ፓርከር ከሻድዌል የሚለየው፣ የሥላሴን ትምህርት አይቀበልም ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[የአምላክ] ውድ ልጅ ቤተ ክርስቲያን . . . እውነቱን በጸጋ ተቀብላ . . . ሁሉን ቻይ የሆነውን አንድ ይሖዋን እንድታመልክ [ፈቃዱ ይሁን]።” በተጨማሪም ፓርከር በእጅ የተጻፉ የአዲስ ኪዳን ግልባጮች ለጌታ እግዚአብሔርም ሆነ ለጌታ ኢየሱስ ኪርዮስ የሚለውን ተመሳሳይ ቃል መጠቀማቸው በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት እንደሰወረው ተሰምቶት ነበር። በመሆኑም ፓርከር፣ ኪርዮስ በገባባቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሻድዌል “ጀሆቫ” የሚለውን ስም መተካቱ ትኩረቱን ሳበው።

 ፓርከር ስለዚህ ጉዳይ እውቀት ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው? ግሪክኛ ተምሯል፤ እንዲሁም ስለ ግሪክኛ ሰዋስው በርካታ መጻሕፍትና ትራክቶች አዘጋጅቷል። በተጨማሪም የእንግሊዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አባል ሆኖ ነበር፤ ይህ ማኅበር፣ የተሻሉ የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን የማዘጋጀት ዓላማ ሰንቆ በጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ግልባጮች ላይ ምርምር የሚያደርግ ተቋም ነበር። በ1842 ፓርከር፣ የአዲስ ኪዳን የትርጉም ሥራዎቹን በክፍል በክፍል እያደረገ ማሳተም ጀመረ። c

በፓርከር (በሃይንፌተር) የተዘጋጀው የአዲስ ኪዳን ትርጉም

ፓርከር የአምላክን ስም መልሶ ለማስገባት ያደረገው ጥረት

 ፓርከር ለተወሰኑ ዓመታት እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን የሚዳስሱ ጽሑፎችን ያዘጋጅ ነበር፦ “ኪርዮስ የሚለው ቃል ለጌታ ኢየሱስ የሚሠራው መቼ ነው? ለጌታ እግዚአብሔርስ?” “ኪርዮስ ብዙ ጊዜ የሚሠራበት ሰዋስዋዊ አገባብ ስምን እንጂ ማዕረግን የማያመለክተው ለምንድን ነው?”

 ፓርከር የሻድዌልን የ1859 የማቴዎስ ትርጉምና ኪርዮስ ለሚለው ቃል የሰጠውን ማብራሪያ ሲመለከት ኪርዮስ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ “ይሖዋ ተብሎ መተርጎም እንዳለበት” እርግጠኛ ሆነ። በመሆኑም በአዲስ ኪዳን ትርጉሙ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ወሰነ፤ የጥቅሱን አውድ ወይም የግሪክኛውን ጽሑፍ ሰዋስው ግምት ውስጥ በማስገባት ተገቢ ነው ብሎ ባመነባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ “ጀሆቫ” የሚለውን ስም አካተተ። በመሆኑም ፓርከር በ1863 በአንድ ጥራዝ ያሳተመው የአዲስ ኪዳን ትርጉም በዋናው ጽሑፍ ላይ 187 ጊዜ ያህል የአምላክን ስም ይጠቅሳል። መለኮታዊው ስም በመላው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተካተተበት የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ ትርጉም ይህ ሳይሆን አይቀርም። d

የ1864ቱ የፓርከር አዲስ ኪዳን ትርጉም የርዕስ ገጽ

 በ1864 ፓርከር፣ እሱ ያዘጋጀውን ትርጉም ከኪንግ ጄምስ አዲስ ኪዳን ትርጉም ጋር አጣምሮ በአንድ ጥራዝ አሳተመ። ዓላማውም የእሱ ትርጉምና ሌላኛው ትርጉም የት የትና እንዴት እንደሚለይ ማሳየት ነበር። e

 ፓርከር የአምላክን ስም መልሶ ማስገባት ያለውን አስፈላጊነት ለማስገንዘብ ከኪንግ ጄምስ ትርጉም ላይ አንዳንድ ጥቅሶችን እንደ ምሳሌ አንስቶ ነበር፤ አንደኛው ጥቅስ ሮም 10:13 ነው። ጥቅሱ በኪንግ ጄምስ ትርጉም ላይ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና” ይላል። ከዚያም ፓርከር እንዲህ የሚል ጥያቄ ያነሳል፦ “አንድ ሰው ይህን ጥቅስ [ኪንግ ጄምስ ትርጉም] ላይ አንብቦ እዚህ ላይ የተገለጸው ይሖዋ እንጂ ወልድ ማለትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳልሆነ ሊረዳ ይችላል?”

ሮም 10:13 በኪንግ ጄምስ ትርጉም ላይ (ከላይ) እና በ1864ቱ የፓርከር ትርጉም ላይ

 ፓርከር ትራክቶቹን፣ የምርምር ውጤቶቹንና ሌሎች ጽሑፎቹን ለማሳተምና ለማስተዋወቅ ብዙ ሺ ፓውንድ አውጥቷል፤ ይህ በዚያን ጊዜ ቀላል የሚባል ገንዘብ አይደለም። እንዲያውም በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 800 ፓውንድ የሚሆን ገንዘብ አውጥቷል፤ ይህ በዛሬው ተመን ቢሰላ ከ100,000 የእንግሊዝ ፓውንድ (132,000 የአሜሪካ ዶላር) በላይ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ጽሑፎቹን ለሚያውቃቸው ሰዎችና ከፍተኛ ቦታ ለነበራቸው ቀሳውስት በነፃ በመላክ ሥራውን እንዲገመግሙለት ያደርግ ነበር።

 የፓርከር የጽሑፍ ሥራዎችና የአዲስ ኪዳን ትርጉሞች በብዛት አልታተሙም፤ አንዳንድ ምሁራንም ሥራዎቹን አጣጥለዋል። እነዚህ ምሁራን፣ ፓርከርም ሆነ ሻድዌልና ሌሎች ተርጓሚዎች የአምላክ የግል ስም በእንግሊዝኛ በተዘጋጁ የአዲስ ኪዳን ትርጉሞች ላይ እንዲካተት ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት እውቅና አለመስጠታቸው የሚያሳዝን ነው።

 ትምህርት ሰጪ የሆነውን ይህን የአሥር ደቂቃ ቪዲዮ እንድትመለከትም እንጋብዝሃለን፦ የዎርዊክ ቤተ መዘክር ጉብኝት፦ “መጽሐፍ ቅዱስ እና መለኮታዊው ስም”

a የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ የሆነው “ያህ” በራእይ 19:1, 3, 4, 6 ላይ ይገኛል፤ በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የሚገኘው “ሃሌሉያህ” የሚለው ቃል “እናንተ ሕዝቦች፣ ያህን አወድሱ!” የሚል ትርጉም አለው።

b ሻድዌል ሙሉውን አዲስ ኪዳን አልተረጎመም። ሌሎቹ ተርጓሚዎች ፊሊፕ ዶድሪጅ፣ ኤድዋርድ ሃርዉድ፣ ዊልያም ኒውካም፣ ኤድጋር ቴይለር እና ጊልበርት ዌክፊልድ ናቸው።

c ፓርከር የንግድ ሥራውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሚያደርገው የምርምር ሥራ ለመለየት ሲል በሃይማኖታዊ ጽሑፎቹና በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቹ ላይ ኸርማን ሃይንፌተር የሚለውን የብዕር ስም ይጠቀም ነበር። በአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ተጨማሪ መረጃዎች ላይ ይህ የብዕር ስም በተደጋጋሚ ጊዜ ይጠቀሳል።

d ፓርከር በ1864 ባወጣው እንግሊዝኛ የአዲስ ኪዳን ትርጉም ላይ የአምላክን ስም 186 ጊዜ ያህል ተጠቅሟል።

e ፓርከር ትርጉሙን ከማዘጋጀቱ በፊትም የአምላክን ስም በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ያካተቱ በርካታ የዕብራይስጥ ትርጉሞች ነበሩ። በተጨማሪም ዮሃን ያኮብ ስቶልትስ በ1795 ባዘጋጀው ጀርመንኛ ትርጉም ላይ የአምላክን ስም ከማቴዎስ እስከ ይሁዳ ባሉት መጻሕፍት ላይ ከ90 ጊዜ በላይ ተጠቅሟል።