በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበዴል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም—አነስተኛ ግን ጉልህ እመርታ

የበዴል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም—አነስተኛ ግን ጉልህ እመርታ

እንግሊዛዊው ቄስ ዊልያም በዴል በ1627 ወደ አየርላንድ ሲሄድ በጣም ግራ የሚያጋባ ሁኔታ አጋጠመው። የካቶሊክ ሃይማኖት የነገሠባት አየርላንድ የምትተዳደረው፣ የመንግሥት ሃይማኖት ፕሮቴስታንት በሆነባት በብሪታንያ ነበር። የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አራማጆች ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስን በመላው አውሮፓ በሚነገሩ ቋንቋዎች ተርጉመው ነበር። ሆኖም አንዳቸውም ቢሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ አይሪሽ ቋንቋ ለመተርጎም ፍላጎት አልነበራቸውም።

በዴል የአየርላንድ ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስን “ለማንበብ የግድ እንግሊዝኛ መማር አያስፈልጋቸውም” በሚል ስሜት ተቆርቋሪነቱን አሳየ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በአይሪሽ ቋንቋ ለመተርጎም ቆርጦ ተነሳ። ይሁን እንጂ በተለይ ከፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች መራራ ተቃውሞ ገጠመው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?

ወደ አይሪሽ እንዳይተረጉም የደረሰበት ተቃውሞ

በዴል የግድ አይሪሽ ቋንቋ መማር እንዳለበት ወሰነ። በደብሊን የትሪኒቲ ኮሌጅ ዲን ወይም አስተዳዳሪ በነበረበት ጊዜ፣ በኋላ ደግሞ የኪልሞር ጳጳስ ሆኖ ሲሾም ተማሪዎቹን አይሪሽ እንዲናገሩ ያበረታታቸው ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የእንግሊዟ ቀዳማዊት ንግሥት ኤልዛቤል የትሪኒቲ ኮሌጅን ባቋቋመችበት ወቅት ለተገዢዎቿ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተማር የሚችሉ አገልጋዮችን የማፍራት ዓላማ ነበራት። በዴልም ቢሆን ያደረገው ይህንኑ ነው።

በኪልሞር ደብር አብዛኛዎቹ ሰዎች አይሪሽ ተናጋሪ ነበሩ። በመሆኑም በዴል አይሪሽ መናገር የሚችሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲመደቡለት ጥያቄ አቀረበ። በአገሪቱ ላሉት ለባለሥልጣናት ጥያቄ ያቀረበው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 14:19 ላይ “በጉባኤ ውስጥ አሥር ሺህ ቃላት በልሳን [ሰዎች በማይገባቸው ቋንቋ] ከምናገር ሌሎችንም ማስተማር እችል ዘንድ አምስት ቃላት በአእምሮዬ ብናገር እመርጣለሁ” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር በሚስማማ መንፈስ ነው።

ይሁን እንጂ ተደማጭነት ያላቸው ባለሥልጣናት ሥራውን ለማስቆም የቻሉትን ሁሉ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ታሪክ ጸሐፊዎች እንደገለጹት፣ አንዳንዶች ወደ አይሪሽ መተርጎም “ለመንግሥት አደገኛ” እንደሆነ ጠበቅ አድርገው የገለጹ ሲሆን ሌሎች ደግሞ “የመንግሥትን ጥቅም የሚጻረር” ነገር እንደሆነ ተናገሩ። አንዳንድ ሰዎች፣ የአየርላንድ ሕዝብ ሳይማር እንዲቀር ማድረግ የእንግሊዝን ፍላጎት ለማስጠበቅ ይበጃል የሚል አመለካከት ነበራቸው። እንዲያውም የአየርላንድ ሕዝቦች የራሳቸውን ቋንቋና ባሕል ትተው እንግሊዝኛ እንዲማሩና የእንግሊዝን ሕዝብ አኗኗርና ባሕል እንዲከተሉ የሚያስገድዱ ሕጎች ተደንግገው ነበር።

በዴል መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም ጀመረ

በዴል እንደዚህ ያሉ አምባገነናዊ አመለካከቶች ከተነሳበት ዓላማ እንዲያፈገፍግ አላደረጉትም። በ1630 መጀመሪያ ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ታትሞ አገልግሎት ላይ የዋለውን መጽሐፍ ቅዱስ (የ1611 ኪንግ ጀምስ ቨርሽን) ወደ አይሪሽ ቋንቋ መተርጎም ጀመረ። የበዴል ፍላጎት በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች በቀላሉ ሊገባቸው የሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ማዘጋጀት ነበር። በዴል ድሆች መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው ቋንቋ ማግኘት ካልቻሉ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን መንገድ ለማግኘት ቅዱሳን መጻሕፍትን የመመርመር አጋጣሚ እንደሚያጡ አጽንኦት ሰጥቶ ገልጿል።—ዮሐንስ 17:3

ይህን ችግር ለመረዳት በዴል የመጀመሪያው ሰው አልነበረም። ወደ 30 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ዊሊያም ዳንኤል የሚባል አንድ ጳጳስ ማንኛውም ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት “በማያውቀው ቋንቋ በመጻፉ ከተጋረደበት” ትምህርቱን መረዳት አዳጋች እንደሚሆንበት ተገንዝቦ ነበር። ቀደም ሲል ዳንኤል የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በአይሪሽ ቋንቋ ተርጉሞ ነበር። አሁን ደግሞ በዴል የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን መተርጎም ጀመረ። የበዴል መጽሐፍ ቅዱስ እሱ የተረጎመውንና ቀደም ሲል ዊሊያም ዳንኤል ያዘጋጀውን ትርጉም አካትቶ ይዟል። ከጊዜ በኋላ እንደታየው፣ የበዴል መጽሐፍ ቅዱስ ማለትም በአይሪሽ ቋንቋ የተዘጋጀው የመጀመሪያው ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ለቀጣዮቹ 300 ዓመታት በአይሪሽ ቋንቋ የሚገኝ ብቸኛው ትርጉም ለመሆን በቅቷል።

የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሁር የሆነው በዴል ከእንግሊዝኛ ወደ አይሪሽ በመተርጎሙ ሥራ የሚያግዙት የአገሩ ተወላጅ የሆኑ ሁለት አይሪሽ ተናጋሪዎችን አገኘ። በሥራው እየገፉ ሲሄዱ በዴል እምነት ከሚጣልባቸው አንድ ወይም ሁለት ረዳቶቹ ጋር ሆኖ እያንዳንዱን ጥቅስ በከፍተኛ ጥንቃቄ እያጣራ ማስተካከያ አደረገ። ለማመሣከሪያነት የተጠቀሙት የስዊስ ተወላጅና የሃይማኖት ምሁር በሆነው በጆቫኒ ዲየዳቲ የተዘጋጀውን የጣሊያንኛ ትርጉም እንዲሁም የግሪክኛውን ሰፕቱጀንት እና አንድ ውድ የሆነ ጥንታዊ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።

የትርጉም ቡድኑ፣ የኪንግ ጀምስ ቨርሽን ተርጓሚዎችን (አብዛኞቹን በዴል በግል ያውቃቸዋል) ፈለግ የተከተሉ ከመሆኑም ሌላ የአምላክን የግል ስም በበርካታ ስፍራዎች አስገብተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘፀአት 6:3 ላይ “ኢሆቫ” በሚለው የአምላክ ስም ተጠቅመዋል። በዴል ያዘጋጀው ዋናው ቅጂ አየርላንድ፣ ደብሊን ውስጥ በማርሽ ቤተ መጻሕፍት ይገኛል።—“በዴል እውቅና ተሰጠው” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

በመጨረሻ ለሕትመት በቃ

በዴል ፕሮጀክቱን በ1640 ገደማ አጠናቀቀ። ይሁን እንጂ መጽሐፉን ወዲያውኑ ማሳተም አልቻለም። ለምን? አንደኛ ነገር የሚደርስበት ከባድ ተቃውሞ አሁንም አላባራም። ተቺዎች የትርጉም ሥራውን ዋጋ ለማሳጣት ሲሉ የበዴል ዋና ተርጓሚ የነበረውን ግለሰብ ስም አጠፉ። የክፋታቸው ክፋት ሰውየው ተይዞ እንዲታሠር አደረጉ። ይባስ ብሎም በ1641 አየርላንድ ውስጥ በእንግሊዝ አገዛዝ ላይ በማመፅ ደም አፋሳሽ የሆነ ከባድ ብጥብጥ ተከሰተ። በዴል እንግሊዛዊ ቢሆንም አየርላንዳውያን ለእነሱ ያለውን ከልብ የመነጨ አሳቢነት ስለተገነዘቡ ጉዳት እንዳይደርስበት ለተወሰነ ጊዜ ጥበቃ አደረጉለት። የኋላ ኋላ ግን ዓማፂ ወታደሮች ይዘው በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ በእስር አቆዩት። ይህ ሁኔታ በ1642 ሕይወቱ በአጭሩ እንዲቀጭ አድርጓል። በመሆኑም በዴል መጽሐፉን ታትሞ ለማየት አልታደለም።

በዴል ያዘጋጀው ዋና ቅጂ የመጀመሪያው ገጽ፣ በ1640 ገደማ፤ በ1685 የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ

በዴል ቤቱ በተበረበረና በወደመ ጊዜ የትርጉም ሥራው ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ ተቃርቦ ነበር። ደግነቱ የቅርብ ጓደኛው የሆነ አንድ ሰው በዴል ተርጉሞ ያዘጋጀውን ጽሑፍ እንዳለ ማዳን ችሏል። ከጊዜ በኋላ ጽሑፉ የአርማግ ሊቀ ጳጳስና የአየርላንድ ቤተ ክርስቲያን መሪ በሆነው ናርሲሰስ ማርሽ እጅ ገባ። እሱም የሳይንስ ሊቅ የሆነው ሮበርት ቦይል ባደረገለት የገንዘብ ድጋፍ የበዴልን መጽሐፍ ቅዱስ በ1685 ለሕትመት እንዲበቃ አደረገ፤ እርግጥ ይህን ማድረግ ድፍረት ጠይቆበታል።

አነስተኛ ግን ጉልህ እመርታ

የበዴል መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት አላተረፈም። ያም ሆኖ በአየርላንድ ብቻ ሳይሆን በስኮትላንድና በሌሎች አገሮችም ለሚኖሩ አይሪሽ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ከበፊቱ በተሻለ መረዳት እንዲችሉ የረዳ አነስተኛ ግን ጉልህ እመርታ ነበር። አሁን እነዚህ ሰዎች የአምላክን ቃል በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አንብበው መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ማርካት ይችላሉ።—ማቴዎስ 5:3, 6

“የበዴልን መጽሐፍ ቅዱስ ስናነብ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በአፍ መፍቻ ቋንቋችን በሚገባ መረዳት ችለናል። ይህ ደግሞ እኔና ቤተሰቤ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን አስደናቂ እውነቶች መማር እንድንችል በር የከፈተልን ቁልፍ ነው”

የበዴል መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ የእውነት አፍቃሪዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ማርካቱን ቀጥሏል። በአንፃራዊ ሁኔታ በቅርቡ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በትክክል የተማረ አንድ አይሪሽ ተናጋሪ እንዲህ ብሏል፦ “የበዴልን መጽሐፍ ቅዱስ ስናነብ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በአፍ መፍቻ ቋንቋችን በሚገባ መረዳት ችለናል። ይህ ደግሞ እኔና ቤተሰቤ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን አስደናቂ እውነቶች መማር እንድንችል በር የከፈተልን ቁልፍ ነው።”