በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዓለም ላይ ያሉት ቋንቋዎች የመጡት “ከባቤል ግንብ” ነው?

በዓለም ላይ ያሉት ቋንቋዎች የመጡት “ከባቤል ግንብ” ነው?

“እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ በታተናቸው፤ ከተማዋንም መሥራት አቆሙ። እግዚአብሔር በዚያ የመላውን ዓለም ቋንቋ ስለ ደበላለቀ የከተማዪቱ ስም ባቤል ተባለ።”—ዘፍጥረት 11:8, 9

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው ይህ ታሪክ በእርግጥ ተፈጽሟል? በዚህ ጥቅስ ላይ እንደተገለጸው ሰዎች የተለያዩ ቋንቋዎችን መናገር የጀመሩት በታሪክ ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ ነው? አንዳንዶች፣ ሰዎች በተለያዩ ቋንቋዎች መነጋገር የጀመሩበትንና ቋንቋዎች የተስፋፉበትን መንገድ አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ዘገባ ከእውነታው የራቀ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንድ ደራሲ “ስለ ባቤል ግንብ የሚነገረው አፈ ታሪክ እስከ ዛሬ ከተነገሩት ታሪኮች ሁሉ ጨርሶ የማይመስል ነው” በማለት ተናግረዋል። አንድ አይሁዳዊ ረቢም እንኳ ይህ ታሪክ “የብሔራትን አመጣጥ ለማስረዳት የተደረገ በእውነታ ላይ ያልተመረኮዘ ሙከራ” እንደሆነ ገልጸዋል።

ሰዎች ስለ ባቤል ግንብ የሚገልጸውን ታሪክ የሚያጣጥሉት ለምንድን ነው? በአጭር አነጋገር፣ የቋንቋን አመጣጥ አስመልክቶ ከሚሰነዘሩ አንዳንድ ጽንሰ ሐሳቦች ጋር ስለሚጋጭ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ምሁራን የተለያዩ ቋንቋዎች መነገር የጀመሩት በአንድ ወቅት ላይ እንዳልሆነ ይናገራሉ፤ ከዚህ ይልቅ የተለያዩ ቋንቋዎች ቀስ በቀስ የዳበሩት የሰው ዘር ቋንቋዎች ሁሉ መገኛ ከሆነ አንድ ቋንቋ ተነስተው እንደሆነ ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ በጥንት ዘመን የነበሩት የተለያዩ ቋንቋዎች እድገት ያደረጉት ሁሉም በየፊናቸው እንደሆነ እንዲሁም ሰዎች ቀላል የሆኑ ድምፆችን ከማሰማት ተነስተው ቀስ በቀስ ሐሳባቸውን ለመግለጽ የሚያስችል ውስብስብ ቋንቋ ማዳበር እንደቻሉ ይናገራሉ። ፕሮፌሰር ፊች ዚ ኢቮሉሽን ኦቭ ላንግዌጅ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “እስካሁን ድረስ አጥጋቢ የሆነ መልስ ማግኘት አልቻልንም” ብለዋል፤ ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ከላይ እንደተገለጹት ያሉ እርስ በርስ የሚጋጩ ጽንሰ ሐሳቦች መኖራቸው ብዙ ሰዎች እኚህ ፕሮፌሰር በተናገሩት ሐሳብ እንዲስማሙ አድርጓቸዋል።

ታዲያ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ስለ ሰው ልጅ ቋንቋዎች አጀማመርና እድገት ምን ያገኙት ነገር አለ? እነሱ ያገኟቸው ነገሮች ከላይ ከተገለጹት ጽንሰ ሐሳቦች ጋር ይስማማሉ? ወይስ ስለ ባቤል ግንብ የሚገልጸውን ታሪክ ይደግፋሉ? እስቲ በመጀመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን ይህን ዘገባ እንመርምር።

ታሪኩ የተፈጸመው የትና መቼ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሰዎች ቋንቋ የተደበላለቀውና ሰዎቹ ወደተለያየ ቦታ የተበተኑት “በሰናዖር” ይኸውም ከጊዜ በኋላ ባቢሎኒያ ተብሎ በተጠራው ስፍራ እንደሆነ ይናገራል። (ዘፍጥረት 11:2)  ይህ የሆነው መቼ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከአብርሃም ዘመን ከ250 ዓመት ገደማ ቀደም ብሎ በተወለደው በፋሌቅ ዘመን ‘ሕዝቦች ተከፋፍለው’ እንደነበር ይናገራል። ስለዚህ ስለ ባቤል የሚገልጸው ታሪክ የተፈጸመው ከ4,200 ዓመታት ገደማ በፊት ሳይሆን አይቀርም።—ዘፍጥረት 10:25 የ1980 ትርጉም፤ 11:18-26

አንዳንድ ምሁራን፣ የዘመናችን ቋንቋዎች የመነጩት ከአንድ የመጀመሪያ ቋንቋ፣ ማለትም ወደ 100,000 ከሚጠጉ ዓመታት አስቀድሞ ሰዎች ይነጋገሩበት ከነበረ አንድ ቋንቋ እንደሆነ ይገልጻሉ። * ሌሎች ደግሞ የዛሬዎቹ ቋንቋዎች ቢያንስ ከ6,000 ዓመታት በፊት ይነገሩ ከነበሩ የተለያዩ ቋንቋዎች ጋር ተዛማጅነት እንዳላቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የቋንቋ ተመራማሪዎች፣ የጠፉ ቋንቋዎች እድገት ያደረጉበትን ሂደት ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው? “ይህ አስቸጋሪ ሥራ ነው” በማለት ኢኮኖሚስት መጽሔት ይናገራል። “ከሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች በተለየ መልኩ የቋንቋ ምሁራን፣ ስላለፉት ዘመናት ለማጥናት በቅሪተ አካላት ላይ ምርምር ማድረግ አይችሉም።” መጽሔቱ አክሎ እንደተናገረው፣ ቋንቋ በጊዜ ሂደት እየተሻሻለ እንደመጣ የሚያምን አንድ የቋንቋ ምሁር አንድ ድምዳሜ ላይ የሚደርሰው “በግምታዊ ሐሳቦች ላይ የተመሠረተ ስሌት” ተጠቅሞ ነው።

ይሁንና “የቋንቋ ቅሪተ አካላት” አሉ። እነዚህ ቅሪተ አካላት ምንድን ናቸው? ደግሞስ ስለ ሰው ልጅ ቋንቋዎች አጀማመር ምን ይጠቁሙናል? ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦ “የሰው ልጅ ሊያገኝ የሚችላቸው የቋንቋ ቅሪተ አካላት ይኸውም በጽሑፍ የሰፈሩ ጥንታዊ መዛግብት ዕድሜያቸው ከ4,000 ወይም ከ5,000 ዓመታት አይበልጥም።” የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች እነዚህን “የቋንቋ ቅሪተ አካላት” ማለትም “በጽሑፍ የሰፈሩ ጥንታዊ መዛግብት” ያገኟቸው የት ነው? በታችኛው ሜሶጶጣሚያ ማለትም ጥንት ሰናዖር በነበረበት ስፍራ ነው። * በመሆኑም የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ያገኙት ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ታሪክ ጋር የሚስማማ ነው።

የተለያዩ ቋንቋዎች የተለያየ አስተሳሰብ

የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ፣ አምላክ በባቤል ሰዎቹ ‘እርስ በርሳቸው እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እንደደበላለቀው’ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 11:7) በዚህም የተነሳ ሰዎቹ የባቤልን ‘ከተማ መሥራት አቁመው በምድር ሁሉ’ ተበታተኑ። (ዘፍጥረት 11:8, 9) ከዚህ ለማየት እንደምንችለው መጽሐፍ ቅዱስ፣ የዘመናችን ቋንቋዎች በሙሉ ከአንድ ቋንቋ እንደተገኙ አይገልጽም። ከዚህ ይልቅ ሐሳብን በተሟላ ሁኔታ ለመግለጽ የሚያስችሉ በርካታ አዳዲስ ቋንቋዎች በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ብቅ እንዳሉ ይጠቁማል፤ እነዚህ ቋንቋዎች የሰዎችን የተለያዩ ስሜቶችና አመለካከቶች መግለጽ የሚችሉ ሲሆን አንዳቸው ከሌላው የተለዩ ናቸው።

በሜሶጶጣሚያ የተገኘና የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፈበት ሸክላ፣ ሦስተኛው ሺህ ዓመት ዓ.ዓ.

በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ስላሉት የተለያዩ የቋንቋ ቤተሰቦችስ ምን ለማለት ይቻላል? መሠረታዊ ተመሳሳይነት አላቸው ወይስ የተለያዩ ናቸው? ሊራ ቦሮዲትስኪ የተባሉት የሳይንስ ምሁር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የቋንቋ ጥናት ባለሙያዎች፣ የዓለምን ቋንቋዎች (7,000 ወይም ከዚያ በላይ ሲሆኑ ከእነዚህም ጥናት የተደረገባቸው በጣም ጥቂቶቹ ናቸው) ጠለቅ ብለው በመረመሩ መጠን በእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ከዚህ በፊት ያልታወቁ በርካታ ልዩነቶች አግኝተዋል።” በእርግጥም በአንድ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ቋንቋዎች ተመሳሳይነት ሊኖራቸው ቢችልም በሌላ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ ከሚገኙ ቋንቋዎች ጋር ግን መሠረታዊ የሆነ ልዩነት አላቸው፤ ለምሳሌ ትግርኛ እና አማርኛ ተመሳሳይነት ቢኖራቸውም በሌላ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ ካሉት እንግሊዝኛና ጀርመንኛ ጋር በጣም ይለያያሉ።

ቋንቋ፣ ሰዎች በአካባቢያቸው ስላሉት ነገሮች ለምሳሌ ስለ ቀለም፣ መጠን፣ ቦታና አቅጣጫ ያላቸው አመለካከት እንዲሁም እነዚህን ነገሮች የሚገልጹበት መንገድ የተለያየ እንዲሆን ያደርጋል። ለአብነት ያህል፣ በአንድ ቋንቋ “በቀኝ እጅህ ላይ ትኋን  አለ” ይባል ይሆናል። በሌላ ቋንቋ ግን ይህንኑ ሐሳብ ለመግለጽ “በደቡብ ምዕራባዊው እጅህ ላይ ትኋን አለ” ይባላል። እንዲህ ዓይነቶቹ ልዩነቶች ግራ መጋባት እንደሚፈጥሩ ምንም ጥያቄ የለውም። ከዚህ አንጻር፣ የባቤልን ግንብ ለመሥራት የተነሱት ሰዎች ግንባታውን መቀጠል አስቸጋሪ ቢሆንባቸው ምንም አያስደንቅም።

ትርጉም አልባ ድምፅ ወይስ ትርጉም አዘል ንግግር?

የሰው ልጅ የመጀመሪያ ቋንቋ ምን ይመስል ነበር? የመጀመሪያው ሰው አዳም ለሁሉም እንስሳትና የሚበሩ ፍጥረታት ስም ሲያወጣ አዳዲስ ቃላትን መፍጠር ችሎ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 2:20) በተጨማሪም አዳም ለሚስቱ ያለውን ስሜት ለመግለጽ ግጥም ገጥሟል፤ ሔዋንም አምላክ የሰጣቸውን ትእዛዝ እንዲሁም አለመታዘዝ የሚያስከትለውን መዘዝ ማብራራት ችላ ነበር። (ዘፍጥረት 2:23፤ 3:1-3) ከዚህ ለማየት እንደምንችለው የመጀመሪያው ቋንቋ፣ ሰዎች ሐሳባቸውን እንደ ልብ ለማስተላለፍ እና አዳዲስ ሐሳቦችን ለመግለጽ አስችሏቸዋል።

በባቤል ቋንቋዎች መደበላለቃቸው፣ የሰው ልጆች እውቀታቸውን አንድ ላይ አጣምረውና በጉልበት ተረዳድተው መሥራት እንዳይችሉ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል። ሆኖም አዳዲሶቹ ቋንቋዎች፣ ልክ እንደ መጀመሪያው ቋንቋ ሁሉ ሐሳብን በተሟላ መንገድ ለመግለጽ የሚያስችሉ ነበሩ። የሰው ልጆች ከተበተኑ በኋላ በጥቂት መቶ ዓመታት ውስጥ ከተሞችን መቆርቆር፣ ኃያል ሠራዊቶችን ማደራጀትና በአገራት መካከል በሚካሄዱ የንግድ እንቅስቃሴዎች መካፈል ችለው ነበር። (ዘፍጥረት 13:12፤ 14:1-11፤ 37:25) ታዲያ በርካታ ቃላትና የሰዋስው ሕግጋት ያሉት ቋንቋ ባይኖራቸው እንዲህ ዓይነቱ እድገት ላይ መድረስ ይችሉ ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የሰው ልጆች የመጀመሪያ ቋንቋም ሆነ በባቤል የተፈጠሩት ቋንቋዎች ሐሳብን በተሟላ መንገድ ለመግለጽ የሚያስችሉ እንጂ ትርጉም አልባ ድምፆች አልነበሩም።

ዘመናዊ ምርምሮችም ይህን ይደግፋሉ። ዘ ካምብሪጅ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ላንግዌጅ እንዲህ ይላል፦ “ጥናት የተካሄደባቸው ማኅበረሰቦች በሙሉ፣ ሌላው ቀርቶ ከባሕል አንጻር ‘ያልሠለጠኑ’ የሚባሉት እንኳ፣ ‘ሠልጥነዋል’ ከሚባሉት ሕዝቦች ጋር በሚወዳደር ደረጃ በደንብ የዳበረ ቋንቋ እንዳላቸው ማስተዋል ተችሏል።” በተመሳሳይም የሀርቫርድ ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ስቲቨን ፒንከር ዘ ላንግዌጅ ኢንስቲንክት በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት “በድንጋይ ዘመን ያለ” በሌላ አባባል ያልሠለጠነ ቋንቋ የለም።

የቋንቋ የወደፊት ዕጣ

የቋንቋ “ቅሪተ አካላትን” ዕድሜና የተገኙበትን ቦታ፣ በቋንቋ ቤተሰቦች መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት እንዲሁም የጥንት ቋንቋዎች ሐሳብን በተሟላ መንገድ ለመግለጽ የሚያስችሉ መሆናቸውን ከመረመርን በኋላ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? ብዙዎች፣ ‘በባቤል ስለተፈጸመው ነገር የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሙሉ በሙሉ ሊታመን የሚችል ነው’ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ አምላክ በባቤል የሕዝቡን ቋንቋ የደበላለቀው በእሱ ላይ ስላመፁ እንደሆነ ይነግረናል። (ዘፍጥረት 11:4-7) ይሁን እንጂ “አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሕን ልሳን” ወይም ቋንቋ እንደሚሰጣቸው አምላክ ቃል ገብቷል። (ሶፎንያስ 3:9 የ1954 ትርጉም) ይህ ‘ንጹሕ ልሳን’ ማለትም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነት በዛሬው ጊዜ በመላው ዓለም የሚገኙ ሕዝቦችን አንድ አድርጓቸዋል። ወደፊት ደግሞ አምላክ፣ የሰው ዘር አንድ የጋራ ቋንቋ እንዲኖረው በማድረግ እና በባቤል የተፈጠረውን ግራ መጋባት በማስተካከል የሰው ልጆች ከዚህ የበለጠ አንድነት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል።

^ አን.8 ስለ ቋንቋ የሚገልጹ ጽንሰ ሐሳቦች አብዛኛውን ጊዜ የተመሠረቱት፣ ሰዎች ከጦጣ መሰል ፍጥረታት ተሻሽለው እንደመጡ በሚገልጸው ጽንሰ ሐሳብ ላይ ነው። የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች በተሰኘው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ብሮሹር ከገጽ 27-29 ላይ ይህን ጽንሰ ሐሳብ በተመለከተ ሐሳብ ማግኘት ትችላለህ።

^ አን.9 የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች፣ አናታቸው ላይ ቤተ መቅደሶች ያሏቸውና መወጣጫ ደረጃ የተሠራላቸው ፒራሚድ መሰል ግንቦችን በሰናዖር አቅራቢያ በቁፋሮ አግኝተዋል። የባቤልን ግንብ ለመሥራት የተነሱት ሰዎች፣ በድንጋይ ሳይሆን በጡብ እንደተጠቀሙና ለማያያዣም ቅጥራን እንዳደረጉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 11:3, 4) ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚገልጸው በሜሶጶጣሚያ ድንጋይ “እንደ ልብ ላይገኝ እንዲያውም ጨርሶ ሊጠፋ” ይችላል፤ በሌላ በኩል ግን ቅጥራን በብዛት ይገኝ ነበር።