በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ስም በስዋሂሊ ማሳወቅ

የአምላክን ስም በስዋሂሊ ማሳወቅ

“ስዋሂሊ።” ብዙዎች ስለዚህ ቋንቋ ሲያስቡ መጀመሪያ ወደ አእምሯቸው የሚመጡት አፍሪካ እና የዱር አራዊት የሚፈነጩበት የሴሬንጌቲ የግጦሽ አካባቢ ነው። ይሁንና ስለዚህ ቋንቋና ስለ ተናጋሪዎቹ ከዚህ ባለፈ ብዙ ሊባል የሚችል ነገር አለ።

ስዋሂሊ፣ በትንሹ 12 በሚያህሉ የማዕከላዊና የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ 100 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የሚጠቀሙበት ቋንቋ ነው። * ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ኬንያ እንዲሁም ሌሎች አገሮች ብሔራዊ ወይም የሥራ ቋንቋቸው ስዋሂሊ ነው። በአጎራባች አገሮች ውስጥ ያሉ ሰዎችም የንግድ ልውውጥ ለማድረግና በቀላሉ ለመግባባት በዚህ ቋንቋ ይጠቀማሉ።

ስዋሂሊ የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦችን አንድ በማድረግ ረገድ በጣም ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በታንዛኒያ ብቻ ቢያንስ ቢያንስ 114 የጎሣ ቋንቋዎች ይነገራሉ። ከምትኖርበት አካባቢ ከ40 እስከ 80 ኪሎ ሜትር በሚያህል ርቀት ላይ የሚገኙት ሰዎች አንተ ከምትናገረው ፈጽሞ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ ቢሆን ምን ዓይነት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እስቲ አስበው! አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አንድን ቋንቋ የሚናገሩት በተወሰኑ ትናንሽ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ይሆናሉ። ታዲያ ከእነዚህ ሰዎች ጋር መግባባት የምትችለው እንዴት ነው? ከዚህ አንጻር አንድ የጋራ ቋንቋ መኖሩ ጠቃሚ የሆነበትን ምክንያት መረዳት አያዳግትም።

የስዋሂሊ ታሪክ

ስዋሂሊ ቢያንስ ከአሥረኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ሲነገር እንደኖረ ይታመናል። የጽሑፍ ቋንቋ የሆነው ግን በ16ኛው መቶ ዘመን ነው። ይህን ቋንቋ የሚማሩ ሰዎች ብዙዎቹ ቃላት ከአረብኛ ጋር የሚመሳሰል ነገር እንዳላቸው ለመገንዘብ ጊዜ አይወስድባቸውም። እንዲያውም ወደ 20 በመቶ የሚጠጉት የስዋሂሊ ቃላት ምንጫቸው አረብኛ ሲሆን የተቀሩት አብዛኞቹ ቃላት ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ ከሚነገሩ ቋንቋዎች የተወሰዱ ናቸው። በመሆኑም ለብዙ መቶ ዓመታት ስዋሂሊ ይጻፍ የነበረው በአረብኛ ፊደላት መሆኑ አያስደንቅም።

በዛሬው ጊዜ ስዋሂሊ የሚጻፈው በላቲን ፊደላት ነው። ይህ ለውጥ የተደረገው ለምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት፣ አንዳንድ የአውሮፓ ሚስዮናውያን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለምሥራቅ አፍሪካ ሕዝብ ለማካፈል በማሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚህ አካባቢ ወደመጡበት ወደ 19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ መመለስ ያስፈልገናል።

የአምላክ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ደረሰ

በ1499 ቫስኮ ደ ጋማ በአፍሪካ ደቡባዊ ጫፍ በኩል ባደረገው ዝነኛ ጉዞ ወቅት የፖርቹጋል ተወላጆች የሆኑ ሚስዮናውያን በዛንዚባር አንድ ሚስዮን በማቋቋም የካቶሊክ ሃይማኖት ወደ ምሥራቅ አፍሪካ እንዲገባ አደረጉ። ይሁን እንጂ ይህ በሆነ በ200 ዓመታት ውስጥ፣ በአካባቢው በተነሳ ተቃውሞ ምክንያት ፖርቹጋላውያኑ የተባረሩ ሲሆን ያቋቋሙት “የክርስትና” ሃይማኖትም እንዲጠፋ ተደረገ።

ከዚያ በኋላ ለ150 ዓመታት ያህል የአምላክ ቃል ድጋሚ በምሥራቅ አፍሪካ አልተሰበከም። በ1844 ዮሃን ሉትቪክ ክራፕፍ የሚባል አንድ የጀርመን ሚስዮናዊ የአምላክን ቃል ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ይዞ መጣ። ክራፕፍ ሞምባሳ፣ ኬንያ ሲደርስ በምሥራቅ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ በዋነኝነት የሚታወቀው ሃይማኖት እስልምና ነበር፤ በመሃል አገር የሚኖሩት ብዙዎቹ ሕዝቦች ግን ባሕላዊና መናፍስታዊ እምነቶችን ይከተሉ ነበር። ክራፕፍ፣ ሁሉም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት እንዲችል ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ያምን ነበር።

ክራፕፍ ምንም ጊዜ ሳያጠፋ ስዋሂሊ መማር ጀመረ። ከመጣ ብዙም ሳይቆይ ይኸውም ሰኔ 1844 መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎምን ተፈታታኝ ሥራ ተያያዘው። የሚያሳዝነው ግን በቀጣዩ ወር ሚስቱ፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ሕፃኗ ልጃቸው ተከታትለው በመሞታቸው ከባድ ሐዘን ላይ ወደቀ፤ ከባለቤቱ ጋር በትዳር ያሳለፉት ሁለት ዓመት ብቻ ነበር። ይህ ሁኔታ በጣም እንደጎዳው የታወቀ ቢሆንም አስፈላጊ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎሙን ሥራ ገፋበት። በ1847 የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕራፎች ታትመው ወጡ፤ ይህ በስዋሂሊ ቋንቋ ለሕትመት የበቃ የመጀመሪያው ጽሑፍ ነው።

ዮሃን ክራፕፍ በ1847 ባዘጋጀው የስዋሂሊ ትርጉም ላይ ዘፍጥረት 1:1-3

ክራፕፍ፣ ስዋሂሊን በተለመዱት የአረብኛ ፊደላት ፈንታ በላቲን ፊደላት በጽሑፍ ያሰፈረ የመጀመሪያው ሰው ነበር። ከአረብኛ ፊደላት ይልቅ የላቲንን ለመጠቀም ከመረጠባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ የኋላ ኋላ ስዋሂሊ ቋንቋን ለመማር ለሚፈልጉ “አውሮፓውያን . . . የአረብኛ ፊደላት እንቅፋት ይሆኑባቸዋል” የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ “የላቲን ፊደላት ‘የአገሬው ሕዝብ የአውሮፓውያንን ቋንቋዎች መማር’ ቀላል እንዲሆንለት ያደርጋሉ” የሚል ነው። ለብዙ ዓመታት አንዳንዶች የአረብኛውን ፊደላት መጠቀማቸውን የቀጠሉ ሲሆን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም በእነዚህ ፊደላት ታትመዋል። ይሁን እንጂ የላቲኑን ፊደላት መጠቀም ብዙዎች ስዋሂሊን መማር ቀላል እንዲሆንላቸው አድርጓል። ብዙ ሚስዮናውያንና ሌሎች የስዋሂሊ ተማሪዎች ይህ ለውጥ በመደረጉ በጣም እንደተደሰቱ ጥርጥር የለውም።

ክራፕፍ የአምላክን ቃል ወደ ስዋሂሊ ለመተርጎም ፈር ቀዳጅ ከመሆኑም በተጨማሪ ከዚያ በኋላ ለተነሱ ተርጓሚዎች መሠረት ጥሏል። በስዋሂሊ ቋንቋ የመጀመሪያውን የሰዋስው መጽሐፍና መዝገበ ቃላትም አዘጋጅቷል።

የአምላክ ስም በስዋሂሊ

በ1891 በአረብኛ ፊደላት በተዘጋጀ የስዋሂሊ ትርጉም ላይ ማቴዎስ ምዕራፍ 1 በከፊል

የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ሦስት ምዕራፎች ለመጀመሪያ ጊዜ በታተሙበት ጽሑፍ ላይ የአምላክ ስም የተተረጎመው “ሁሉን ቻይ አምላክ” እየተባለ ነበር። ይሁን እንጂ በ19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ አካባቢ ሌሎች በርካታ ሰዎች ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የመጡ ሲሆን ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በስዋሂሊ መተርጎም ጀመሩ። ከእነሱ መካከል ዮሃን ራፕማን፣ ዊሊያም ቴይለር፣ ሃሪ ቢንስ፣ ኤድዋርድ ስቲር፣ ፍራንስስ ሃጅሰን እና አርተር ማደን ይገኙበታል።

እነዚህ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ባዘጋጇቸው አንዳንድ ትርጉሞች ውስጥ የአምላክ ስም በጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በሙሉ መካተቱ ትኩረት የሚስብ ነው! ዛንዚባር ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን የተረጎሙት ሰዎች መለኮታዊውን ስም “ያሁዋ” ያሉት ሲሆን ሞምባሳ ሆነው የተረጎሙት ደግሞ “ጄሆቫ” ብለውታል።

በ1895 ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በስዋሂሊ ማግኘት ተቻለ። በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት በርከት ያሉ ሌሎች ትርጉሞች ተዘጋጁ፤ በእርግጥ ከእነዚህ ትርጉሞች ውስጥ አንዳንዶቹ በስፋት አልተሰራጩም። በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ አካባቢ በምሥራቅ አፍሪካ የሚነገረው ስዋሂሊ ወጥ እንዲሆን ብዙ ጥረት ተደርጓል። ይህም ስዋሂሊ ዩኒየን ቨርሽን የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በ1952 እንዲዘጋጅ መንገድ የከፈተ ሲሆን ይህ ትርጉም ሰፊ ስርጭት አግኝቷል። የዚህ ትርጉም መውጣት “ዬሆቫ” የሚለው የአምላክ ስም አጠራር በስዋሂሊ በስፋት ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጓል።

“ስዋሂሊ ዩኒየን ቨርሽን” በተባለው ትርጉም የመግቢያ ገጽ ላይ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም የሚገኝበት አንቀጽ

የሚያሳዝነው ነገር እነዚያ የመጀመሪያ ትርጉሞች መታተማቸው ሲቀር መለኮታዊው ስምም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መካተቱ እየቀረ መጣ። ከአዳዲሶቹ ትርጉሞች አንዳንዶቹ መለኮታዊውን ስም ሙሉ በሙሉ ከትርጉማቸው ውስጥ ያወጡት ሲሆን ሌሎች ደግሞ በጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ አስገብተውታል። ለምሳሌ ያህል፣ ዩኒየን ቨርሽን በተባለው ትርጉም ውስጥ የአምላክ ስም 15 ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሲሆን በ2006 ታርሞ በተዘጋጀው እትም ላይ ደግሞ 11 ጊዜ ብቻ ይገኛል። *

መለኮታዊውን ስም “ያሁዋ” እና “ጄሆቫ” ብለው የተረጎሙት የመጀመሪያዎቹ ትርጉሞች

ይህ ትርጉም መለኮታዊውን ስም ከእነዚህ ቦታዎች በቀር ጨርሶ ቢያወጣውም አንድ አስገራሚ ገጽታ አለው። ከመግቢያ ገጾቹ በአንዱ ላይ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ ጉልህ በሆነ መንገድ ሰፍሯል። ይህም እውነትን የሚፈልጉ ሰዎች የሰማዩ አባታችንን የግል ስም ከራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲማሩ ለመርዳት በጣም ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል።

ይሁንና በስዋሂሊ ከተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጋር በተያያዘ ሌላም ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ክንውን ተፈጽሟል። በ1996 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በስዋሂሊ ወጣ። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከማቴዎስ እስከ ራእይ ድረስ በ237 ቦታዎች ላይ የይሖዋ ስም መጀመሪያ ወደነበረበት ቦታ እንዲመለስ ያደረገ የመጀመሪያው የስዋሂሊ ትርጉም ነው። በማስከተልም ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በዚሁ ቋንቋ በ2003 ወጣ። እስካሁን ድረስ 900,000 የሚያህሉ የአዲስ ዓለም ትርጉም ቅጂዎች ታትመዋል።

የአምላክ ስም፣ በአንዳንድ የማዕረግ ስሞች የሚተካበት ወይም በመቅድም ላይ በሚሰፍሩ የማብራሪያ ሐሳቦች ላይ ብቻ የሚገኝበት ዘመን አልፏል። በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ስም በስዋሂሊ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከ7,000 ጊዜ በላይ ይገኛል፤ በመሆኑም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱሳቸው ላይ ይሖዋ የሚለውን ስም በተደጋጋሚ ማንበባቸው ወደ እሱ ይበልጥ እንዲቀርቡ ይረዳቸዋል።

ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ሁሉም የስዋሂሊ ተናጋሪዎች ሊረዱት በሚችሉ ቀላል የሆነ ዘመናዊ ስዋሂሊ ለማዘጋጀት ጥረት ተደርጓል። በተጨማሪም በሌሎች ትርጉሞች ውስጥ በበርካታ ጥቅሶች ላይ የሚገኙት ስህተቶች በዚህ ትርጉም ላይ እንዲስተካከሉ ተደርገዋል። በዚህም የተነሳ ይህን ትርጉም የሚያነብብ ሰው፣ ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ በመንፈሱ መሪነት ያስጻፈውን ‘ትክክለኛ ቃል’ እያነበበ እንደሆነ መተማመን ይችላል።—መክብብ 12:10

ብዙዎች በስዋሂሊ በተዘጋጀው “የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም” መጠቀም ያስደስታቸዋል

ብዙዎች በስዋሂሊ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘታቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በሙሉ ጊዜው አምላክን የሚያገለግል የይሖዋ ምሥክር የሆነው የ21 ዓመቱ ቪሴንት “አዲስ ዓለም ትርጉም በቀላል ስዋሂሊ የቀረበ በመሆኑና የይሖዋን ስም ሌሎቹ ትርጉሞች ባወጧቸው ቦታዎች ላይ መልሶ በማስገባቱ በጣም ተደስቻለሁ” ብሏል። ፍሪዳ የምትባል የሦስት ልጆች እናት ደግሞ ይህ ትርጉም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች ማስረዳት ቀላል እንዲሆንላት እንዳደረገ ይሰማታል።

የአምላክን ቃል ወደ ስዋሂሊ ለመተርጎም ከተደረገው የመጀመሪያ ሙከራ አንስቶ ይህ ሥራ ከ150 ለሚበልጡ ዓመታት ሲከናወን ቆይቷል። ኢየሱስ ‘የአባቱን ስም እንደገለጠ’ ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 17:6) በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛው እና በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙት ከ76,000 በላይ የሚሆኑ ስዋሂሊ ተናጋሪ የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ዓለም ትርጉምን በመጠቀም የይሖዋን ስም በማሳወቁ ሥራ ተካፋይ በመሆናቸው ደስተኞች ናቸው።

^ አን.3 በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚሠራበት ስዋሂሊ በተወሰነ መጠን ይለያያል።

^ አን.18 መለኮታዊው ስም የሚገኝባቸው ቦታዎች ዘፍጥረት 22:14፤ ዘፀአት 6:2-8 (ሁለት ጊዜ)፤ 17:15 (ያህዌ ተብሎ)፤ መሳፍንት 6:24፤ መዝሙር 68:20፤ 83:18፤ ኢሳይያስ 12:2፤ 26:4፤ 49:14 እና ኤርምያስ 16:21 ናቸው።