በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ሰላም መፍጠር የሚቻለው እንዴት ነው?

ሰላም መፍጠር የሚቻለው እንዴት ነው?

ፍራንክና ጄሪ ተስማምተው የሚኖሩ ጎረቤታሞች ነበሩ፤ በመካከላቸው የነበረው ግንኙነት የተለወጠው ጄሪ ቤቱ ውስጥ እስከ ሌሊት የቆየ ግብዣ ባዘጋጀበት ዕለት ነበር። * ፍራንክ ጫጫታው እንደረበሸው ገለጸ፤ ጄሪ ደግሞ ፍራንክ በተናገረበት መንገድ በጣም ተከፋ። በዚህ ምክንያት መጨቃጨቅ ጀመሩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተኮራረፉ።

ፍራንክና ጄሪ ያጋጠማቸው ችግር የተለመደ ነው። ሁለት ሰዎች በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር ብዙውን ጊዜ በንዴት ይጦፋሉ፤ እንዲሁም አንዱ ሌላውን ሊወነጅል ይችላል። ይህን ሁኔታ ለማስተካከል እርምጃ ካልወሰዱ ጓደኝነታቸው ሊያከትም ይችላል።

አንተም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞህ የሚያውቅ ከሆነ ሁኔታው እንዳላስደሰተህ ግልጽ ነው! በእርግጥ፣ አብዛኞቻችን ከወዳጆቻችንና ከጎረቤቶቻችን ጋር በሰላምና በስምምነት መኖር እንፈልጋለን። ይሁንና አልፎ አልፎ አለመግባባት ቢፈጠርስ? በውስጣችን ያሉትን መጥፎ ባሕርያት ማሸነፍና ስሜታችንን የጎዳንን ሰው ይቅር ማለት እንችላለን? የተፈጠረውን አለመግባባት ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታትስ እንችላለን?

የፍራንክንና የጄሪን ሁኔታ ተመልከት። ሁለቱም ወዳጅነታቸው እንዲፈርስ ምክንያት የሚሆኑ በርካታ ነገሮችን አድርገዋል፦ (1) ጄሪ አሳቢነት አላሳየም፤ (2) ፍራንክ ብስጭቱን የገለጸው ጄሪን በሚያናድድ መንገድ ነበር፤ (3) ሁለቱም ስሜታቸውን መቆጣጠር አልቻሉም፤ (4) ሰላም ለመፍጠር ምንም ጥረት አላደረጉም።

ከጊዜ በኋላ ግን ሁኔታውን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መመልከትና የተፈጠረውን አለመግባባት ትተው ሰላም መፍጠር ቻሉ። ለዚህ የረዳቸው ምንድን ነው? አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ወዳጅነት እንዳይፈርስ ብቻ ሳይሆን ከተፈጠረው ችግር በኋላም ወዳጅነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር የሚረዱ ጠቃሚ መመሪያዎችን መከተላቸው ነው።

እነዚህ መመሪያዎች በዓለም ላይ በስርጭት ረገድ ተወዳዳሪ በሌለው መጽሐፍ ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰላም እንዲሰፍንና የደረሰው የስሜት ቁስል እንዲሽር የሚረዱ እንደ ማስተዋል፣ ደግነት፣ ፍቅርና ትዕግሥት ያሉ ባሕርያትን እንድናፈራ ያበረታታል።—ምሳሌ 14:29፤ 1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

 መጽሐፍ ቅዱስ የፍራንክንና የጄሪን ብቻ ሳይሆን የብዙ ሰዎችን ሕይወት መለወጥ ችሏል። ሥር የሰደዱ መጥፎ ባሕርያትን ማስወገድ የቻሉ ሰዎችን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳዩ ብዙ ተሞክሮዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአውስትራሊያ የሚኖረው ሮበርት ሥር የሰደደ የግልፍተኝነት ባሕሪውን ማሸነፍ ችሏል። በኢስት ቲሞር የሚኖረው ኔልሰን ደግሞ ለረጅም ጊዜ የቆየ ጥላቻውን በመተው ቀድሞ እንደ ጠላት ይቆጥረው ከነበረው ሰው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሥርቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ሮበርትንና ኔልሰንን የረዳቸው እንዴት ነው? ንቁ! መጽሔት ከሁለቱም ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል።

ቃለ መጠይቅ 1

ሮበርት፣ እስቲ ስለ አስተዳደግህ ጥቂት አጫውተን።

ያደግሁት ደስታ በራቀው ቤተሰብ ውስጥ ነው። አባቴ ግልፍተኛ ስለነበር ብዙውን ጊዜ ይደበድበኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደም በደም ሆኜ ራሴን እስክስት ድረስ ይደበድበኛል። በመሆኑም እኔም እያደር ይበልጥ ግልፍተኛና ዓመፀኛ ሆንኩ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ በፀባይ ማረሚያ ውስጥ ሁለት ዓመታት አሳልፌያለሁ። በኋላም ከባድ ወንጀል በመፈጸሜ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት እስር ቤት ገባሁ። ከእስር ቤት ስለቀቅ ሕይወትን እንደ አዲስ ለመጀመር በማሰብ ወደ አውስትራሊያ ሄድኩ።

ሮበርት ከልጅነቱ ጀምሮ ቁጡና ዓመፀኛ የነበረ ሲሆን እስር ቤት የገባበት ጊዜም አለ

ወደዚያ መሄድህ ባሕሪህን ለማስተካከል ረድቶሃል?

ፀባዬን ለመለወጥ የረዳኝ ወደዚያ መሄዴ ሳይሆን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ ነው። ይሁን እንጂ የግልፍተኝነት ባሕሪዬን መቆጣጠር በጣም ከባድ ሆኖብኝ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ብዙውን ጊዜ የተስፋ መቁረጥና የዋጋ ቢስነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። አንድ ቀን ግን በምሳሌ 19:11 (NW) ላይ በሚገኘውና “ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል፤ በደልንም መተዉ ውበት ያጎናጽፈዋል” በሚለው ሐሳብ ላይ አሰላሰልኩ። እኔም ይህን ዓይነቱን ማስተዋል ለማግኘት ጓጓሁ፤ በመሆኑም ከአንድ ሰው ስሜት፣ ንግግር ወይም ድርጊት በስተ ጀርባ ያለው ምን እንደሆነ ማሰብ ጀመርኩ። በዚህም የተነሳ ይበልጥ የሰው ችግር የሚገባኝ፣ ታጋሽና ይቅር ባይ እየሆንኩ መጣሁ።

ይህን በተግባር ያሳየህበትን አንድ ምሳሌ ልትነግረን ትችላለህ?

በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛዬን ሳላስበው አናደድኩት፤ እሱም ሰዎች ባሉበት ተናገረኝ። በዚህ ጊዜ በጣም እንዳዋረደኝ ተሰማኝ! ይሁን እንጂ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አስታወስኩና ወዲያውኑ ይቅርታ ጠየቅሁት። (ሮም 12:17) በኋላም ጓደኛዬ ቁጣው ሲበርድ ሄጄ ብቻውን አነጋገርኩት፤ በዚህ ወቅት በቤተሰቡ ውስጥ ችግር እንዳጋጠመው ተረዳሁ። ስለዚህ ሰላም መፍጠር ቻልን፤ እንዲያውም ከጊዜ በኋላ አንድ የሚያምር ኮት ሰጠኝ። እንደ ቀድሞው ግልፍተኛ ብሆን ኖሮ እንደዚያ ሲያዋርደኝ በንዴት ምን ላደርገው እንደምችል ሳስበው ይዘገንነኛል።

በቤተሰብ ውስጥ ችግር ሲያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ?

እኔና ባለቤቴ 20 ዓመት የሆነው ልጅ አለን፤ እንደ ሌሎች ቤተሰቦች ሁሉ እኛም አለመግባባት ያጋጥመናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ይቅርታ” የማለትን አስፈላጊነት ጨምሮ ብዙ ነገር አስተምሮኛል። ከልብ በመነጨ ስሜት ይቅርታ መጠየቅ ጠብን ለማስቀረት ወይም ለማብረድ የሚያስችል ከፍተኛ ኃይል እንዳለው አስተውያለሁ።

 ቃለ መጠይቅ 2

ኔልሰን፣ በቀላሉ የምትቀረብና ተግባቢ ነህ። ይሁንና በአንድ ወቅት ሥር የሰደደ ጥላቻ ነበረህ አይደል?

አዎን! ወጣት ሳለሁ መንግሥትን የሚቃወም አንድ የፖለቲካ ቡድን አባል ሆኜ ነበር። በተጨማሪም እኔ የምኖርበትን አውራጃ ለመቆጣጠር ይሞክር ለነበረው ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ ጥላቻ ነበረኝ። እንዲሁም ማርሻል አርት ሠልጥኜ ተደባዳቢ ሆንኩ፤ ከዚያም የሚያበሳጨኝን ሰው ሁሉ መደብደብ ጀመርኩ።

ኔልሰን ወጣት ሳለ የአንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድን አባል ነበር

ለውጥ እንድታደርግ ያነሳሳህ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና የተማርኩትን በሥራ ላይ ማዋል ጀመርኩ፤ ከተማርኩት ውስጥ በተለይ ሁለቱ ልቤን ነክተውታል። የመጀመሪያው “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል” የሚለው ነው። (ማቴዎስ 7:12) ሁለተኛው ደግሞ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ይላል። (ማቴዎስ 22:39) መጽሐፍ ቅዱስን ያስተማሩኝ የይሖዋ ምሥክሮች የዘር ወይም የጎሣ ልዩነት ሳያደርጉ ለሁሉም ሰው እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንደሚያሳዩ አስተዋልኩ። እኔም እንደ እነሱ መሆን ፈለግሁ። በዚህ ረገድ ስለተሳካልኝ ቀድሞ የሚያውቁኝ ሰዎች በጣም ተገረሙ፤ እኔን መፍራታቸውንም አቆሙ።

የቀድሞ ፀባይህ አገርሽቶብህ ያውቃል?

ከቤት ውጭ አገርሽቶብኝ አያውቅም። ቤት ውስጥ ግን አንዳንድ ጊዜ ስሜቴን መቆጣጠር ያቅተኝ ነበር። እንዲያውም አንድ ቀን በጣም ስለተናደድኩ ባለቤቴን መታኋት፤ በዚህም በጣም ተጸጸትኩ። ይሁንና ባለቤቴ በደግነት ይቅር አለችኝ፤ ይህም ስሜቴን ለመቆጣጠር ከቀድሞው የበለጠ ቁርጥ ውሳኔ እንዳደርግ አነሳሳኝ።

ሰዎች አንተን መፍራታቸውን እንዳቆሙ ተናግረሃል። ይህን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ልትነግረን ትችላለህ?

አዎን። አንድ ቀን፣ ቀደም ብዬ የጠቀስኩት ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ካለው ከአውጉስቶ ጋር ተገናኘሁ። መጀመሪያ ላይ ስጋት አድሮበት ነበር። እኔ ግን ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጠሁትና ልዩነታችንን መርሳት እንዳለብን ነገርኩት፤ ከዚያም ወደ ቤቴ እንዲመጣ ጋበዝኩት። አውጉስቶ ግብዣዬን ተቀብሎ የመጣ ሲሆን ባደረግሁት ለውጥ በጣም ተገረመ፤ በመሆኑም እሱም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። አሁን እኔና አውጉስቶ የቅርብ ጓደኛሞች ብቻ ሳንሆን መንፈሳዊ ወንድማማቾችም ነን።

 ‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ’

የጠብ መንስኤዎች ውስብስብና የተለያዩ ናቸው፤ በተጨማሪም ሰላም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት በጎ ምላሽ የሚሰጠው ሁሉም ሰው አይደለም። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” የሚል እውነታውን ያገናዘበ ምክር ይሰጣል።—ሮም 12:18

በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ኃይል እንዳለው የሚያሳዩ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው፤ መጽሐፍ ቅዱስ እኛ ፈቃደኛ እስከሆንን ድረስ እንደ “ምሽግ” ያሉ ሥር የሰደዱ መጥፎ ባሕርያትን ለመደርመስ ይረዳናል። (2 ቆሮንቶስ 10:4) ምሳሌ 3:17, 18 ጥበብን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ “መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤ የሚይዟትም ይባረካሉ።”

ኔልሰንና አውጉስቶ አሁን ጥሩ ጓደኛሞች ናቸው

አንተስ ይበልጥ ደስተኛና ሰላማዊ መሆን ትፈልጋለህ? ከሰዎች ጋር ችግር የማይፈታው የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖርህ ትመኛለህ? ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ መንገዱን እንዲያሳይህ ፈቃደኛ ሁን፤ ይህን በማድረግህ ፈጽሞ አትቆጭም።

^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።