በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የዋንደሪንግ አልባትሮስ ኃይል ቆጣቢ የበረራ ዘዴ

የዋንደሪንግ አልባትሮስ ኃይል ቆጣቢ የበረራ ዘዴ

አንዳንድ አዕዋፍ በሚበርሩበት ወቅት በፍጥነት ወደ ላይ የሚወነጨፉ ሲሆን ይህም በአየር ላይ ተንሳፍፎ መቆየት ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። ዋንደሪንግ አልባትሮስ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ክንፉ ከጫፍ እስከ ጫፍ 3.4 ሜትር የሚደርሰውና እስከ 8.5 ኪሎ ግራም የሚደርስ ክብደት ያለው ይህ ወፍ ብዙም ጉልበት ማውጣት ሳያስፈልገው በሺህዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች መብረር ይችላል! ሚስጥሩ ያለው ሰውነቱ በሚሠራበት መንገድና በሚበርርበት ወቅት ወደ ላይ ተወንጭፎ በሚወጣበት ዘዴ ላይ ነው።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አልባትሮስ በሚበርርበት ጊዜ ክንፎቹ ሙሉ በሙሉ ከተዘረጉ በኋላ እንደተዘረጉ እንዲቆዩ የሚያስችሉት ለየት ያሉ ጅማቶች አሉት፤ በዚህ ጊዜ በጡንቻዎቹ መጠቀም ስለማያስፈልገው ጡንቻዎቹን ማሳረፍ ይችላል። የዚህ ወፍ ሌላው ሚስጥር ደግሞ በሚበርርበት ወቅት በየመሃሉ ወደ ላይ የሚወነጨፍበት መንገድ ሲሆን እንዲህ ማድረግ የቻለው በውቅያኖስ ላይ የሚነሱ ነፋሳትን ጥሩ አድርጎ ስለሚጠቀም ነው።

አልባትሮሶች በባሕር ላይ በሚበርሩበት ጊዜ መጀመሪያ ወደ ላይ ከወጡ በኋላ አቅጣጫቸውን በመቀየር በግማሽ ክብ ቅርጽ ወደ ታች ይወርዳሉ፤ በተደጋጋሚ እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረጉ መብረራቸው የአየሩን ግፊት ተቋቁመው ፍጥነታቸውን ሳይቀንሱ ለመብረር ያስችላቸዋል። የሳይንስ ሊቃውንት፣ የተራቀቁ የመከታተያ ካሜራዎችንና ልዩ የሆነ የኮምፒውተር ሶፍት ዌር ተጠቅመው እነዚህ ወፎች ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ የቻሉት በቅርቡ ነው። እነዚህ ተመራማሪዎች፣ አልባትሮሶች የሚያስፈልጋቸውን ኃይል የሚያገኙት ከፍ ብለው ከበረሩ በኋላ ወደ ታች መውረድ ሲጀምሩ እንደሆነ መገንዘብ ችለዋል። ወፎቹ መጀመሪያ ነፋሱን እየሰጠነቁ ወደ ላይ ይወጣሉ፤ ከዚያም አቅጣጫቸውን በመቀየር በነፋሱ ትይዩ ሆነው ወደ ታች ይወርዳሉ። የሳይንስ ሊቃውንት “ኃይል የሚያገኙበት ሂደት የተስተካከለና ቀጣይ ነው” ይላሉ። ውጤቱስ? እነዚህ አዕዋፍ አንድም ጊዜ ክንፋቸውን ሳያራግቡ ለበርካታ ሰዓታት መብረር ይችላሉ!

መሐንዲሶች ይህን እውቀት ማግኘታቸው ነዳጅ ቆጣቢ የሆኑ፣ ምናልባትም ያለሞተር የሚሠሩ የበረራ መሣሪያዎችን ንድፍ ለማውጣት ያስችላቸው ይሆናል።

ምን ይመስልሃል? የአልባትሮስ ኃይል ቆጣቢ የበረራ ዘዴ እና ሰውነቱ የሚሠራበት ልዩ መንገድ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?