በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በቃኝ፣ መገላገል እፈልጋለሁ!”

“በቃኝ፣ መገላገል እፈልጋለሁ!”

ቤቱ ውድቅድቅ ያለ መሆኑ ለረጅም ጊዜ ችላ እንደተባለ ያስታውቃል። ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ በውሽንፍር የተመታ ሲሆን በአንዳንዶቹ ወቅቶች ከባድ ጉዳት ደርሶበታል። አሁን ግን ምሰሶው ስለተናጋ ቤቱ መፍረሱ የማይቀር ይመስላል።

ይህ ምሳሌ በዛሬው ጊዜ ብዙ ትዳሮች የሚገኙበትን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። እናንተስ ትዳራችሁ ወደዚህ አቅጣጫ እያመራ እንደሆነ ይሰማችኋል? ከሆነ ችግር የማያጋጥመው ትዳር እንደሌለ እርግጠኛ ሁኑ። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያገቡ ሰዎች “በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል” በማለት እውነታውን በግልጽ አስቀምጦታል።—1 ቆሮንቶስ 7:28

አንድ የተመራማሪዎች ቡድን የሰጠው ሐሳብ የዚህን ጥቅስ እውነተኝነት ያጠናክራል፤ ጋብቻ “በማኅበረሰባችን ውስጥ አብዛኞቹ ሰዎች በተለምዶ የሚወስዱት በጣም አደገኛ እርምጃ” እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “በጣም አስደሳች የነበረውና በብሩህ ተስፋ የተጀመረው ግንኙነት አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ካጋጠሙት ሁሉ የከፋ ሥቃይና ብስጭት የሚያስከትልበት ሊሆን ይችላል።”

የእናንተስ ትዳር? ከታች ከተዘረዘሩት ችግሮች ቢያንስ አንዱ ትዳራችሁን እየበጠበጠው ነው?

  •  የማያባራ ጭቅጭቅ

  •  መራራ ንግግር

  •  ውስልትና

  •  ቅሬታና ምሬት

ትዳራችሁ እንደተናጋና ሊፈርስ እንደተቃረበ የሚሰማችሁ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? መፍትሔው መፋታት ነው?