በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጤናማ እናቶች፣ ጤናማ ሕፃናት

ጤናማ እናቶች፣ ጤናማ ሕፃናት

ጤናማ እናቶች፣ ጤናማ ሕፃናት

ናማ የሆነው ሕፃን በምትወደው እናቱ እቅፍ ውስጥ ለሽ ብሎ ተኝቷል። በአባትየው ፊት ላይ ደግሞ ኩራት ይነበባል። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ስለሚወለዱ አስደሳች የሆነው ይህ ክንውን እንደዋዛ ይታያል። ደግሞም ልጅ መውለድ ተፈጥሯዊ ነው፤ ታዲያ ምን የሚያስጨንቅ ነገር አለው?

እርግጥ ነው፣ ልጅ መውለድ አብዛኛውን ጊዜ በሰላም የሚከናወን ሂደት ቢሆንም ሁልጊዜ እንደዚያ ነው ማለት ግን አይደለም። በመሆኑም ለመውለድ የሚያስቡ አስተዋይ ወላጆች አላስፈላጊ ችግሮችን ለማስወገድ አስቀድመው የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ልጅ ከመውለድ ጋር ለተያያዙ ችግሮች መንስኤ የሚሆኑትን ነገሮች ለማወቅ እንዲሁም እናትየው ጥሩ የሆነ የቅድመ ወሊድ የሕክምና ክትትል እንድታገኝ ለማድረግ ይጥራሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ በምጥና በወሊድ ወቅት የሚያጋጥሙ አደገኛ ሁኔታዎችን ለመቀነስ አንዳንድ ቀላል እርምጃዎችን ይወስዳሉ። እስቲ ለመውለድ የሚያስቡ ወላጆች ሊወስዷቸው የሚገቡትን እነዚህን እርምጃዎች በዝርዝር እንመልከት።

ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮች መንስኤ

ከመውለድ ጋር በተያያዘ እናትየውም ሆነ ሕፃኑ ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች አንዱ መንስኤ እናትየው በእርግዝና ወቅት ጥሩ እንክብካቤ አለማግኘቷ ነው። በሆንግ ኮንግ የሚገኘው የፕሪንስ ኦቭ ዌልስ ሆስፒታል በአራስ ልጆች እንክብካቤ ክፍል ውስጥ የሕፃናት ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ቹንግ ካምላኡ እንዲህ ብለዋል፦ “እናቶች በእርግዝና ወቅት እንክብካቤ አለማግኘታቸው ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። . . . [በእርግዝናቸው ወቅት እንክብካቤ ከማያገኙት] እናቶች አብዛኞቹ ጤናማና የፋፉ ሕፃናት ለመውለድ ይጠብቃሉ፤ ሆኖም ሁኔታው ሁልጊዜ እንደሚታሰበው አይሆንም።”

ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል ውሜንስ አሶሲዬሽን እናቶች ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ችግሮችን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “በወሊድ ወቅት ለእናቶች ሞት ዋነኛ መንስኤ ከሆኑት ነገሮች መካከል ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ከመጠን በላይ ደም መፍሰስ፣ ከፅንሱ አመጣጥ ጋር በተያያዘ ችግሮች መኖራቸው፣ የኢንፌክሽን መፈጠር እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት ናቸው።” ይሁን እንጂ መጽሔቱ አክሎ እንደገለጸው እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ የሚረዱ የታወቁ ውጤታማ ሕክምናዎች አሉ፤ አብዛኛውን ጊዜም እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ የሚያስፈልገው “ዘመናዊ ሕክምና . . . እጅግ የተራቀቀ መሆን አይኖርበትም።”

ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ ሕክምና በቀላሉ ሊገኝ ቢችል ኖሮ ብዙ ሕፃናት ይተርፉ ነበር። ዩኤን ክሮኒክል እንደዘገበው “ሁሉም እናቶችና አራስ ልጆች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉና ውስብስብ የሕክምና መሣሪያ የማይጠይቁ ብሎም በሚገባ የታወቁ” ሕክምናዎችን ማግኘት ቢችሉ “ከሚሞቱት አራስ ሕፃናት መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑትን ማዳን ይቻላል።” የሚያሳዝነው ግን ብዙውን ጊዜ እናቶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንደማያውቁና የቅድመ ወሊድ የሕክምና ክትትል እንደማያደርጉ ፊሊፒንስ ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቧል።

እናቶችና ሕፃናት ጥሩ የቅድመ ወሊድ የሕክምና ክትትል እንዲያገኙ ማድረግ

“ጤናማ እናቶች፣ ጤናማ ሕፃናት ይኖሯቸዋል” በማለት ዩኤን ክሮኒክል ይናገራል። በተጨማሪም ይኸው ምንጭ እንደገለጸው አንዲት ሴት በእርግዝና ወራት፣ በምትወልድበት ጊዜና ከዚያ በኋላ በቂ ወይም ምንም የሕክምና ክትትል ካልተደረገላት ሕፃኑም እንዲሁ በቂ ወይም ምንም የሕክምና ክትትል አይደረግለትም።

በአንዳንድ አገሮች አንዲት ነፍሰ ጡር በቂ የሆነ የሕክምና ክትትል ማግኘት አዳጋች ሊሆንባት ይችላል። ምናልባትም ረጅም ርቀት መጓዝ ሊኖርባት አለዚያም የሕክምና ወጪዎቿን ለመሸፈን አቅሟ ላይፈቅድ ይችላል። ያም ቢሆን አንዲት እርጉዝ ሴት የሚቻል ከሆነ የተወሰነ የቅድመ ወሊድ የሕክምና ክትትል ለማግኘት መጣር ይኖርባታል። በተለይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ትምህርቶች መሠረት የምትኖር ሴት እንዲህ ማድረጓ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ያልተወለደውን ሕፃን ሕይወት ጨምሮ የሰው ሕይወት ቅዱስ እንደሆነ ይናገራል።—ዘፀአት 21:22, 23 * ዘዳግም 22:8

በቂ የሕክምና ክትትል ማድረግ ሲባል በየሳምንቱ ሐኪም ዘንድ ሄዶ መመርመር ማለት ነው? እንደዚያ ማለት ላይሆን ይችላል። የዓለም የጤና ድርጅት፣ ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥሙ አንዳንድ ችግሮችን በተመለከተ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው “በእርግዝናቸው ወራት አራት ጊዜ ብቻ ሐኪም ዘንድ ሄደው የተመረመሩ ሴቶች 12 ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ በሐኪም ከተመረመሩ ሴቶች ጋር ሲወዳደሩ” ያገኙት ጥቅም ተመሳሳይ ነው።

ሐኪሞች ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር

የሕክምና ባለሙያዎች በተለይም በእርግዝናና በወሊድ ዙሪያ ልዩ ሥልጠና ያገኙ ሐኪሞች የእናቲቱንም ሆነ የፅንሱን ጤንነት ለመጠበቅ የሚከተሉትን እርምጃዎች ይወስዳሉ፦

የነፍሰ ጡሯን የቀድሞ የጤና ሁኔታ የሚያሳዩ መረጃዎችን የሚመለከቱ ከመሆኑም በላይ እናቲቱንም ሆነ በማደግ ላይ ያለውን ፅንስ የሚነኩ የጤና ችግሮች መኖራቸውን ለማወቅ እንዲሁም ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል ሲሉ ምርመራዎችን ያደርጋሉ።

ሐኪሞቹ እንደ ደም ማነስ፣ ኢንፌክሽንና አርኤች ኢንኮምፓተብሊቲ የሚባለው በእናቲቱና በሕፃኑ ደም አለመጣጣም የተነሳ የሚፈጠር ችግር እንዲሁም ሌሎች በሽታዎች መኖራቸውን ለመመርመር የደምና የሽንት ናሙናዎችን ይወስዱ ይሆናል። እናቲቱ እንደ ስኳር በሽታ፣ ኩፍኝ፣ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችና የኩላሊት ሕመም የመሳሰሉት የጤና ችግሮች ይኖሩባት እንደሆነ በምርመራ ያረጋግጣሉ።

ነፍሰ ጡሯ እንደ ኢንፍሉዌንዛ፣ ቴታነስና አርኤች ኢንኮምፓተብሊቲ ላሉት የጤና ችግሮች ክትባት መውሰድ የሚያስፈልጋት ከሆነና እሷም ከተስማማች ክትባቱን እንድትወስድ ሐሳብ ያቀርቡላት ይሆናል።

በተጨማሪም ቪታሚኖችን በተለይም ከአረንጓዴ አትክልቶች፣ ከፍራፍሬዎችና ከጉበት የሚገኘውን ፎሊክ አሲድ እንድትወስድ ሊያዙላት ይችላሉ።

ሐኪሞች ከእያንዳንዱ እርግዝና ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና ችግሮችን ለይተው ካወቁና አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ካደረጉ ወይም እናቲቱ እንዲህ እንድታደርግ ከረዷት እሷም ሆነች ያልተወለደው ሕፃን ጤናማ የመሆናቸው አጋጣሚ ሰፊ እንዲሆን ያደርጋሉ።

በምጥና በወሊድ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቀነስ

በዓለም የጤና ድርጅት ውስጥ የቤተሰብና የማኅበረሰብ ጤና ረዳት ዳይሬክተር የነበሩት ጆይ ፑማፒ “ለአንዲት ነፍሰ ጡር ሴት በጣም አደገኛው ጊዜ የምጥና የወሊድ ወቅት ነው” በማለት ተናግረዋል። ታዲያ በዚህ አስጊ ወቅት ከባድ የሆኑ ብሎም ለሕይወት የሚያሰጉ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል ምን ሊደረግ ይችላል? እንደ እውነቱ ከሆነ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ቀላል ናቸው፤ ሆኖም እናቲቱ ችግሮቹ ከመከሰታቸው በፊት እነዚህን እርምጃዎች ልትወስድ ይገባል። * በተለይም ደም መውሰድ ሊያስከትል የሚችለውን ከባድ የጤና እክል በመፍራት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ለማክበር ሲሉ ደም መውሰድ የማይፈልጉ እናቶች እንዲህ ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 15:20, 28, 29 

እንደነዚህ ያሉት ነፍሰ ጡር ሴቶች የጤና ክትትል የሚያደርግላቸው ግለሰብ (ሐኪምም ሆነ አዋላጅ) በደም ምትክ የሚሰጡ አማራጭ ሕክምናዎችን በመስጠት ረገድ ብቃትና ልምድ ያለው መሆኑን ለማረጋገጥ የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ነፍሰ ጡር እናቶችና ባሎቻቸው፣ ሆስፒታሉ ወይም የማዋለጃ አገልግሎት የሚሰጠው ጤና ጣቢያ ፍላጎታቸውን ለማክበር ፈቃደኛ መሆኑን ማረጋገጣቸው ብልህነት ነው። * የሚከተሉትን ሁለት ጥያቄዎች ሐኪሙን ልትጠይቁት ይገባል፦ 1. እናቲቱ ወይም ሕፃኑ ብዙ ደም ቢፈሳቸው ወይም ሌላ ውስብስብ ችግር ቢፈጠር ምን ታደርጋለህ? 2. አንተ በሌለህበት ወቅት እናቲቱ ብትወልድ ፍላጎቷ እንዲከበርላት ለማድረግ ምን አማራጭ ዝግጅት ታደርጋለህ?

እርግጥ ነው፣ አስተዋይ የሆነች ሴት ምጥ ሳይጀምራት በፊት የደሟ መጠን እንዳልወረደ ወይም በትክክለኛ ሁኔታ ላይ መሆኑን ሐኪሟን ትጠይቃለች። ሐኪሙም የነፍሰ ጡሯን ደም ለመጨመር ፎሊክ አሲድና ቢ ቡድን ውስጥ የሚመደቡ ሌሎች ቪታሚኖችን እንዲሁም አይረን እንድትወስድ ይመክራት ይሆናል።

በተጨማሪም ሐኪሙ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን ከግምት ያስገባል። ለምሳሌ ያህል፣ ነፍሰ ጡሯ የቅድመ ወሊድ የሕክምና ክትትል ስታደርግ ትኩረት የሚያሻው የጤና እክል እንዳለባት የሚያሳይ ነገር ነበር? ይህች ሴት ብዙ ላለመቆም መጠንቀቅ ያስፈልጋታል? ተጨማሪ እረፍት ማግኘት ይኖርባታል? ክብደት መጨመር ወይም መቀነስ አሊያም ተጨማሪ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋት ይሆን? ለአፏም ሆነ በአጠቃላይ ለሰውነቷ ንጽሕና ተጨማሪ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋታል?

በእርጉዝ ሴቶች ላይ የሚታይ የድድ በሽታ ፕሪኤክላምፕሲያ በተባለው ከባድ የጤና እክል የመያዝን አጋጣሚ ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል ጥናቶች ያመለክታሉ፤ ይህ በሽታ ኃይለኛ ራስ ምታት ሊያስከትል እንዲሁም የደም ግፊት በድንገት እንዲጨምርና በሰውነት ውስጥ ከሚያስፈልገው በላይ ፈሳሽ እንዲኖር ሊያደርግ ብሎም ሌሎች ችግሮችን ሊያመጣ ይችላል። * ፕሪኤክላምፕሲያ ያለ ጊዜው መውለድን ሊያስከትል የሚችል ሲሆን በተለይም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ለሕፃናትና ለእናቶች ሞት ዋና መንስኤ ነው።

በእርግጥም ጠንቃቃ የሆነ ሐኪም ነፍሰ ጡሯ በሰውነቷ ውስጥ ኢንፌክሽን መኖሩን የሚጠቁሙ ምልክቶችን ትኩረት ሰጥቶ ይከታተላል። እንዲሁም ያለ ጊዜዋ ምጥ ከጀመራት ሕይወቷን ለማትረፍ በአፋጣኝ ሆስፒታል እንድትገባ ያደርጋል።

በዓለም የጤና ድርጅት ውስጥ ከእርግዝና ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማስቀረት የተቋቋመው ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ካሲ ሞኒሩል ኢስላም “ሴቶች ሕይወት ለመስጠት ሲሉ ለሞት ይጋለጣሉ” ብለዋል። ይሁን እንጂ በእርግዝና እና በወሊድ ወቅት እንዲሁም ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ ባለው ጊዜ ጥሩ የሕክምና ክትትል ማግኘት ሞትን ጨምሮ በርካታ የጤና ችግሮችን ለማስቀረት ሊረዳ ይችላል። በእርግጥም ጥሩ ጤንነት እንዲኖርሽ ጥረት ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ደግሞም ጤናማ ልጅ እንዲኖርሽ ከፈለግሽ ጤናማ እናት ለመሆን የምትችይውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብሻል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 በመጀመሪያው የዕብራይስጥ ጽሑፍ ላይ ይህ ጥቅስ የሚያመለክተው በእናቲቱም ሆነ ባልተወለደው ሕፃን ላይ ለሞት የሚያደርስ ጉዳት መድረሱን ነው።

^ አን.21 የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ባልና ሚስት ልጃቸው ከመወለዱ በፊት በአካባቢው ያለውን የይሖዋ ምሥክሮች የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ሊያማክሩ ይችላሉ። የዚህ ኮሚቴ አባላት ሆስፒታሎችንና ሐኪሞችን ተዘዋውረው በማነጋገር የይሖዋ ምሥክር ለሆኑ ሕሙማን ያለ ደም ስለሚሰጡ ሕክምናዎች መረጃ ይሰጧቸዋል። በተጨማሪም የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴው የሕመምተኛውን እምነት የሚያከብርና ያለ ደም ሕክምና በመስጠት ረገድ ልምድ ያለው ሐኪም በማፈላለግ እገዛ ሊያደርግ ይችላል።

^ አን.24 የድድ በሽታ ፕሪኤክላምፕሲያ በተባለው የጤና እክል የመያዝን አጋጣሚ ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥናቶች ማድረግ ቢያስፈልግም ምንጊዜም ቢሆን ለድድሽና ለጥርስሽ ጥሩ እንክብካቤ ማድረግ ብልህነት ነው።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ጥቅምት 2007 ታትሞ በወጣው አኃዛዊ መረጃ መሠረት ከእርግዝና ጋር በተያያዙ ችግሮች የተነሳ በየደቂቃው አንዲት ሴት ትሞታለች፤ ይህም በዓመት 536,000 ሴቶች ይሞታሉ ማለት ነው።—ዩናይትድ ኔሽንስ ፖፑሌሽን ፈንድ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በየዓመቱ 3.3 ሚሊዮን ሕፃናት ሞተው የሚወለዱ ሲሆን 4 ሚሊዮን ሕፃናት ደግሞ ከተወለዱ በኋላ ባሉት 28 ቀናት ውስጥ ይሞታሉ።”ዩኤን ክሮኒክል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 በእርግዝና ወቅት መደረግ ያለበት ዝግጅት

1. የሕክምና ክትትል የምታደርጊበትን ሆስፒታል፣ የሚከታተልሽን ሐኪም ወይም አዋላጅ ቀደም ብለሽ በጥንቃቄ ምረጪ።

2. ክትትል ወደሚያደርግልሽ ሐኪም ወይም አዋላጅ አዘውትረሽ መሄድሽ ከእነዚህ ባለሙያዎች ጋር ወዳጅነት እንድትመሠርቺና በእነሱ ላይ እምነት እንድትጥይ ይረዳሻል።

3. ለጤንነትሽ ከፍተኛ ትኩረት ስጪ። የምትችዪ ከሆነ ለነፍሰ ጡር ሴቶች የሚታዘዙ ቪታሚኖችን ውሰጂ፤ ሆኖም ክትትል የሚያደርግልሽ ሐኪም ካላዘዘልሽ በስተቀር ማንኛውንም መድኃኒት (ያለ ሐኪም ትእዛዝ የሚሸጡ መድኃኒቶችንም ጭምር) አትውሰጂ። የአልኮል መጠጥ አለመውሰድሽ ጥበብ ነው። አልኮልን አላግባብ ስለመጠቀምና ስለ አልኮል ሱሰኝነት ጥናት የሚያደርግ ብሔራዊ የምርምር ተቋም እንዲህ ይላል፦ “[ነፍሰ ጡር] እናቶች ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ መጠጣታቸው የበለጠ አደገኛ የሚሆነው ለሕፃኑ ቢሆንም በእርግዝና ወቅት አንዲት ሴት በማንኛውም መጠን የአልኮል መጠጥ መጠጣቷ ችግር ስለማስከተሉ በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር የለም።”

4. ከመውለጃሽ ጊዜ በፊት (ከ37 ሳምንት በፊት) የምጥ ሕመም ከተሰማሽ ክትትል የሚያደርግልሽን ሐኪም ወይም የሆስፒታሉን የማዋለጃ ክፍል ወዲያውኑ አነጋግሪ። በአፋጣኝ እርምጃ መውሰድሽ ያለ ጊዜሽ እንዳትወልጂ ሊረዳሽ ይችላል፤ እንዲሁም ያለጊዜው ከመውለድ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለማስወገድ ሊረዳሽ ይችላል። *

5. ከሕክምና ጋር በተያያዘ ውሳኔሽን በጽሑፍ አስፍሪ። ለምሳሌ ብዙዎች የሕክምና መመሪያ ካርድ የተባለውን ሰነድ ቀደም ብለው መሙላታቸው ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። በአገርሽ የሚሠራበትንና በሕግ ተቀባይነት ያለውን የሕክምና መመሪያ ካርድ ለማወቅ ጥረት አድርጊ።

6. ከወለድሽ በኋላ ለራስሽም ሆነ ለሕፃኑ ጤንነት ጥንቃቄ አድርጊ፤ በተለይም ሕፃኑ የተወለደው ያለጊዜው ከሆነ ይህን ማድረግሽ አስፈላጊ ነው። የሆነ ችግር ካስተዋልሽ ወዲያውኑ የሕፃኑን ሐኪም አማክሪ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.41 የደማቸው መጠን አነስተኛ የሆነ ያለ ጊዜያቸው የተወለዱ ሕፃናት ሰውነታቸው በቂ ቀይ የደም ሕዋስ ማመንጨት ስለሚያስቸግረው አብዛኛውን ጊዜ ደም ይሰጣቸዋል።