በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለም በተቃወሰበት ጊዜ

2 | መተዳደሪያህ

2 | መተዳደሪያህ

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች በየቀኑ ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና ይላሉ። የሚያሳዝነው ደግሞ በዓለም ላይ የተከሰቱት ቀውሶች ሁኔታው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሆን አድርገዋል። እንዴት?

  • በአንድ አካባቢ ላይ ቀውስ ሲከሰት ኑሮ ይወደዳል፤ ለምሳሌ የምግብ ዋጋና የቤት ኪራይ ይጨምራል።

  • ቀውስ ባለባቸው አካባቢዎች ሥራ አጥነት ይጨምራል፤ ወይም ሰዎች የሚያገኙት ደሞዝ ይቀንሳል።

  • አደጋዎች የንግድ ቦታዎችን፣ መኖሪያ ቤቶችን ወይም ሌሎች ንብረቶችን ያበላሻሉ ወይም ያወድማሉ፤ ይህም ብዙዎችን ለድህነት ይዳርጋል።

ማወቅ ያለብህ ነገር

  • ገንዘብህን በአግባቡ የምትይዝ ከሆነ ቀውስ በሚፈጠርበት ወቅት የተሻለ ዝግጁነት ይኖርሃል።

  • ገንዘብ አላፊ ጠፊ ነው፤ ዛሬ ያለህ ገቢ፣ የቆጠብከው ገንዘብ ወይም ንብረትህ ነገ ዋጋውን ሊያጣ ይችላል።

  • ገንዘብ የማይገዛቸው ነገሮች አሉ፤ ለምሳሌ ደስታ ወይም ሰላማዊ የቤተሰብ ሕይወት በገንዘብ ሊገዛ አይችልም።

አሁን ማድረግ የምትችለው ነገር

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ምግብና ልብስ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:8

ባለን ነገር መርካት ሲባል ያማረን ነገር ሁሉ ይኑረን አለማለት ነው፤ ለዕለት የሚያስፈልገን ነገር ከተሟላልን በዚያ እንረካለን። በተለይ መተዳደሪያችንን የሚነካ ችግር ሲያጋጥም ይህ አመለካከት አስፈላጊ ነው።

ባለህ ነገር መርካት በአኗኗርህ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ሊጠይቅብህ ይችላል። ከአቅምህ በላይ የምትኖር ከሆነ ያለብህ የገንዘብ ችግር እየባሰ መሄዱ አይቀርም።