በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርትና ገንዘብ ሕይወትን አስተማማኝ ለማድረግ ይረዳሉ?

ትምህርትና ገንዘብ ሕይወትን አስተማማኝ ለማድረግ ይረዳሉ?

ብዙዎች፣ የተማሩና ሀብታም የሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው አስተማማኝ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ዩኒቨርሲቲ ገብቶ መማር ጎበዝ ሠራተኛና የተሻለ ዜጋ ለመሆን እንዲሁም ጥሩ የቤተሰብ ሕይወት ለመምራት እንደሚረዳ ያምናሉ። በተጨማሪም ጥሩ ትምህርት፣ የተሻለ ክፍያ የሚያስገኝ ሥራ ለመያዝ እንደሚያስችልና ከፍ ያለ ገቢ ያላቸው ሰዎች ደስተኛ እንደሚሆኑ ያስባሉ።

ብዙዎች የሚያደርጉት ምርጫ

በቻይና የሚኖረው ጃንግ ቸን የሰጠውን አስተያየት እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “ከድህነት መላቀቅ የምችልበት ብቸኛው መንገድ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ መያዝ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ‘አስደሳችና አርኪ ሕይወት ለመምራት ከፍተኛ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ መያዝ አለብኝ’ የሚል አስተሳሰብ ነበረኝ።”

ብዙዎች የወደፊት ሕይወታቸውን አስተማማኝ ለማድረግ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ገብተው መማር ይፈልጋሉ፤ ምናልባትም በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር ሲሉ ወደ ሌላ አገር ሊሄዱ ይችላሉ። በኮቪድ-19 ምክንያት ዓለም አቀፍ ጉዞ ማድረግ ከባድ እስከሆነበት ጊዜ ድረስ ይህ ነገር በጣም የተለመደ ሆኖ ነበር። የኢኮኖሚ ትብብርና እድገት ድርጅት (OECD) በ2012 ባወጣው ሪፖርት ላይ እንደገለጸው “ወደ ውጭ አገር ሄደው ከሚማሩ ተማሪዎች መካከል 52 በመቶ የሚሆኑት የእስያ ተወላጆች ናቸው።”

ብዙውን ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን ውጭ አገር ወዳለ ዩኒቨርሲቲ ልከው ለማስተማር ሲሉ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ይከፍላሉ። በታይዋን የሚኖረው ቺሺያንግ እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆቼ ሀብታሞች አይደሉም፤ ግን እኔን ጨምሮ አራት ልጆቻቸውን ዩናይትድ ስቴትስ ወዳለ ኮሌጅ ልከው አስተምረዋል።” እንደ ሌሎች በርካታ ቤተሰቦች ሁሉ የቺሺያንግ ቤተሰቦችም ለዚህ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ሲሉ ከባድ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል።

ውጤቱ ምን ያሳያል?

ከፍተኛ ትምህርት በመከታተልና ሀብት በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት የመሩ በርካታ ሰዎች የኋላ ኋላ ለብስጭት ተዳርገዋል

ትምህርት ሕይወትን የሚያሻሽልባቸው አንዳንድ መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ግን ሰዎች ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ የጠበቁትን ዓይነት ሕይወት አያገኙም። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ሰዎች ለዓመታት መሥዋዕትነት ከፍለውና ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቀው ትምህርታቸውን ቢያጠናቅቁም የፈለጉትን ሥራ ማግኘት አልቻሉም። ሬቸል ሙዪ የተባለች ጋዜጠኛ በሲንጋፖር ቢዝነስ ታይምስ ላይ ያወጣችው ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “ከተመረቁ በኋላ ሥራ አጥተው የሚቀመጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል።” በታይዋን የሚኖር ጂየንጂየ የተባለ የዶክትሬት ምሩቅ “ብዙዎች ከተመረቁበት ትምህርት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ሥራ ለመያዝ ተገደዋል” በማለት ተናግሯል።

አንዳንዶች በፈለጉት የሙያ መስክ ሥራ ቢያገኙም ሕይወታቸው ያሰቡትን ያህል አስተማማኝ አልሆነም። በታይላንድ የሚኖረው ናይረን ዩናይትድ ኪንግደም ሄዶ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቆ ከተመለሰ በኋላ በተማረበት መስክ ሥራ አገኘ። እንዲህ ብሏል፦ “እንደጠበቅኩት በዲግሪ መመረቄ ከፍተኛ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ እንድይዝ ረድቶኛል። ግን ይህን ደሞዝ ለማግኘት ስል ብዙ ሰዓት መሥራት ይጠበቅብኝ ነበር፤ የሥራ ጫናውም ከባድ ነበር። ከጊዜ በኋላ ድርጅቱ እኔን ጨምሮ አብዛኞቹን ሠራተኞቹን ከሥራ ቀነሰ። ይህ አጋጣሚ የትኛውም ሥራ ቢሆን አስተማማኝ እንዳልሆነ እንድገነዘብ አድርጎኛል።”

ሀብታም የሆኑ ወይም የተደላደለ የሚባል ሕይወት የሚመሩ ሰዎችም እንኳ የቤተሰብ ወይም የጤና ችግር ያጋጥማቸዋል፤ የገንዘብ ጉዳይም ያስጨንቃቸዋል። በጃፓን የሚኖረው ካትሱቶሺ እንዲህ ሲል በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “ብዙ ገንዘብ የነበረኝ ቢሆንም ፉክክሩና ሰዎች በምቀኝነት ተነሳስተው የሚያደርሱብኝ በደል አማሮኝ ነበር።” በቬትናም የምትኖር ላም የተባለች ሴት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ሰዎች ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ መያዛቸው የወደፊት ሕይወታቸውን አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚረዳቸው ይሰማቸዋል። እውነታው ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው፤ እንዲህ ያለ ሥራ ያላቸው ሰዎች ብዙ ይጨነቃሉ፣ ጤንነታቸው ይጎዳል እንዲሁም ስሜታዊ ቀውስና የመንፈስ ጭንቀት ያጋጥማቸዋል።”

ፍራንክሊንን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ትምህርትን ከመከታተልና ሀብት ከማሳደድ የበለጠ ቦታ የሚሰጣቸው ነገሮች እንዳሉ ተገንዝበዋል። አንዳንዶች ቁሳዊ ሀብትን በማሳደድ ላይ ከማተኮር ይልቅ ጥሩ ሰው በመሆንና ሌሎችን በመርዳት የወደፊት ሕይወታቸውን የተሻለ ማድረግ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። ሆኖም እንዲህ ያለውን አኗኗር መከተል የወደፊት ሕይወትን አስተማማኝ ለማድረግ ይረዳል? ቀጣዩ ርዕስ የዚህን ጥያቄ መልስ ይዟል።