በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ከሁሉ የላቀውን የአምላክ ስጦታ ትቀበላለህ?

ከሁሉ የላቀው የአምላክ ስጦታ—ውድ የሆነበት ምክንያት

ከሁሉ የላቀው የአምላክ ስጦታ—ውድ የሆነበት ምክንያት

አንድን ስጦታ ውድ የሚያደርገው ምንድን ነው? አራት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፦ (1) ስጦታውን የሰጠው አካል፣ (2) ስጦታው የተሰጠበት ምክንያት፣ (3) ስጦታውን ለመስጠት የተከፈለው መሥዋዕት እና (4) የስጦታው አስፈላጊነት ናቸው። በእነዚህ ነጥቦች ላይ ማሰላሰላችን አምላክ ለሰጠን ከሁሉ የላቀ ስጦታ ይኸውም ለቤዛው ያለንን አድናቆት ለማሳደግ ይረዳናል።

ስጦታውን የሰጠው አካል

አንዳንድ ስጦታዎችን ከፍ አድርገን የምንመለከታቸው ሥልጣን ካለው ወይም በጣም ከምናከብረው ሰው ስለተቀበልናቸው ሊሆን ይችላል። ሌሎች ስጦታዎች ደግሞ የወጣባቸው ገንዘብ አነስተኛ ቢሆንም ያገኘናቸው ከምንወደው የቤተሰብ አባል ወይም ከቅርብ ወዳጃችን በመሆኑ ትልቅ ቦታ እንሰጣቸዋለን። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ጆርዳን ከራስል የተቀበለውን ስጦታ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ታዲያ ይህ ከቤዛው ስጦታ ጋር በተያያዘ የሚሠራው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ ደረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም [እንደላከው]” ይናገራል። (1 ዮሐንስ 4:9) ይህ ሐቅ ቤዛውን ከሁሉ የላቀ ስጦታ ያደርገዋል። ከአምላክ የበለጠ ሥልጣን ያለው አካል የለም። አንድ መዝሙራዊ አምላክን አስመልክቶ ሲጽፍ “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል [ነህ]” ብሏል። (መዝሙር 83:18) ስጦታ ሊሰጠን የሚችል ከዚህ የሚበልጥ ሥልጣን ያለው አካል ሊኖር ይችላል?

በሁለተኛ ደረጃ፣ አምላክ “አባታችን” ነው። (ኢሳይያስ 63:16) እንዴት? ሕይወት የሰጠን እሱ ነው። በተጨማሪም አንድ ጥሩ አባት ለልጆቹ እንደሚያስብ ሁሉ እሱም ምንጊዜም ያስብልናል። አምላክ የጥንት ሕዝቦቹን ኤፍሬም ብሎ በመጥራት እንዲህ ብሏል፦ “ኤፍሬም ከፍ አድርጌ የምመለከተው ውድ ልጄ አይደለም? . . . አንጀቴ ለእሱ የሚንሰፈሰፈው ለዚህ ነው። ደግሞም እራራለታለሁ።” (ኤርምያስ 31:20) አምላክ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ አገልጋዮቹም ተመሳሳይ ስሜት አለው። እሱ ሁሉን ቻይ የሆነ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ታማኝ አባታችንና ወዳጃችን ነው። ይህ ከእሱ ለምናገኘው ስጦታ ሁሉ አድናቆት እንዲኖረን አያደርግም?

ስጦታው የተሰጠበት ምክንያት

አንዳንድ ስጦታዎችን ከፍ አድርገን የምንመለከታቸው ስጦታውን የሰጠን አካል እንዲህ ያደረገው ተገዶ ሳይሆን ከልብ በመነጨ ፍቅር ተነሳስቶ በመሆኑ ነው። ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ተነሳስቶ ስጦታ የሚሰጥ ሰው፣ ላሳየው ደግነት በምላሹ ምንም እንዲደረግለት አይጠብቅም።

አምላክ ልጁን ለእኛ የሰጠን ስለሚወደን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ . . . አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል።” አምላክ ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? “እኛ በእሱ [በኢየሱስ] አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል” ነው። (1 ዮሐንስ 4:9) አምላክ ይህን የማድረግ ግዴታ ነበረበት? በፍጹም! “ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ” የአምላክ “ጸጋ” መገለጫ ነው።—ሮም 3:24

የአምላክ ስጦታ፣ “ጸጋ” ወይም እንዲሁ የተገኘ ነፃ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።” (ሮም 5:8) አምላክ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ስላለው ደካማ፣ ምስኪን እንዲሁም ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆችን ለመርዳት ተነሳስቷል። ይህ ውለታ፣ ልንከፍል የምንችለው ወይም ይገባናል የምንለው አይደለም። አምላክ የሰጠን ስጦታ ወደር የማይገኝለት የፍቅር መግለጫ ነው።

ስጦታውን ለመስጠት የተከፈለው መሥዋዕት

ሌሎች ስጦታዎች ደግሞ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጣቸው ሰጪው ትልቅ መሥዋዕት ስለከፈለባቸው ነው። አንድ ሰው እሱ ራሱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ነገር ከራሱ ወስዶ ለእኛ ቢሰጠን ስጦታውን ከፍ አድርገን እንደምናየው ምንም ጥርጥር የለውም።

አምላክ “አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐንስ 3:16) አምላክ ልጁን ከምንም ነገር በላይ ይወደዋል፤ በመሆኑም ከዚህ የበለጠ ስጦታ ሊሰጠን አይችልም። አጽናፈ ዓለምን በፈጠረባቸው ሕልቆ መሳፍርት የሌላቸው ዘመናት ኢየሱስ አብሮት የሠራ ሲሆን አምላክም ‘በእሱ የተነሳ ልዩ ደስታ ይሰማው ነበር።’ (ምሳሌ 8:30) ኢየሱስ የአምላክ ‘ተወዳጅ ልጅ’ እንዲሁም “የማይታየው አምላክ አምሳል” ነው። (ቆላስይስ 1:13-15) በሁለቱ መካከል ያለውን ያህል የጠበቀ ወዳጅነት ሊኖር አይችልም።

ሆኖም አምላክ ‘ለገዛ ልጁ እንኳ አልሳሳም።’ (ሮም 8:32) ይሖዋ የሰጠን ምርጡን ነው። የትኛውም ስጦታ ይህን ያህል መሥዋዕትነት ሊያስከፍለው አይችልም።

የስጦታው አስፈላጊነት

ለአንድ ስጦታ ከፍ ያለ ቦታ የምንሰጥበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ስጦታው በጣም የሚያስፈልገን ምናልባትም በአስቸኳይ ማግኘት ያለብን ስለሆነ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ከባድ በሽታ ይዞሃል እንበል፤ ሆኖም የሕክምና ወጪውን ለመሸፈን አቅምህ አይፈቅድም። በዚህ ጊዜ አንድ ሰው የሕክምና ወጪውን ለመሸፈን ፈቃደኛ ቢሆን በጣም አመስጋኝ አትሆንም?

“ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ።” (1 ቆሮንቶስ 15:22) የአዳም ዘሮች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም ከሕመምና ከሞት ማምለጥ አንችልም፤ እንዲሁም በራሳችን ከአምላክ ጋር ልንታረቅም ሆነ ከኃጢአት ነፃ ልንሆን አንችልም። ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን “ሕያው” የማድረግ አቅምም ቢሆን የለንም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንዳቸውም ቢሆኑ ሌላውን ሰው መዋጀት፣ ወይም ለእሱ ቤዛ የሚሆን ነገር ለአምላክ መክፈል ጨርሶ አይችሉም፤ (ለሕይወታቸው የሚከፈለው የቤዛ ዋጋ እጅግ ውድ ስለሆነ መቼም ቢሆን ከአቅማቸው በላይ ነው)።” (መዝሙር 49:7, 8) በእርግጥም የቤዛውን ዋጋ ለመክፈል አቅም ስለሌለን የግድ የሌላ አካል እርዳታ ያስፈልገናል። የሚረዳን ከሌለ ምንም ተስፋ ሊኖረን አይችልም።

ይሖዋ ለእኛ ባለው ታላቅ ፍቅር ተነሳስቶ “ለሕክምና” የሚያስፈልገውን ወጪ በፈቃደኝነት እንደሸፈነልን ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል፤ በመሆኑም በኢየሱስ አማካኝነት ‘ሁላችንም ሕያው እንሆናለን።’ ቤዛው ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? “የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።” በእርግጥም በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ እምነት ማሳደር የኃጢአት ይቅርታ እና የዘላለም ሕይወት ያስገኛል። (1 ዮሐንስ 1:7፤ 5:13) ቤዛው በሞት ለተለዩን የምንወዳቸው ሰዎችስ ምን ጥቅም ያስገኛል? “ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል ስለሆነ የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው [በኢየሱስ] በኩል ነው።”—1 ቆሮንቶስ 15:21 *

የኢየሱስ መሥዋዕት ወደር የማይገኝለት ስጦታ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ስጦታ እጅግ ከፍተኛ ሥልጣን ካለውና በጣም ከሚወደን አካል የተሰጠ ነው። እንዲሁም የይሖዋ አምላክን ያህል ከፍተኛ መሥዋዕት ከፍሎ ስጦታ ሊሰጠን የሚችል ማንም የለም። በተጨማሪም የትኛውም ስጦታ ከኃጢአትና ከሞት የታደገንን ስጦታ ያህል አስፈላጊ ሊሆን አይችልም። በእርግጥም በቃላት ሊገለጽ የማይችለውን የቤዛውን ያህል ዋጋ ሊኖረው የሚችል ስጦታ የለም።

 

^ አን.19 አምላክ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት ስላለው ዓላማ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ተመልከት፤ መጽሐፉ www.pr418.com/am ላይም ይገኛል።