በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ ተማሪ ያጋጠመው ግራ መጋባት

አንድ ተማሪ ያጋጠመው ግራ መጋባት

ፒተር ጭንቅ ብሎት ወንበሩ ላይ እንደተቀመጠ ይቁነጠነጣል። በጣም የሚያከብራት መምህርቱ ቻርልስ ዳርዊንና እሱ ያረቀቀው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ሳይንሳዊ ግንዛቤ እንዲሰፋ ብሎም የሰው ልጆች ከአጉል እምነት እንዲላቀቁ ያደረጉት እንዴት እንደሆነ አስረድታ መጨረሷ ነበር። ከዚያም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲናገሩ ተማሪዎቿን ጋበዘቻቸው።

ፒተር ግራ ተጋብቷል። ወላጆቹ አምላክ ምድርንም ሆነ በምድር ላይ ያሉትን ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ እንደፈጠረ አስተምረውታል። ስለ ፍጥረት የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እምነት የሚጣልበት እንደሆነ፣ ዝግመተ ለውጥ ግን ምንም ተጨባጭ ማስረጃ የሌለው ተራ ጽንሰ ሐሳብ እንደሆነ አስረድተውታል። የፒተር መምህርትም ሆነች ወላጆቹ እሱ ጥሩ ነገር እንዲገጥመው የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። ታዲያ ፒተር ማመን የሚገባው ማንን ነው?

በእያንዳንዱ የትምህርት ዘመን በመላው ዓለም በሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች ይህን የመሰለ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ታዲያ ፒተርና እንደ እሱ ያሉ ሌሎች ተማሪዎች ምን ማድረግ አለባቸው? በዚህ ጉዳይ ላይ የየራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ ይገባቸዋል ቢባል አትስማማም? ስለ ዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብም ሆነ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ ስለሚናገረው ሐሳብ የሚቀርቡትን ማስረጃዎች ከመረመሩ በኋላ የትኛውን እንደሚያምኑ ራሳቸው መወሰን አለባቸው።

እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎች የሚያስተምሩትን በጭፍን እንዳንቀበል ያስጠነቅቃል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች ‘በማሰብ ችሎታቸው’ ተጠቅመው የተማሩትን በመመርመር ትክክል መሆኑን እንዲያረጋግጡ ያበረታታል።—ሮም 12:1, 2

ይህ ብሮሹር በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሕይወት በፍጥረት እንደተገኘ የሚገልጽ ትምህርት እንዲሰጥ የሚፈልጉ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ ታስቦ የተዘጋጀ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዓላማው ሕይወት ድንገት እንደተገኘና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወት አመጣጥ የሚገልጸው ዘገባ አፈ ታሪክ እንደሆነ የሚያስተምሩ ሰዎች የሚያቀርቧቸው ሐሳቦች ትክክል መሆን አለመሆናቸውን መመርመር ነው።

ሴል የሕይወት መሠረታዊ ነገር ስለሆነ በዚህ ብሮሹር ውስጥ በሴል ላይ እናተኩራለን። ሴሎች የተሠሩበትን ሁኔታ በተመለከተ አንዳንድ አስደናቂ ሐሳቦችን ትመለከታለህ። በተጨማሪም የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ የሚደግፉ መላምቶች ትክክል መሆን አለመሆናቸውን እንድትገመግም የሚረዱ ጥያቄዎች ይቀርቡልሃል።

ይዋል ይደር እንጂ ሁላችንም ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው ወይስ በዝግመተ ለውጥ? የሚለውን ጥያቄ መጠየቃችን አይቀርም። ከዚህ በፊትም ቢሆን ይህን ርዕሰ ጉዳይ በቁም ነገር ሳታስብበት አልቀረህም። ይህ ብሮሹር ብዙ ሰዎች ‘ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው’ ብለው እንዲያምኑ ካደረጓቸው ማስረጃዎች መካከል ጥቂቶቹን ይዟል።